Wednesday, October 23, 2013

የእግዚአብሔር ቃል

የእግዚአብሔር ቃል


    I.      የእግዚአብሔር ቃል ምንድን ነው
ይህንን ጥያቄ ለመመለስም ሆነ ለትምህርቱ መግቢያ እንዲሆነን ከትንቢተ ሆሴዕ 8፡ 12 እናንብብ፦

 የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል”።
ጥቅሱ እግዚአብሔር ቃሉን በተመለከተ በኤፍሬም ላይ ያለውን ቅሬታ ያስታውቃል  ኤፍሬም ለእግዚአብሔር ቃል ያሳየው ይህ ዝንባሌ በእግዚእብሔር መጽሐፍ ላይ የተሰራ በደል ነበር  ጥቅሱም እግዚአብሔር ለሕጉ ወይም ለቃሉ የሰጠውን ዋጋ እና ሰዎች ደግሞ በፊናቸው ለእግዚአብሔር ቃል  የሰጡትን ዋጋ እና ያሳዩትን ምላሽ ያመለክታል  ይህ የሰዎች ምላሽ ከወደቀው ሰው ባሕርይ የሚወጣ የተለመደ ዝንባሌ ነው  ከዚህ ጨለማ ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ብርሃን ብቻ ነው
በዚሕ ጥቅሰ አንደምናየው እግዚአብሔር የሕጉ ወይም የቃሉ ጸሐፊ ሆኖ ተገልጦአል ስለዚሕ አግዚአብሔር የጻፈው ይህ መጽሐፍ ቃሉ ታላቅ ነው  ታላላቅ ትምሕርቶች አሉት  በትንቢተ ኢሳይያስ 42፡ 18-25 በተለይም ቁጥር 21 ላይ
እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ”። ይላል
ቃሉ ክቡር ነው፣ ቃሉ ስልጣን አለው
በዚሕ የመጀመሪያው የትምሕርት ክፍል አራት ነጥቦችን እንመለከታለን  እነርሱም
1)     መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው
2)    ልዩ ልዩ የእምነት ክፍሎች እና ቤተ እምነቶች ስለ ቃሉ ምን እንደሚያምኑ
3)    መገለጥ እና
4)    የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን የሚሉት ናቸው

1)    መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው
ከላይ ያየነው የሆሴዕ ጥቅስ እንደሚያስረዳው ጽፌለታለሁ የሚለው ቃሉን የጻፈው እና የሰጠው የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል እርግጥ ነው መጽሐፉ ሲጻፍ እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ከ40 የማያንሱ ሰዎች አሉ ነገር ግን የተባረከው እምነታችን ይህ መጽሐፍ የሕያው አግዚአብሔር የጽሑፍ ስራ ነው እያንዳንዱ ፊደል ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ጣቶች የተቀረጸ ነው እያንዳንዱ ቃል ከዘላለማዊው አምላክ ከናፍርት የወጣ ነው እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የተጻፈ ነው
ይህ መጽሐፍ በሰዎች እጅ ባለ ብዕር ሲጻፍ የበላይ ተቆጣጣሪው ራሱ እግዚአብሔር ነበር  በሁሉም ሰፈራ ሲናገር የነበረው ራሱ እግዚአብሔር ነው  መጽሐፉም የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ድምጽ አይደለም  ቃሎቹም አጥናፍ አለሙን እና በውሰጡ የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ እና ለሁሉም ሕይወትንና እስትንፋስን የሰጠ ሕያውን እና ግዑዙን ሁሉ የሰራ የማይታየው ሁሉን ቻይ የሆነው የዘላለማዊው አምላክ የእግዚአብሔር ናቸው
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ነው  አተኩረን ስናየውና ተጠግተን ስንሰማው ''እኔ የእግዚአብሔር ጽሑፍ ነኝ ገጾቼን ግለጥና በእግዚአብሔር ብዕር መጻፌን እይ አንብበኝ እና የኔ ደራሲ ማን እንደሆነ በየገጾቹ ራሱን ሲገልጥ ተመልከት'' ሲለን እንሰማዋለን
ይህንን እውነት የበለጠ ለማስተዋል የእግዚአብሔርን ቃል ባህርያት በዝርዝር ሊያስተምረን የሚችለውን የ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 15-4፡ 2 ያለውን ክፍል ተጠግተን እናያለን
“ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።
በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም”።
ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ቃል ከተነገሩ በርካታ ታላላቅ ምንባባት መካከል አንዱ ነው ምናልባትም ከ119ኛው መዝሙር ቀጥሎ ስለ እግዚአብሔር ቃል የሚናገር ጎላ ያለ ክፍል ነው በዚህ ምንባብ ብቻ ቃሉን በተመለከተ ቢያንሰ 10 የሚደርሱ ምስክርነቶችን እናገኛለን
) የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ እና ቀላል ነው
ሐዋርያው ጢሞቴዎስን ሲያስታውሰው “ከሕፃንነትህም ጀምረህ መጻሕፍትን አውቀሃል” ይለዋል ይህም አባባሉ የቃሉን ግልጽነትና ቀላልነት ያመለክታል፣ ሕፃንም እንክዋን ሊረዳውና ሊያውቀው ይችላል በአዲስ ኪዳን ተዘግበውልን ከሚገኙ የኢየሱስ ጸሎቶች መካከል በአንዱ
“አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና” (ማቴ 11፡ 25-26) ሲል እንሰማዋለን
ዳዊትም በመዝሙሩ የእግዚአብሔርን ቃል ስመልክቶ
“የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል” (መዝ 119፡ 130) ሲል
ጨምሮም
የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል” (መዝ 19፡ 7) ይላል
የንባብ ክፍላችን እንደሚያስረዳው ቅዱሳት መጻሕፈት ጥበብን ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው አንድ ሰው በሰማያት ላይ ሆኖ ሊያውቀው የተገባው ነገር ግልጽ ቀላል እና የማያሳስት በሆነ የእግዚአብሔር ቃል ቋንቋ ግልጽ ሆኖ መሰጠቱን ማወቁ ምን ያህል የሚያጽናና እና የሚያስደንቅ ነገር ነው!
ለ) የእግዚአብሔር ቃል ሊታወቅ የሚችል ነው
ሐዋርያው “ቅዱሳት መጻህፍትን አውቀሃል” ሲል ጢሞቴዎስ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያውቅ ይመሰክራል፤ ይህም ቃሉ ሊታወቅ የሚችል መሆኑን ያመለክታል፡፡ ቃሉ ሊታወቅ መቻሉ በመላው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመስክሮለታል፡፡ በአንድ ወቅት ጌታ ኢየሱስ ቃሉ እውነት መሆኑን (ዮሐ 17፡ 7)፣እንዲሁም እውነትን ማወቅ እንደምንችል (ዮሐ 8፡ 32) ተናግሮአል፡፡ በተጨማሪም ኢየሱስ
“ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል” (ዮሕ 7፡ 17) ሲል ተናግሮአል፡፡
ጳውሎስም፡- “ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ”  ሲል ተናግሮአል፡፡
በእርግጥም ጴጥሮስም ደግሞ፣ በእግዚአብሔር እውቀት በዓለም ካለው ጥፋት እንዳመለጥን ከነገረን በኁዋላ፣ ቀጥሎ የሚነግረን ካወቅነው በኁዋላ ከእርሱ እንዳንመለስ ሲሆን፣ ያ ካልሆነ ግን አስቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቅነው የተሻለ እንደ ነበር ነው፡፡ (2ጴጥ 2፡20-21)፡፡ እዚህ ላይ እውነት፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ሊታወቅ የሚችል እንደሆነ የሚያሳዩንን አስፈላጊ የሆኑ መመሳሰሎችን እናያለን፡፡ እውነት ሊታወቅ የማይችል እንደሆነ ለማጽናት የሚፈልጉ አንዳንድ ክፍሎችን ለመገዳደር ቀጥሎ ያለውን ልብ በሉ፡-
·         የማይጠፋ / የማያልቅ ምግብ ነው “እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” (1ጴጥ 2፡ 1-3)
·         ልንጠቀምበት የምንችል ሰይፍ ነው “የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” (ኤፌ 6፡ 17)
·         የሚያበራ እሳት ነው “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ 119፡ 105)
·         የሚያንጸባርቅ መስታወት ነው “ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል” (ያዕ 1፡ 23- 25)

) የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ ነው
ጢሞቴዎስ የሚያውቃቸው መጻሕፍት ቅዱሳት እንደሆኑ ጳውሎስ ይናገራል፣ ይኸውም የመጽሐፉን ቅድስና ያመለክታል፡፡ “እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” (1ጴጥ 1፡ 16)፣ ቃሉም ከባህርዩ የተካፈለ ነው! ጳውሎስ ሲጽፍ “ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም” (ገላ 1፡ 11-12) ይለናል፡፡
1.      የእግዚአብሔር ቃል ምንጩ ራሱ እግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ፣ በመላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረውና ይተጻፈው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ለምስሌ ሉቃ 8፡ 11-1፤ ሮሜ 10፡ 17፤ ቲቶ 2፡ 5፤ ኤፌ 6፡17 እና ዕብ 4፡ 12)፡፡
2.     እግዚአብሔር ቅዱስ የሆነውን ያህል ቃሉም ቅዱስ እስከሆነ ድረስ መራከስ የለበትም፤ ይልቁንም በአክብሮት መያዝ አለበት፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ። (መዝ 119፡ 161) ሲል ይጽፋል፡፡
3.     የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ እስከሆነ ድረስ ለቀልድ ልናቀርበው አንችልም፤ የትኛውም ቅዱስ ከሆነ ነገር ጋር ሰዎች እንዲቀልዱ እግዚአብሔር በጭራሽ አይፈቅድም፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ቃሉን በተቀበለበት ስፍራ ቆሞ በነበረበት የእግሩን ጫማ እንዳወለቀ ልብ በሉ (ዘጸ 3፡ 5)፡፡  እግዚአብሔር ማለት በትክክል የተናገረውን ነው፣ የሚናገረውም በትክክል የሆነውን ነው፤ እግዚአብሔር ልክ እንደቃሉ ነው፣ ቃሉም እንደእግዚአብሔር ነው፤ ይህንንም ጉዳይ የሚያጸናልን ምሳሌ የናዳብና የአብዩ (ዘሌ 10፡ 1-7) እንዲሁም የኦዛን (2ሳሙ 6፡ 1-11) ታሪክ ነው፤ ይሞቱት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሲቀልዱ ነው፡፡ ምንም ያህል ኃጢአተኛ ቢሆንም በለዓም እንዲህ አለ፡- “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም” (ዘኁ 22፡ 18)፡፡
4.     የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ ሆኖ ከቅዱስ እግዚአብሔር ባህርይ የተካፈለ እስከሆነ ድርስ እግዚአብሔርና ቃሉ የማይነጣጠሉ ናቸው ብለን መደምደም እንችላለን፡፡ አለቃን ከኃላፊነቱና ከስልጣኑ፣ ክርስቶስን ከትዕዛዛቱ፣ ጌታን ከሕግ አውጪነቱ፣ ነብዩን ከአዋጃዊ ቃሉና መልዕክቱ፣ ወይም ኢየሱስን ከፍርዱ መነጠል ማንም አይቻለውም፡፡ ስጋ የሆነው ቃል እና የተጻፈው ቃል ላይነጣጠሉ ተጣምረዋል፣ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። (ማቴ 19፡ 6)፤ ስለዚህ በዚህ መሰረት ኢየሱስ እንዲህ ይላል፡-  “ብትወዱኝ (እኔን፣ ስጋ የሆንሁትን ቃል)ትእዛዜን  (የተጻፈውን ቃል) ጠብቁ” (ዮሐ 14፡ 15 በቅንፍ የገባው ሃሳብ የራሴ ነው)፡፡
) የእግዚአብሔር ቃል ኃይለኛ ነው
ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ስለሚያውቃቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ሲናገር፣ እነዚህን መጻህፍት የሚችሉ ናቸው ሲል ይገልጣቸዋል፤ ይህም የመጻህፍቱን ታላቅ የሆነውን ኃይል ያመለክታል፡፡ ታላቅ ኃይሉን የሚያጸኑልንን በርካታ ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ የክርስቶስን ወንጌል በተመለከተ “የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና”። /ለማዳን የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል/ (ሮሜ 1፡ 16)፡፡ ይለዋል፣ ጨምሮም “የመስቀሉ ቃል ….የእግዚአብሔር ኃይል ነው” (1ቆሮ 1፡18) ይላል፡፡ እንደገናም ጳውሎስ “የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው” (2ቆሮ 10፡ 4) ይላል፡፡ ከእነዚህ የጦር ዕቃዎች መካከል አንዱ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው የመንፈስ ሰይፍ ነው (ኤፌ 6፡ 17)፡፡ በእርግጥም በዕብራውያን 4፡ 12 “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” የሚለውን ማለፍ አይቻለንም፡፡
የተነገረው ቃል እና የተጻፈው ቃል አንድ ናቸው፡፡ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ከተነገረው የእግዚአብሔር ቃል በኃይል የሚያንስ አይደለም፡፡ በዘፍጥረት 1 ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ “እግዚአብሔርም … አለ” የሚል እናነባለን፤ እግዚአብሔርም በተናገረ ጊዜ አንድ ነገር ይሆን ነበር፤

“ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” (ዕብ 11፡ 3)

ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና” (2ጴጥ 3፡ 5)

በእግዚአብሔር ቃል ችሎታ መታመን ያስፈልገናል፣ ምክንያቱም በሰው ልብና ሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን የስነምግባር እና የመንፈሳዊነት ለውጥ ለማከናወን ብቻውን ኃይል አለው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚከተሉትን ነገሮች ለማከናወን ኃይል አለው፡-

·         ይመልሳል /ነፍስን/ “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል” (መዝ 19፡ 7)
·         መንፈሳዊ ትንሳኤን ይሰጣል “ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና” (መዝ 119፡ 50)
·         ብርሃንን ይሰጣል “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ 119፡ 105)
·         ማስተዋልን ይሰጣል “የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል” (መዝ 119፡ 130)
·         ነጻ ያወጣል “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” አላቸው። (ዮሐ 8፡ 32)
·         ያነጻል “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” (ዮሐ 15፡ 3)
·         ይቀድሳል “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” (ዮሐ 17፡ 17)
·         ያስረዳል “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና” (ሐዋ 18፡ 28)
·         ያድናል “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና” (ሮሜ 1፡ 16)
·         እምነትን ያፈራል “ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና” (ሮሜ 1፡ 17)
·         ያስታርቃል “….በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። ….ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን” (2ቆሮ 5፡ 19-20)
·         ይወልዳል “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” (ያዕ 1፡ 18)

ጳውሎስ ታዋቂ በሆነው የሮሜ መጽሐፉ ምዕራፍ 1 ቁጥር 16-17 እንዲህ ብሎ ጽፎአል “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና” ይህ ምንባብ ስለወንጌሉ የሚከተለውን ይላል፡-
·         ኃይል ነው፣
·         የተለየና የታወቀ ኃይል፣
·         መለኮታዊ ኀይል፡- የእግዚአብሔር፣
·         ነፍስን የሚያድን ኃይል፡- ለማዳን፣
·         ሉል አቀፍ ኃይል፡-  ለ….ሁሉ፣
·         ሁኔታዊ ኀይል፡- ለሚያምኑ ሁሉ፣
·         ገላጭ ኃይል፡- በእርሱ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጦአል፡፡

ሠ) የእግዚአብሔር ቃል ነፍስን የሚያድን ነው
ጢሞቴዎስ የሚያውቃቸው ቅዱሳት መጻሕፍት “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉ” እንደሆነ ጳውሎስ ይናገራል፡፡ ይህም በተለይ ለሰዎች ልጆች ደህንነትን የሚያመጣ ኃይል መሆኑን ያመለክታል፡፡ ቆርነሌዎስ እርሱና ቤተሰቡ ሊድኑ የሚችሉበትን ቃሎች እንዲነግረው ጴጥሮስን መጥራት ነበረበት (ሐዋ 11፡ 13-14)፡፡ ያዕቆብም ቃሉ ነፍሳችንን ማዳን ይችላል ይለናል (ያዕ 1፡ 21)፡፡ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ
“ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ” (1ቆሮ 15፡ 1-2) ይላል፡፡ በሮሜ 1፡ 16 እንደተጠቀሰው የክርስቶስ ወንጌል የሚያምነውን ሁሉ ለማዳን የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡
በንባብ ክፍላችን “መዳን የሚገኝበትን” የሚለው ሃረግ በግሪኩ አገባብ ቀጣይ የሆነ የድነት ስራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በማዳን ስራው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ዳዊት እንዳለው “አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” (መዝ 119፡ 11) ነው፡፡ ኢየሱም ቢሆን በሰይጣን በራሱ ለቀረበለት የኃጢያት ፈተና ታልፎ እንዳይሰጥ ምን ያህል የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃሎች እንደተጠቀመ አስተውሉ (ማቴ 4፡ 1-11)፡፡ ዮሐንስ ሲናገር የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከመሆኑ አስቀድሞ በነበረው ኃጢአተኛ የአሮጌው ሰው ሕይወት ልማዶች እና ልምምዶች እንዳይቀጥል የእግዚእብሔር ቃል (ዘሩ) በእርሱ ይኖርበታል ይላል (1ዮሐ 3፡ 9)፡፡ አንዲት እናት ልጅዋ ቤት ለቆ ሲወጣ በስጦታ ባበረከተችለት መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጽ ላይ እንዲህ ብላ ጽፋ ነበር፡- 'ይህች ታናሽ መጽሐፍ ከኃጢአት ትጠብቅሃለች፣ ነገር ግን ደግሞ ከዚህች ታናሽ መጽሐፍ አርቆ የሚጠብቅህ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ኃጢአት ብቻ ነው'፡፡
እንግዲህ ነፍስን የሚያድነው ብቸኛ የእግዚአብሔር ኃይል የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ፣ በሚከተለው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ለመለወጣችን ወይም እንደ ክርስቲያ ለመኖር እንዲቻለን ባለው ሂደት ውስጥ ከቃሉ ተነጥሎ ያለ “ቀጥተኛ የመንፈስ ቅዱስ አሰራር” አያስፈልገንም፤ ሁለተኛም ወንጌሉን መስበክ አለብን!
አንድ የጥንት እንግልዝኛ መዝሙር እንዲህ ይላል፡- 'ኃጢአት ሲቀጥል፣ ጸጋው መቀጠል አለበት፣ ወንጌሉ ለሁሉ ነው!'
ስብሃት ለአምላክ ደግሞ፡-
ዘምር ዘምር ወንጌሉን ከሁሉ ያ ሃብይ ይደምቃል
ተካፈል በእልልታ አሁንያን ድንቅ የወንጌሉን ቃል

ረ) የእግዚአብሔር ቃል ተጻፈ ነው
ጢሞቴዎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደሚያውቅ ጳውሎስ ይናገራል፡፡  ቅዱሳት መጻሕፍት የሚለው ሃረግ የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ቃል በጽሑፍ መልክ የቀረበ፣ ጽሑፍ ሆኖ የተሰጠ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ጳውሎስ እኛ ልናነበውና ልንረዳው እንድንችል ጻፍሁ ይላል፡፡
ቀደም ሲል እንዳነሳነው የእግዚአብሔር ቃል በጽሑፍ የቀረበ ከመሆኑ የተነሳ ይህ ማለት የእግዚአብሔር ቃል በተነገረበት ጊዜ ከነበረው ኃይል ያነሰ ኃይል አለው ማለት አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ የተጻፈውን ቃል ይጠቀምበት እንደነበረው ሁኔታ ካየነው፣ የሰይጣንን ፈተናዎች እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መትቶ በመለሰ ጊዜ በእርግጥም በቃሉ ኃይል ያምን እንደነበር ማረጋገጥ ይቻላል (ማቴ 4፡ 1-11)
የእግዚአብሔር ቃል በጽሑፍ የተሰጠ የመሆኑ ጉዳይ በእውነትም አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ይኸውም የሚያመለክተው መጽሐፉ የሚነበብ እና የሚጠና መጽሐፍ መሆኑን ነው፡፡ አለበለዚያ በዚህ መልኩ መቅረቡ ለምን አስፈለገ?
በነዚህ የተቀደሱ ገጾች በተደጋጋሚ የምንመከረው አዘውትረን እንድናነበው ነው (ቆላ 4፡ 16፤ 1ተሰ 5፡ 27፤ ራዕ 1፡ 3 እና ነህ 8፡ 3 ጀምሮ)፡፡ ኢየሱስ በአንድ ወቅት  “….የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ”(ማቴ 21፡ 42) ሲል ከጠየቀው ያነሰ ነገር ከእኛ አይጠብቅብንም፡፡

ሰ) የእግዚአብሔር ቃል መንፈስ ያለበት በመንፈስ የተሰጠ ነው፡፡
ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን” በመንፈስ የተሰጠውን መጽሐፍ ታውቃለህ ይለዋል፣ ይኸውም እያንዳንዱ ቃል በቃል በጸሐፊዎቹ የቀረበው በመንፈስ መሆኑን ያመለክታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ የተነገረ በቃል የተሰጠ ነው፡፡ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ተስፋ በዚሁ መልኩ በመንፈስ እየተነዱ እንደሚናገሩ ነው፡-
“አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና”  (ማቴ 10፡ 19-20)
በመንፈስ መነዳት ብቻ ሳይሆን ያ በመንፈስ በመነዳት የተነገረው ቃል ከቶ እንደማያልፍና እንደማይጠፋ ተናግሮአል (ማቴ 5፡ 18)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ በመነዳት የተሰጠ መጽሐፍ ካልሆነ እንግዲያውስ ጽፈው ያስተላለፉልን ሰዎች አንዳንዴ በቅጡ እንክዋን ያልተረዱትን ነገረ ጻፉ ብለን እንቆጥራለን (ምሳሌ፣ 1ጴጥ 1፡ 9-11)፡፡
መነዳት የተሰኘው ቃል እስትንፋስ ማለት ነው፣ ይኸውም ለመናገር አስፈላጊ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ነው፤ ስለዚህ ይህ ማለት እግዚአብሔር ተናግሮአል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ መላው መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እሰትንፋስ የተሰጠ እንደሆነ አረጋግጦአል፡፡ በሉቃስ 24፡ 44 ላይ፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው” ሲል ብሉይ ኪዳንን በመንፈስ በመነዳት የተሰጠ እንደሆነ አጽንቶአል፡፡ አዲሱ ኪዳንም ገና ከመጻፉና ተጽፎ ከመጠናቀቁ በፊትም ቢሆን በመንፈስ የተሰጠ እንደሆነ በዮሐንስ 16፡ 13 ላይ፡- “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋ”  ሲል ያጸናዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መነዳትን ለራሱ ያጸናዋል፡፡ ከ2000 ጊዜ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን የመልዕክታቸውን የመጀመሪያ መገኛ ሲናገሩ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ይላሉ፤ እንዲህ ያሉ በነቢያት ዘንድ ብቻ የሚገኙ ሌሎች ሃረጎችም ለ1300 ጊዜ ተገልጸዋል፡፡ ስለዚህ በንባብ ክፍላችን እንደሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ በመነዳት የተሰጠ ነው፡፡
ቃል በቃል የሆነው እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በመንፈስ የተገለጠ የእግዚአብሔር ፈቃድ እስከሆነ ድረስ እኛም፡-
·         ምንም ያህል ሞኝ የሆንን ያህል ቢያስመስለንም በውስጡ ያለውን ማንኛውንም ትዕዛዝ መታዘዝ አለብን፤
·         ምንም ያህል የማይቻል ቢመስለንም በውስጡ ያለውን ማንኛውንም ተስፋ መታመን አለብን፤
·         ምንም ያህል ጥበብ የሌላቸውና ያልተማሩ ሰዎች ቢያስመስለንም  በውስጡ ያለውን እያንዳንዱን አስፈሪ ነገር መፍራት አለብን፤
·         ምንም ያህል የማይታመኑና እና ይማይቻሉ ቢመስሉም በውሰጡ ያለውን እያንዳንዱን ቃል ማመን አለብን፡፡

ሸ) የእግዚአብሔር ቃል ውጤታማ ነው 
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲናገር ለትምህርት፣ ለተግሳጽ፣ ልብን ለማቅናት፣ በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅመውን ቅዱሳት መጻሕፍት ታውቃለህ ይለዋል፡፡ በኤርምያስ ዘመን “ነብያቱ በበዓል ትንቢት ተናገሩ፣ የማይረባንም ነገር ተከተሉ” (ኤር 2፡ 8) ይላል፡፡ አንደ ሰው የእግዚአብሔርን ምክር ተከትሎ ሲሄድ እንዴት ልዩ ይሆን!
·         በሁሉ ረገድ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያስተምር፣ የእግዚአብሔር ቃል ለትምህርት ይጠቅማል (1ጴጥ 1፡ 3)፡፡
·         ሰው ሰራሽ የሆኑትን እና ሃሳብ ወለድ የሆኑትን የሃሰት አስተምህሮዎች ሁሉ የሚያርም ስለሆነ፣ የእግዚአብሔር ቃል ለተግሳጽ ይጠቅማል፡፡
·         የትኛውንም ጠማማ የሆነ የሰውን ጎዳና ቀጥ አድርጎ ስለሚያስተካክል የእግዚአብሔር ቃል ልብን ለማቅናት /ለእርማት/ ይጠቅማል፡፡
·         በየትኛውም እና በሁሉም ትክክለኛና አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛውንና ግልጹን ነገር ስለሚያስተምር የእግዚአብሔር ቃል በጽድቅ ላለው ምክር ይጠቅማል፡፡

ቀ) የእግዚአብሔር ቃል በቂ ነው
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲናገር ቅዱሳት መጻሕፍት የተሰጡት“የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ” ነው ይላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በቂነት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው ዋና ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር መንፈስ ቅዱስ ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራቸው (ዮሐ 14፡ 26) እንዲሁም ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራቸው (ዮሐ 16፡ 13) ነው፡፡ ይሁዳም ሲናገር “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት” (ቁጥር 3) ይናገራል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል በራሱ ካለው ብቃት የተነሳ ሌላ ተጨማሪ ነገር፣ የተባዛ፣ የተቀነሰ፣ ወይም የተሻሻለ ነገር ጨምሮ መፈለግ በጽኑ የተከለከለ ነው (ራዕ 22፡ 18-19)፡፡ በዚሁ መሰረት ልንጠባበቃቸው የሚያስፈልጉ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፡- የአግዚአብሔር ቃል ሙሉ እና በቂ እስከሆነ ድረሰ፣ የመጨረሻ የሆነ እና በቃት ያለው ለሁሉም የሚበቃ እስከሆነ ድረስሽ፡-
·         ምንም አይነት ስሜታዊ የሆነ የግል ልምምድ
·         ምንም አይነት እላፊ መገለጥ
·         ምንም አይነት ተዓምራታዊ ድርጊቶች
·         ምንም እይነት በሰው ላይ የሚካሄድ “የመንፈስ ቅዱስ አሰራር” ልንፈልግ አይገባንም፡፡
በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ ጽኑ እና የማይነቃነቅ የሆነ እምነት በአሁኑ ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ እና ከቤተክርስቲያን ውጭ ካሉ በርካታ የተሳሳቱ ትምህርቶች ብዙዎችን ይጠብቃል፡፡

በ) የእግዚአብሔር ቃል መሰበክ አለበት
ጳወሎስ ለጢሞቴዎስ ሊሰበክ የሚገባውን ቅዱሳት መጻሕፍት ታውቃህ ይለዋል “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” (2ኛ ጢሞ 4፡ 1-2) በስብከት ስራ ውስጥ መካተት የሚገባቸው ሶስት ጉዳዮች አሉ፡-
1.      ዘዴ አለ ይኸውም ስብከት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ሰባኪ ነበር (ማቴ 4፡ 17)፣ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ በሁሉ ስፍራ የተገለጠውና የታወቀው በዚህ ታላቅ ዘዴ ነው (ቲቶ 1፡ 3)፣ ሰዎች ወደክርስቶስ ይሳቡና ይመጡ ነበር (ዮሐ 6፡ 44-45)፣ እምነትም በሰዎች ልብ ውስጥ ይፈጠር ነበር (ሮሜ 10፡ 13-17)፣ ነፍሳትም ይድኑ ነበር (1ቆሮ 1፡ 21)፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ” (1ቆሮ 9፡ 16) ማለቱ ለምን እንደሆነ እዚህ ላይ ማየት ይቻለናል፡፡
2.     መልዕክቱ አለ፣ ይኸውም ቃሉ ነው፡፡ አዎ ቃሉና ቃሉ ብቻ የሰባኪ የሚያውጀው መልዕክቱ ሊሆን ይገባዋል (1ቆሮ 1፡ 21)፡፡ ዓለም በአሁኑ ሰዓት ሊሰማው የሚያስፈልገው ንጹሁን፣ ግልጹን፣ ውብ የሆነውን፣ እና ያልገለሞተውን የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ነው፡፡
3.     ተግባሩ አለ፣ ይኸውም ማስረዳት፣ መውቀስ፣ መገሰጽ እና መምከር ነው፡፡ በውጭ ያሉ ኃጢአተኞችን ማስረዳት፣ ከእነርሱ የተሻለ አውቀው ነገር ግን ኃጢአትን በማድረግ የሚቀጥሉትን መውቀስ እና መገሰጽ፣ ልባቸው የወደቀባቸውን እና ተስፋ የቆረጡትን ደግሞ መምከር ወይም ማበረታታት አለብን፡፡
ለዚህ ውጥንቅጡ ለወጣ ዓለምና ዘመን ቃሉን ወይም መልዕክቱን ለማድረስ ስንሰብክና ስናውጅ እነዚህን በርካታ መንገዶች መጠቀም አለብን፡፡ የሐዋርያውን አባታዊ ልመናና ማሳሰቢያ የተመለከትን እንደሆን ጢሞቴዎስ ስራዬ ብሎ ቃሉን እንዲሰብከው ጳውሎስ ለልመናው ያቀረባቸው እሴቶች እና ምስክሮች እንዴት ከፍ ያሉ ናቸው! “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ” ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በሚወደውና በሚያመልከው በእግዚአብሔር፣ ተስፋው በሆነው እና በሁሉ ሊፈርድ ባለው እርሱም በሚጠባበቀው በመምጣቱ፣ ሁሉንም በምትገዛው በመንግስቱ እያማለና እየገዘተ ቃሉን እንዲሰብክ ይመክረዋል፡፡ ሰው በሚወደው ይለመናል፣ ዛሬሰ እኛ ሰባኪያን ከፌዝ ርቀን ቃሉን ብቻ ለመስበክ በምንወደው በማን ወይስ በምን ብንለመን ይቀለን ይሆን?   
ይህንን የንባብ ክፍል ስናጠቃልል፣ ጳውሎስ እጅግ በተዋበና እጥር ምጥን ባለ ሆኖም ጠቅለል ባለ መልኩ የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ፣ ለታወቅ የሚችል፣ ቅዱሰ፣ በጽሑፍ የቀረበ፣ ኃይለኛ፣ ነፍስን የሚያድን፣ በመንፈስ በመነዳት የተሰጠ፣ ውጤታማ፣ በቂ እና ሊሰበክ የሚገባው መሆኑን ሲያጸናልን ተመልክተናል፡፡ ይህም ምንባብ ቅዱሱ መጽሐፍ አስደናቂ የሆነውን የራሱን ባህርይ አስመልክቶ ከያዛቸውና ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ ምስክርነቶቹ አንዱና ዋናው ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሔርን ቃል ከዚህ በፊት ከነበረን በላይ ልንወደውና ልናከብረው፣ ልናነበውና ልናጠናው፣ ልናሰላስለውና ልንታዘዘው፣ ልንኖረውና ልናስተምረው፣ ልንኖርለትና ልንሞትለት ይገባናል፡፡
2)   በክርስትናው ዓለም ያሉ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች ስለ እግዚእብሔር ቃል ምን ይላሉ?

1.    ካቶሊኮች፡- ስለ ትምህርታቸው ማረጋገጫ ከእግዚአብሔረ ቃል ብቻ አይወስዱም፡፡ ቃሉን ከባህል እና ከልማድ ጋር በእኩል ደረጃ እያዩ ባህልና ልማድ ኃይማኖታዊ ስሜትና ክብር ማግኘት አለባቸው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት ቃልና የጳጳሱ ትዕዛዝ ከመጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ስልጣን አለው፣ ቤተ ክርስቲያንም ትርጉሙን ካልሰጠች በቀር ማንኛውም አባል ቃሉ ሊገባው አይችልም ይላሉ፡፡

2.   ኦርቶዶክሶች፡- የእግዚአብሔር ቃል ለመሰረተ እምነት የመጨረሻውና ሙሉ የሆነ ምንጭ ተደርጎ አይቆጠርም፡፡ የተቀደሱ ልማዶች በተጨማሪ መሰረተ እምነቱን መወሰን አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔርንም ቃል ሆነ በውስጡ ያሉ መለኮታዊ እውነቶችን በትክክል የምትተረጉመው ቤተ ክርስቲያንና ቅዱስ ሲኖዶሱ (አጠቃላይ ጉባዔዋ) ብቻ ናቸው፡፡


3.   ሊብራሎች (የለዘብተኛ ስነ መለኮት አራማጆች)፡- መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል አካቶ የያዘ ነው እንጂ ራሱ እንዳለ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ስህተት የሆኑ ነገሮች አሉበት፣ እንደ ማንኛውም መጽሐፍ በብዙ እየተተቸ ሊጠና ይገባዋል፣ የያዛቸውም እውነቶች ምሳሌዎች ብቻ እንጂ በቀጥታ እንዳለ ወይም እንደ ተጻፈ መወሰድ የለባቸውም ይላሉ፡፡


4.   የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት (ለምሳሌ ካልቪንስቶች፣ ፒዩሪታንስ፣ ኩዌከሮች፣ ጴንጤ ቆስጤዎች፣ መጥምቃውያን፣ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ወዘተ)፡- የእግዚአብሔር ቃል ለመሰረተ እምነትና  ለሕይወት የመጨረሻ ባለ ስልጣን ነው ይሉና ቃሉን እና መንፈሱን ለየብቻ ነጥሎ የማየት ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ ከዚህ ምልከታቸው የተነሳ በትምህርታቸው ውጫዊ መረዳትና ውስጣዊ ምሪት የሚሉት ነገር አላቸው፡፡

5.   ሉተራን፡- የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ለእምነትና ለሕይወት ብቸኛ የበላይ ስልጣን ነው፡፡ መጽሐፉ በወንጌሉ ሰዎቸን ወደ እምነት የሚጠራ የክርስቶስ መጽሐፍ ስለሆነ ቃሉና መንፈሱ ፈጽሞ አይነጣጠሉም፡፡ ቃሉ ግልጽ ነው፣ የታዘዘውንም ይፈጽማል፡፡


6.   ሞርሞኖች፣ የይሆዋ ምስክሮች (የመጠበቂያ ግንብ አማኞች)፡- የሞርሞን መጽሐፍ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ   ከመጽሐፍ ቅዱሰ ጋር እኩል የሆነ ስልጣን እንዳልው ሲቆጠር፣ የይሆዋ ምስክር ተብዬዎቹ ደግሞ አንድ ሰው ድርጅታቸው የሚያወጣውን ጽሑፍ ማንበብ ትቶ ያለ ማቁዋረጥ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ቢያነብና ቢያጠና ከሃዲ ይሆናል ይላሉ፡፡ እነርሱም የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ለመቀየር መብት ያላቸው ይመስላቸዋል (ለምሳሌ በዮሐ 1፡ 1 የተጻፈውንና ቃልም እግዚአብሔር ነበረ የሚለውን ለክህደታቸው እንዲመች ቃልም god ነበረ ሲሉ ትንሽ አይፈሩም)፡፡
ለማጠቃለል፡- አንዳንዶች ከእግዚአብሔር ቃል ከመጽሐፍ ቅዱሰ የበለጠ የሚያዩት በላጭ አላቸው፣ ሌሎችም ተጨማሪ አላቸው፣ የተቀሩትም አሳንሰው ያዩታል፣ ከፊሎቹም ቃሉን ከመንፈሱ ነጥለው ሁለተኛ ልምመድ ይናፍቃሉ፣ ሌሎችም ለቃሉ እኩያ ያበጃሉ፣ አንዳንዶችም ቃሉን ይለውጣሉ፤ እኛ ግን ቃሉን ብቻ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገን እንይዛለን፡፡

3)   የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ ነው /የእግዚአብሔር መገለጥ/
እግዚአብሔር አምላክ የመገለጥ አምላክ ነው፡፡ ለፍጥረቱ ራሱን የገለጠባቸው መንገዶች አጠቃላይ መገለጥ እና ልዩ መገለጥ ተብለው በሚጠሩ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎቸ ይመደባሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ሊያሳዩ ከሚችሉ ክፍሎች መካከል መዝሙር 19 በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህም መዝሙር የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጽ ሲሆን እርሱም በግዑዙ ዓለምና ለእስራኤል በተሰጠው አምላካዊ ሕግ አማካይነት ስለሆነው መገለጥ ይናገራል፡፡
1.      ስለ አጠቃላይ መገለጥ ስናወራ እየተነጋገርን ያለንበት ርዕሰ ጉዳይ እግዚአብሔር በፍጥረቱ በኩል ራሱን እንደገለጠ ያለውን እውነታ ነው፡፡

ሰው በዙሪያው ያለውን የእግዚአብሔርን የእጁን ስራ ፍጥረትን አይቶ ሰሪውን ሊገነዘብ ይችል ይሆናል፣ ሆኖም ይህ እወቀት ፍጡር የሆነውን ሰው ከፈጣሪው ጋር ወዳለ ፍጹም ሕብረት አያስጠጋውም፡፡ ውድቀት / የሰው ኃጢአት የሰውን አስተሳሰብ በማጨለሙ ምክንያት ይህ መገለጥ ለሰው ፈጣሪ መኖሩን እርሱም አንድ ብቻ እንደሆነ ቢያሳውቀውም እንክዋን ይህ እውቀት ብቻውን ከእውነተኛው አምላክ ጋር አያገናኘውም፡፡ በዚህ ምክንያት ሌላ መገለጥ አስፈልጎአል፡፡

2.     ስለ ልዩ መገለጥ ስንነጋገር የምናተኩረው ነፍስን ሊመልስ ሰለሚቻለው የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር በፍጹምነት በልጁ በኩል ራሱን መግለጡን እየነገረን ወደ እምነት ይጠራናል፡፡ ልጁን አይተን እውነተኛውን አምላክ እና ሰማያዊውን አባት እናያለን እናውቃለንም፡፡ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ በትምህርቱና በስራው፣ በተቀበለው መከራ፣ በሞቱና በትንሳኤው በኩል ራሱን ገለጠ፡፡ ይህንን የኢየሱስን መገለጥ የምናየው በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባለው ፍጹም ብርሃን ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ወደር የሌለው የእውነተኛው አምላክ እውነተኛና ፍጹም መገለጥ ምንጭ ነው፡፡

ቀደም ሲል እንዳነሳነው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር የኖረው ቃሉ ንግግሩ ከጥንት ጀምሮ በነቢያቱ በሁዋላም በውድ ልጁ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ተጽፎ እናያለን “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (ዕብ 1፡ 1-2)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ነብያቱንና ሐዋርያቱን በመንፈስ ቅዱስ በሚሆን መነዳት እየተጠቀመባቸው የሰጠን በጽሑፍ የተቀመጠ የመገለጥ ክምችት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ቀኖና (Chritological Canon) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት በእምነት ብቻ ከክርስቶስ የተነሳ የሚገኝ የነጻ ወንጌል እና ጽድቅ የሚታደልበት ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ ስለ ብሉይ ኪዳን፡-ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም” (ሉቃ 16፡ 29ና 31)፣ ብሎአል፡፡  ለእምነት የሚያስፈልገን የተጻፈው ቃል እንጂ ትንግርት አይደለም፡፡

እነዚህም መጻሕፍት ስለክርስቶስ ይናገራሉ፡- “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም” (ዮሐ 5፡39-40) በተጨማሪም ሉቃስ 24፡ 44-45 ተመልከት፡፡

ኢየሱስ ስለ አዲስ ኪዳን፡-እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” (ማቴ 10፡ 40) ብሎአል፡፡ ይህም ማለት የሐዋርያቱን ትምህርትና መልዕክት የሚቀበል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ታላላቅ ክፍሎች ብሉይ እና ሐዲስ 66ቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ስህተት የሌለባቸው ፍጹማን እና ነጹሐን የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን አምነን እንመሰክራለን፡፡ ነብያቱ አስቀድመው በተናገሩትና ኢየሱስም በሕይወቱ፣ በኑሮው፣ በትምህርቱና በስራው፣ በሞቱና በትንሳኤው በገለጠውና ባጸናው መካከል ልዩነት የለም፡፡

ሐዋርያቱም በሰበኩትና በጻፉት፣ በኖሩለትና በሞቱለት ጉዳይ መካከል ልዩነት የለም ከእርሱም “የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት”። (1ዮሐ 1፡ 5)፤ “ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ” (1ቆሮ 14፡ 37)፡፡ በነቢያቱ የተነገረው፣ በኢየሱስ ሕይወት የጸናው፡ በሐዋርያቱ የተሰበከውና የተጻፈው እርሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የተጻፈውም ፡-
·         ለእምነት- ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል (ዮሐ 20፡ 31)
·         ለትምህርት፡- በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና (ሮሜ 15፡ 4)
·         ለተግሳጽ- ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ (1ቆሮ10፡ 11)፡፡

4)   የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን
ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ (Sola Scriptura) ይተሰኘው የ15ኛው ክፍለ ዘመን የቤተክርስቲያን አዳሾች የእምነት አቅዋም የቅዱሳት መጻሕፍትን ስልጣን የሚያጸና ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያለምንም ሰብዓዊና ፍጥረታዊ ድጋፍ በራሱ የቆመ፣ የልምምዶች ሁሉ ዳኛ እና ሚዛን መሆኑን፣ ሁሉም ነገሮች የሚጸኑትም ሆነ የሚወድቁት በእርሱ እየተመዘኑ፣ እየተለኩና እየተሰፈሩ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል /ቅዱሳት መጻሕፍት ይኸውም የብሉይ ኪዳን ነበያትና፣ የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ጽሑፎች/ የትኞቹም ትምህርቶች ሆኑ ሁላቸውም መምህራን የሚገመገሙበትና የሚመዘኑበት ብቸኛ ሚዛን ወይም መለኪያ እንደሆነ አጥብቀን እናምናለን፣ እናስተምራለን፣ እናስታውቃለንም፡፡
ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ሲገልጠው፡- 'በሁሉ ላይ መግዛት ያለባት፣ ሁሉም ሊያከብሩአትና ሊታዘዙዋት የሚገባ ንግስት ናት' ይላታል፡፡ ሉተር ስለስልጣን ሲያስተምር፡- 'ማንም የፈለገውን አይነት ሰው ቢሆን እና ምንም ዓይነት መጠሪያና ማዕረግ ቢኖረው እኔን አይገደኝም፣ ማንም ቢሆን የትኛውም ቤተክርስቲያን ወይም የትኛውም ኃይማኖታዊ ልማድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አለቃና ዳኛ ሊሆን ከቶውንም ቢሆን ሽራፊ ፈቃድ የለውም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነትም ሊያረጋግጥ የሚቻለው ባለስልጣን የለም፡፡ እርሱ ብቻውን የገዛ ራሱን ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ የሚችል ምትክ የማይገኝለት ስልጣን ነው፡፡ የሚወዱት እና የሚታዘዙት ተማሪዎቹ ግን የእርሱ ምስክሮቹ ብቻ ናቸው' ይላል፡፡ ይህ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ ይሚችል በስልጣን ላይ ያለ ማንም ሰው ወይም ድርጅታዊ ተቅዋም የለም ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ ራሱ ብቻውን የገዛ ራሱን ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በእምነት ጉዳዮች ስልጣን የሚያርፈው በሃይማኖት መግለጫዎች ላይ እና በቤተክርስቲያን ጉባዔዎች ላይ አልያም በከፍተኛ የስልጣን ተዋረድ በጳጳሱና በኤጲስ ቆጶሳቱ ላይ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት ወንጌል ላይ ብቻ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ስልጣን የሚወጣውም በወንጌሉ ውስጥ ካለው ይዘት ነው ሲል ሉተር ይሞግታል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በስብከት የሚተላለፍ በስልጣን የሚሰበክ የተስፋ መጽሐፍ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ጉዳይ በለ አደራ እንጂ ባለ ድርሻ የሆነ ማንም የለም፡፡
ቤተክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ትመሰክራለች፣ በታዛዥነት እውቅና ሰጥታው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ፈጣሪዋ መሆኑን ለራሱ እንደመሰከረ ታምናለች እንጂ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ቃል መሆን ያለመሆኑን ለአፍታም ተጠራጥራ አትጠይቅም፤ ያን ባደረገች ጊዜ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መሆንዋ ይቀራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጥረቱ የሆነችውን የቤተክርስቲያንን ትክክለኛነት ያረጋግጣል እንጂ ቤተክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ማስረጃና ማረጋገጫ የምታቀርብለት አይደለችም፡፡ ቤተክርስቲያን ወንጌሉን በባለአደራነት ስትሰብክ አምና ብቻ ነው እንጂ ገምታ ወይም መስሎአት አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ስልጣን አለው ስንል እያልን ያለነው ቢያንስ አራት ነገሮችን ነው፣ እነዚህም ከፍ ሲል ለመስረዳት በተሞከረው ዝርዝር ውስጥ በከፊል ያነሳናቸው ናቸው፣ እነርሱም፡-
1.      ይፈጥራል፣ ያጸናል፣ ለእምነት ብቸኛ መመሪያ ይሆናል ማለታችን ነው (ማቴ 24፡ 35፤ ሉቃ 4፡ 32-36፤ 24፡ 44፤ ዮሐ 10፡ 35፤ 12፡ 48፤ 1ቆሮ 1፡ 18፤ 14፡ 37፤ 1ተሰ 2፡ 13፤ 2ጢሞ 3፡ 16፤ 2ጴጥ 1፡ 23)፡፡
2.     ብቻውን በቂ ነው፣ ማለትም ለእምነት አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ያስተምራል (ዘዳ 4፡ 2፤ ኢያ 1፡ 7-8፤ መዝ 19፡ 7፤ ማቴ 5፡ 17፤ ማር 16፡ 20፤ ዮሐ 8፡ 12-20፣ 31፤ ሐዋ 20፡ 32፤ ሮሜ 1፡ 16-17፤ 10፡ 17፤ 1ቆሮ 1፡ 21፤ ኤፌ 1፡ 13፡ 1ጢሞ 6፡ 3-5፤ ራዕ 22፡ 18-19)፡፡
3.     ግልጽ ነው፣ ራሱን ይገልጻል፣ ለሰዎችም ያበራላቸዋል (መዝ 19፡ 7-8፤ 119፡ 105፣ 130፤ ማቴ 11፡ 25፤ ዮሐ 5፡ 39፤ ሐዋ 17፡ 11፤ 2ቆሮ 1፡ 19-20፤ 4፡ 3-6፤ 2ጢሞ 3፡ 15፤ 2ጴጥ 1፡ 19፤ 1ዮሐ 2፡ 12-13)፡፡
4.     አጥጋቢ ነው፣ ምንም ምንም ሳይጨመርበት ቃሉ ብቻውን ይበቃናል፡፡ ቃሉ ሕያው ነው፡፡ የታዘዘውን ይፈጽማል (ዘዳ 8፡ 3፤ ኢሳ 55፡ 10-11፤ ሰቆ 2፡ 17፤ ሉቃ 8፡ 11-15፤ ዮሐ 6፡ 63፤ ሐዋ 6፡ 7፤ 12፡ 24፤ 19፡ 20፤ ሮሜ 10፡ 17፤ 1ቆሮ 1፡ 21፤ 2፡ 4-5፤ 2ቆሮ 4፡ 6፤ ፊል 2፡16፤ 1ተሰ 2፡ 13፤ ያዕ 1፡ 21፤ 1ጴጥ 1፡ 23፤ 2፡ 2፤ 1ዮሐ 1፡ 1-2)፡፡
 ሲጠቃለል፡-  እምነትን እና ደህንነትን በተመለከተ እንደመጨረሻ መለኮታዊ ሰነድ ሊታመን እና ተቀባይነት ያለው ሊሆን ይሚገባው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ብቻ እንጂ ማንኛውም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊና መንፈሳዊ ልምምዶች ወይም ሰነዶችና ትውፊቶች አይደሉም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚባለው የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ያረፈበት ዋናው ምሰሶ እርሱ ብቻ ስለሆነ ማንኛውም ትምህርት፣ መልካም ይሁን ክፉ፣ ትክክል ይሁን ስህተት የሚታወቅበትና የሚመዘንበት ብቸኛ ዳኛ፣ ገዢ ህግና መመሪያ ደንብ፣ የማይለወጥ ቀኖና ሆኖ ይኖራል፡፡ በሰው ፈቃድ አልመጣም፣ አይሻሻልም፣ አይለወጥም፣ መተኪያ የለውም፣ ማንምም ለገዛ ራሱ ሊተረጉመው አልተፈቀደም፡፡ 
   II.      የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊ መልዕክት
ጳውሎስ በቆላስይስ 1፡ 26 እና 28 ስለ እግዚአብሔር ቃል ምስጢር መገለጥ ሲናገር “ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል…. እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው” ይላል፡፡ መገሰጽ እና ማስተማር የእግዚአብሔር ቃል በሰው ሕይወት ውስጥ የሚፈጽመው ተግባር ነው፡፡ ተግሳጽ የተሰኘው ቃል የእግዚአብሔር ቃል አንዱ ይዘት የሆነውን የሕጉን ተግባር ያመለክታል፡፡ አማኝ በሚሰናከልበት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሕጉ በኩል አድርጎ እየገሰጸው ደግሞም በወንጌሉ በኩል እያደሰው ፍጹም ሰው ሊያደርገው መጽናናትን ይሰጠዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ተስፋን ይሰጣል፡፡ ቀደም ሲል ለማብራራት እንደተሞከረው መጽሐፉ የተጻፈልን ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት ነው እንጂ ለተጭበረበረ ዋስትናና ንስሃ ላለመግባት መሰረት ሆኖ እንዲያገለግለን አይደለም፡፡ እኛን ሊገስጸን ለትምህርታችን የተጻፈው ቃል ብቻ ፍጹማን ያደርገናል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል ማዕከላዊ መልዕክት የምንረዳው በይዘቱ ተካተው ከሚታወቁት ሕግና ወንጌል ከተሰኙት ሁለቱ ዋና ዋና ክፍሎቹ ነው፡፡ ይህ ታላቅ መጽሐፍ ባንዳንድ ስፍራ ሕግን ሲያመለክት በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ ስለ ክርስቶስ ያለውን ተስፋ ይሰጣል፡፡ ይኸውም ተስፋ ክርስቶሰ ወደ ዓለም በመምጣቱ ከእርሱ የተነሳ የኃጢአት ስርየት፣ ጽድቅና የዘላለም ሕይወትለሚያምኑ ሁሉ ይሰጣል ብሎ ተስፋ መስጠቱ ወይም በራሱ በወንጌል ውስጥ እንደምናገኘው ክርስቶስ በስጋ ከተገለጠ በኁዋላ በእምነት አማካኝነት የኃጢአት ስርየት፣ የጽድቅና የዘላለም ሕይወት ተስፋን ያደለበት ነው፡፡ ሕግና ወንጌል ስንል መግደልና ሕያው ማድረግ ማለታችን ነው፡፡ “በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል” (ሆሴ 6፡ 5)፤ “ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ” (መዝ 119፡ 25) የእግዚአብሔር ሕግ ኃጢአትን፣ ኃጢአተኝነትንና በኃጢአተኛውና በኃጢአቱ ላይ ከመሆን የማይቀረውን የጻድቁን አምላክ ጽኑ ፍርድ እያመለከተ ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ያሸብራል፡፡ እርሱም ያሸበራቸውን ሁሉ ወንጌሉ በእምነት በኩል በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ እያጸደቀ ሕያው ያደርጋቸዋል፡፡ ማሸበር እና ማጽናናት፣ መግደል እና ሕያው ማድረግ፣ መኮነን እና ማጽደቅ፣ እነዚህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ስራዎች በሕግና በወንጌል የተገለጹት ናቸው፡፡ ሕጉም ኃጢአትን የሚያወግዘውና የሚኮንነው ሲሆን፣ ወንጌሉ ደግሞ በክርስቶስ ለኃጢአተየኛው የተሰጠ የጸጋ ጽድቅ ተስፋ ነው፡፡
1)    ይህንን ጉዳይ የተሻለ ለመረዳት የእግዚአብሔር ሕግና የእግዚአብሔር ወንጌል የተሰኙትን ሁለቱንም በንጽጽር መመልከት ጠቀሜታ አለው፡፡ የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች እንመልዕከት፡-

1.    ሕጉና ወንጌሉ የተሰጡበት መንገድ፡-
Ø  እግዚአብሔር ሕጉን በፍጥረት ጊዜ በሰው ልብ ጽፎታል፡፡ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ”  (ሮሜ 2፡ 14-15) ስለዚህ፡-
-   የሰው ሕሊና ሕግን ያውቃል (ሮሜ 2፡ 15)
-   እጅግ የከፋው ኃጢአተኛ እንክዋን ሕጉ የሚያዘውን ማድረግ እንዳለበት ማየት ይችላል

Ø  ወንጌሉ በሰው ልብ የተጻፈው በፍጥረት ጊዜ አይደለም፡፡
-   1ቆሮ 2፡ 6-14
·         ወንጌል ከሰዎች ተሰውሮ የነበረ ነው፣ አንድ ሰው እንክዋን አያውቀውም ነበር፡፡
·         ወንጌል አዲስ ከመሆኑ የተነሳ የሰው ህሊና በወንጌሉ ይገረማል (ሉቃ 4፡ 14-30፤ ዮሐ 6፡ 41፣ 51- 52፣ 60፣ 66) ወንጌል ለሰው surprise ነው፡፡
·         ሰው ወንጌልን ሊማር የሚችለው ካነበበው ወይም የተሰበከለት እንደሆን ብቻ ነው (ማቴ 28፡ 18-20፤ ሉቃ 9፡ 2፤ ሮሜ 10፡ 14-15፤ 16፡ 25-26)፡፡

-   ሁሉም ሰው በተፈጥሮ ስለ ሕግ የሚያውቀው አንድ ነገር ያለ የመሆኑን ያህል፣ ወንጌልን መማር የሚቻለው ግን ከእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡

2.   ሕጉና ወንጌሉ የሚያስተምሩት፡-
Ø  ሕጉ ማድረግ ያለብን እና የሌለብን ነገር ምን እንደሆነ ያስተምረናል (ዘጸ 20፡ 1-17፤ ዘዳ 27፡ 10 “ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ”)፣ ከዚህ የተነሳ ሕጉ፡-
-   በስራዎች ላይ ያተኩራል (ዘዳ 6፡5-8፤ ማር 12 30-31፤ ያዕ 2፡ 10 “ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል”)
-   ይኮንናል፣ ይገድለንማል እንጂ ጨርሶ ይቅር አይልም፡፡
-   ሰው የሚሰራውን እያመለከተ፣ ምን እንዴት ማድረግ እንዳለብን ይኸውም በቅድስና ፈጽሞ ያለ ኃጢአት መደረግ እንዳለበት ያስጠነቅቃል እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። (ዘሌ 19፡ 2)

Ø  ወንጌሉ እግዚአብሔር ለእኛና ስለእኛ በክርስቶስ ያደረገልንን ይሚያሳይን ነው (ማቴ 26፡ 26-28፤ ሮሜ 4፡ 8 “ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው”፤ 6፡ 3-7፤ 2ቆሮ 5፡ 19-21)፣ ከዚህ የተነሳ ወንጌል፡-
-   በእግዚአብሔር ስራ ላይ ያተኩራል (ሮሜ 3፡ 22-26፤ 5፡ 6-9፤ 8፡ 32)፣
-   የእግዚአብሔርን ጸጋ (ሐዋ 20፡ 24) እና ደህንነትን (ኤፌ 1፡ 13) በነጻ እንዲያው ያቀርባል እንጂ ምንም አይጠይቅም፤
·         ወንጌል ምንም እንድናመጣ አይጠይቀንም፣
·          ወንጌል ሰጪ ብቻ ነው፡፡
·         ወንጌል የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው፣
Ø  ለስጦታ ምንም ክፍያ አትጠየቅም
Ø  ለራስህ ደግሞ ምንም ስጦታ ልትሰጥ አትችልም (ኤፌ 2፡ 8-9)
-   ይቅር ይላል፣ ይቤዣል፣ ያጸድቃል፣ ያድናልም፣ ሰላምንና የዘላለምን ሕይወት ይሰጣል (ሮሜ 3፡ 24፣ 28 “በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ…..ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና” ፤ 5፡ 1 “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ”፤ ቆላ 1፡ 13-4፣21- 22፤ ዮሐ 10፡ 27-28፤ ዮሐ 5፡ 11)
-   ወንጌል እግዚአብሔር የሚሰራውን ይገልጣል፣ ይኸውም ስራ፡-
·         ኃጢአታችንን ይቅር ማለቱ
·         እኛንቅዱሳን አድርጎ መቀበሉን ሲሆን፣ ይህም በወንጌል ማለትም ለደሕንነታችን በሆነውና በኢየሱሰ ክርስቶስ በተሰበከው የምስራቹ ቃል የፈጸመው ነው፣ (ሮሜ 1 ፡ 16)
Ø  ወንጌል ይእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን ልብ አንበል፣ ወንጌል የእግዚአብሔርን ኃይል የሚገልጥና እርሱ በክርስቶስ ያደረገውን የሚናገር ደግሞም ይህንን ሁሉ ያደረገውና የፈጸመው ራሱ ወንጌል መሆኑን እናስተውል፡፡

-   ሁሉም ኃይማኖቶች የእግዚአብሔር የመጀመሪያ መልዕክት የሆነውን ሕጉን በተመለከተ የሚያስተምሩት ነገር ያላቸው ሲሆን በበለጠ ግን ግልጽ የሆነ የሕጉ ትምህርት ሊኖረን የሚችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከዚህ የሚልቀው እጅግ የተሻለው መገለጥ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው የወንጌል መልዕክት የሚገኝ ሲሆን ይኸውም ልዩ መገለጥ የሚባለው ነው፡፡

3.   ሕጉና ወንጌሉ የያዙት ተስፋ፡-
Ø  ሕጉ ሕይወትን እና ደህንነትን ተስፋ ሊገባልን ይችላል (ዘሌ 18፡ 5 “የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ”፤ ሉቃ 10፡ 25-28)፣ ነገር ግን፡-
·         ሕግ ጽድቅን ለማግኘት ሲባል ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ሰዎች ምንም ሳናጉዋድል መልካም ስራን እንድናመጣ ግድ ይለናል፡፡ ይኸውም የጽድቅ ስራ የሕጉ ጽድቅ የሚባለው ነው፡፡ በሕጉ በኩል የሆነው ይህ የጽድቅና የደህንነት ተስፋ ሊረጋገጥ የሚችለው ሕጉን ፈጽመን የምናምዋላና ይምንታዘዝ ከሆነ ብቻ ነው (ገላ 3፡ 12 “ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል”፤ ያዕ 2፡ 10)፡፡
·         ሕጉ ጻድቅ የሆነውን ሰው ብቻ ጻድቅ ብሎ ያውጃል (ሮሜ 2፡ 13 “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና”)፡፡ ሕግ እግዚአብሔር ከሰው የሚጠብቀውንና ሰው ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን የሚገልጥ በእኛም በኩል መቀደሳችንን የሚጠይቅ፣ የእግዚአብሔርን ቁጣና የኃጢአትን ቅጣት ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን የሚከሰንና የሚኮንነን ጭምር ነው፡፡ ሕግ ሁልጊዜ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል እያለ ይከሰናል፡፡

Ø  ወንጌሉም ጭምር እጅግ በተሻለና በተዋበ ሁኔታ የሕይወትን እና የደህንነትን ተስፋ ይሰጣል (ዮሐ 3፡ 15-16፤ 5፡ 24)፣ ነገር ግን፡-
·         ወንጌል ጽድቅን ለማግኘት ሲባል አስቀድመን እኛ ልንፈጽመው የሚገባን ምንም ቅድመ ሁኔታ የለውም (ሮሜ 3፡ 28፤ 4፡ 1-5፤ ገላ 3፡ 18)፣ ስለዚህ፡-
-   ወንጌል ኃጢአተኛ የሆነውን ሰው በክርስቶስ ጻድቅ ብሎ ያውጃል (ሮሜ 4፡ 5፤ 5፡ 6-8)
-   ወንጌል ሁልጊዜ ሕይወትን እና የኃጢአት ይቅርታን በንስሃና በእምነት ለሚመጡ ያቀርባል፡፡ ንስሃና እምነት ግን የሰው ስራ ሳይሆኑ የእግዚአብሔር የጸጋው አሰራር ናቸው፡፡

-   ክርስቶስ ብቻ የሕጉን ጥያቄ ፈጽሞ አከናውኖአል፡፡ ለደህንነታችን እርሱ ያደረገው ብቻ በቂ ነው፡፡
 
4.   የሕጉ ማስፈራሪያና የወንጌሉ ነጻነት፡-
Ø  ሕጉ የሚያስፈራራን በቅጣቱ ብቻ ነው (ዘፍ 2፡ 17 “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”ዘሌ 26፡ 14-17፤ ዘዳ 27፡ 26 “የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ”፤ ገላ 3፡ 10 “ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው”)፡፡

Ø  ወንጌሉ ባበሰረልን ነጻነት ያጽናናል እንጂ ፈጽሞ በቅጣት አያስፈራራንም (2ሳሙ 12፡ 13 ዳዊትም ናታንን፦ “እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል አትሞትም”፤ ማቴ 9፡ 2 “…. አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው”፤ ሉቃ 7፡ 47 “እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል”፤ ዮሐ 8፡ 3-11 /ቁ11 “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት”/፤ 1ጢሞ 1፡ 15 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ”)፡፡

·         ሕጉ በእኛ ላይ ያለውን የቅጣት ማስፈራሪያ ዝም ያሰኝ ዘንድ እኛ የሚገባንን ፍርድ ክርስቶሰ በራሱ ላይ ወሰደው፡፡ በወንጌል ፍርዳችን ተወግዶልናል፡፡

5.   የሕጉና የወንጌሉ ውጤት፡-
Ø  ሕጉ እንድንፈጽም የሚጠይቀንን የግድ ይጭንብናል እንጂ የማድረግን አቅም አይሰጠንም፡፡ ከዚህም የተነሳ
-   አመጸኞች ያደርገናል (ሮሜ 7፡ 5፣ 7-11፣ 13)፣
-   ወደተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያዘቅጠናል እንጂ ከኃጢአታችን እንድንወጣ ፈጽሞ እይረዳንም (ማቴ 27፡ 3-5፤ ሮሜ 7፡ 7፣ 24)
-   እንድናዝን፣ እንድናፍር እና እንድንፈራያደርገናል እንጂሊያጽናናን ከቶ አይችልም (2ሳሙ 12፡ 7-13ሀ፤ ሐዋ 2፡ 36-37)፡፡

Ø  ወንጌሉ እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ኢየሱሰ ያዘጋጀልንን ሰማያዊና መንፈሳዊ በረከት እንድንቀበል የሚጋብዘንና የሚያስችለን ነው (ሐዋ 16፡ 27-31 “…. እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት”፤ ሮሜ 10፡ 17)፣ ስለሆነም፡-
·         ፍርሃትን፣ ጭንቀትንና መሳቀቅን ሁሉ አስወግዶ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሰላምንና ደስታን ይተካል (ሮሜ 5፡ 1-2፣ 10-11፤ 8፡1)
·         ጥሩ ልብ ሆነ ጥሩ አቅዋም፣ የባሀረይ መሻሻልን ሆነ ሃይማኖታዊ መንፈሳዊነትን ወይም ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው የሆነ ፍቅርን እንደቅድመ ሁኔታ አያቀርብም፡፡ ምክንያት አልባው የወንጌል ትሩፋት ጉዳዩ እኛን መለወጥና አዲስ ፍጥረት ማድረግ እንጂ ይቅደም ተከተል ወይም የቅደመ ሁኔታ ነገር ማስቀመጥ አይደለም (2ቆሮ 3፡ 18፤ 5፡ 17፤ ኤፌ 5፡ 8 ቆላ 1፡ 21-22)፡፡

-   ሕጉ እይወቀሰ፣ እየከሰሰ፣ እያሸበረ እና እየኮነነ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሚናን ይኸውም እንደ ሞግዚት ወደ ክርስቶስ መምራትን ዓላማ አድርጎ ያገለግላል አንጂ በራሱ ማናችሁናም ቢሆን ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፡፡ ከዚያ በኁዋላ ወንጌሉ የይቅርታ ስራውን እና በሕይወትህ ፈውስ ማድረግን መስራት ይችላል፡፡ ሕጉ ኃጢአትን ይገልጣል፣ ይቃወማል፣ በኃጢአት ላይ ይፈርዳል እንጂ ኃጢአተኛውን አያድነውም፤ ወንጌሉ በሕጉ የተፈረደበትን ኃጢአተኛ ይቅረ ብሎ ያጸድቀዋል

6.   የሕጉና የወንጌሉ ተደራሲያን፡-
Ø  ሕጉን መስማት ያለባቸው ኃጢአተኞች በሙሉ ናቸው (1ጢሞ 1፡ 9)

Ø  ወንጌሉን መስማት ያለባቸወ ደግሞ ስለ ኃጢአታቸው ልባቸው የተሰበረባቸውና ያዘኑ ሁሉ ናቸው (ኢሳ 61፡ 1-3፣ ሉቃ 7፡ 37)፡፡


·         በማሕበረ ምዕመናን ውስጥ ንስሃ የገቡና ያልገቡ አብረው ሲሰበሰቡ፣ ሁሉም አይነት ሰዎች ባሉበት ሕጉና ወንጌሉ ሁለቱም መታወጅ አለባቸው፡፡ ሕጉ ሲመዝነን አኛ ቀለን እንገኛለን፣ ወንጌል ግን በማንም አይመዘንም፣ ከምናስበው፣ ከመሻታችንና ከሚገባን በላይ ያደርግልንና በሕጉ ፊት ሚዛናችንን ያከብደዋል፣ ከፍም ያደርገዋል፡፡

2)   ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የእግዚአብሔር መገለጥ ነው
የወንጌሉ እምብርተ፣ የቃሉ መገለጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለምዋል የሆነው ያ ሰው “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” የተባለው ነው፡፡ የቃሉን መሰረተ እምነት ለመረዳት ዮሐንስ 1፡ 1እና 14 ላይ ያለውን ትምህርተ ክርስቶስ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው በ1ዮሐ 1፡ 1-3 ባለው ክፍልም ተመሳሳይ አገላለጽ ይጠቀማል፡፡

ስለዚህ ቃሉ ሰው ነው፡፡ ይህንን አገላለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰማ ሰው እንግዳ ሊሆንበት ይችላል፡፡ በተለመደው ሁኔታ ቃል ከሳምባችን በአየር መተላለፊያችን አማካኝነት እየተገፋ በሚወጣው አየር ምክንያት በምላሳችንና በከንፈራችን ላይ የሚፈጠር አንድን ነገር ወይም ሃሳብን የሚገልጽ ትርጉም ያለው ድምጽ ነው፡፡ በሌላም በኩል ቃል የሚሰማ ድምጽ በሚፈጥሩ የጽሁፍ ቃላት የሚፈጠሩ የፊደላት ጥምረት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ “ቃል ሰብዓዊ” በመባል ይታወቃል፡፡ ግን ቃል  ሰው ሊሆን እንደሚችል እንዴት በቀላሉ ማሰብ ይቻላል? ልብ በሉ ዮሐንስ ቃል ሰው ሆነ ይላል፡፡ ይህ ማለት አምላክ ሰው ሆነ ማለት ነው፣ ቃል እግዚአብሔር ነበርና፡፡ ይህ ሚስጥር አዕምሮን ሁሉ የሚያልፍ ምጡቅ ሃሳብ ነው፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረ የእግዚአብሐር ቃል ስጋን ሆኖ የሰውን ደካማ ስጋ ለበሰ፣ ስጋ አምላክ ተባለ፡፡

ዮሐንስ እንዳለው ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፣ ራሱም እግዚእብሔር ነበር፡፡ አስደሳቹ ዜና ግን ይህ ቃል ስጋ ለብሶ እና ሰው ሆኖ በእኛ ዘንድ ማደሩ ነው፡፡ ዮሐንስ በገዛ ራሱ ዓይኖች ቃልን ተመለከተው፣ በእጆቹም ዳሰሰው፣ ከዚህ የተነሳም በግልጽ ስላየውና ስለዳሰሰው ቃል ይመሰክራል፡፡ ቃል በጆሮ የሚሰማ በዓይን የሚነበብ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የሚታይ እና የሚዳሰስ ሆነ፡፡ ሉቃስም ከመጀመሪያ (ቃሉን) በዓይን ያዩት … (ሉቃ 1፡ 1) ሲል ተመሳሳይ አገላለጽን የሚጠቀም እንደሆነ ተመልከቱ፡፡

እንደዮሐንስ ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል ከድምጽ፣ ከንግግርና ከጽሑፍ ያለፈ ሰው የሆነው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱም ከዘላለም እግዚአብሔር አብ ጋር ለዘላለም የሚኖር ነው፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ግን ይህ ቃል የሰውን ስጋ ይለብስ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በድንግል ማሪያም ማህጸን ተጸንሶ ተወለደ፡፡ መላዕክት በሰማያት፣ ጠቢባኑም በምድር ቃል ስጋ ሆኖ በተመለከቱ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱለት፡-

 ….ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ (ዕብ 1፡ 6)፤

ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። (ማቴ 2፡ 11)

ክርስቶስ ቃሉ ነው፡፡ ስለዚህ በስብከት የሚታወጀው ራሱ ክርስቶስ ነው፡- ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። (ሐዋ 8፡ 5)፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ (2ቆሮ 4፡ 5) እንግዲህ ቃሉ ምንድን ነው? ከተባለ ስለክርስቶስ ኢየሱሰ የሆነ መገለጥ ነው፡፡ ደቀመዛሙርት የሰበኩት ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በሕይወቱ፣ በመከራው፣ በሞቱና በትንሳኤው ያደረገው ሁሉ ነው፡፡ ወንጌሉ ስለክርስቶሰ የሆነው መልዕክት ነው (ሮሜ 1፡ 1-5)፡፡