Sunday, August 24, 2025

ለምን ፕሪተሪስት ሆንኩኝ?

ለምን ፕሪቴሪስት ሆንኩኝ?


የተፈጸመውን ወንጌል የተቀበልኩት ያለ ምክንያት አይደለም!!


የመጻኢነትን ጎራ በይፋ ለቅቄ ለምን ፕሪቴሪስት ሆንኩኝ? እንዲህ ያለ ትለቅ ውሳኔ ለመወሰን እና የአቋም ለውጥ ለማድረግ ያስቻሉኝ የማላስተባበላቸውን ምክንያቶቼን ማካፈል እንዳለብኝ ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል። ፈራ ተባ እያልኩ ለብዙ አመታት በተደከመበት የመጽሓፍ ቅዱስ ጥናት ልምምዴ አስቀድሞ “የጌታ ምጽአት ቀርቧል” እያልኩኝ ሳምነው እና ሳስተምረው የኖርኩትን አቋሜን እየተፈታተነ፣ አንዳንድ ጊዜም አለኝ የምለውን ተስፋ ከእጄ ላይ እያራገፈ ጡጦውን እንዳስጣሉት ህጻን ነጭናጫና ብስጩ ያደርገኝ የነበረውን የነገረ ፍጻሜ እውነት የሄ ደግሞ ምን ያመጥብኝ ይሆን ከሚል ስጋት ጋር ስጋፈጥ ኖሬአለሁ። ሳምነው ከኖርኩት ልማዳዊ የትምህርት ቀንበር ለመላቀቅ እና ቃሉ ብቻ በሚናገርለት እውነት ላይ ቆሞ ለመገኘት፣ በዚህ ሁሉ አድካሚ ጉዞ ውስጥ በነገረ ፍጻሜ አቋሙ የፕሪቴሪስት ምልከታ ብቻ ትክክለኛውና ተገቢው የመጽሓፍ ቅዱስ ፍቺ መሆኑን ስቀበል በግሌ “አናት ፈጥፍጥ” “ደብረ በጥብጥ” ሆኖብኝ አልፌዋለሁ። እውነት ከቀንበር ይከብዳል፣ ሲመጣም ብዙ ነውጥ እና መንቀጥቀጥ ስለሚፈጥር ያስፈራል፤ ፍሬውና ውጤቱ ግን ከማር ይጣፍጣል። ከህሊናዬ ጋር በመቆም የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ድጋፍ ያለውን ፕሪቴሪዝምን የእምነት አቋሜ አድርጌ ለመውሰድ፣ አስተምህሮዬንም በዚህ መስመር ለመቅረጽና ዘመኔን ሁሉ ለምቦጬ ላይ ተወትፎ ስጠባው ከኖርኩት የልማድ ጡጦ ለመላቀቅ የነበረብኝ ፈተና ቀላል አልነበረም። ምናልባትም እኔ እንደያዝሁት ያለ አይነት የእምነት አቋም ያላቸውን የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች አንድና ሁለት እንኳ ማግኘት በማልችልበት ወቅት ከብቸኝነቱ ፈተና ጋር ከማን ጋር ላውጋው፣ ማንስ ስራዬ ብሎ ሊሰማው ይችላል የሚል ጥያቄና፣ ከወገኞቹ ወዳጆቼ ዘንድ ሊፈጠርብኝ ከሚችል የመገለል ስጋት ጋር መታገል ነበረብኝ። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን በማመኔ ያጋጠመኝ ከባድ ችግር ነበር ብዬ ለመናገር ባልደፍርም ከተቋምም ሆነ ከግለሰቦች ሊሰነዘርብኝ የሚችል በትር እንደሚኖር ግን አላጣሁትም። እንደውም አንድ ወንድም የእግዚአብሔርን ደግነት አንስቶ ሲያወጋኝ፣ “እንኳንም ከዚህ እምነትህ ጋር ከአገር ወጣህ፣ እዚህ ብትሆን ኖሮ ይሰቅሉህ ነበር” ብሎ አስቆኛል። እኔም “ምን፣ መሰቀል ብርቅ ነው እንዴ? እንኳን እኔ አንድ ጭንጋፍ ቀርቶ የልዑል ልጅ የሆነውም ተሰቅሏል” ብየ መመለሴን አስታውሳለሁ። ዛሬ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ርዕሰ ጉዳዩን ዋጋ ሰጥተው የሚሰሙ፣ ሊማሩም የሚወዱ፣ እምነታቸውን አፋጠው የሚጠይቁ፣ ሲያምኑት የኖሩትን የትምህርት ድሪቶም አውልቆ ለመጣል የሚደፍሩ ጥቂት ያይደሉ የቃሉ ወዳጆችን ተዋውቄአለሁ። ቢያንስ ከነርሱ ጋር እጽናናበታለሁ። እህ ብለው ሊሰሙና ሊማሩ የሚወዱ ከተገኙም በልብ ስፋት የማካፍለው የተፈጸመው ወንጌል አለኝ። በዚህች አጭር ክትባት ፕሪቴሪዝምን ትክክለኛው የነገረ ፍጻሜ አቋም እና የተፈጸመው ወንጌል ትምህርት ነው ብዬ እንደቆምኩ የማሳይበትን ጥቂት ምክንያቶቼን በወፍ በረር ላካፍላችሁ፤ ምናልባትም በወገኖች መካከል የሰከነ ውይይት እንዲኖር መንደርደሪያ ነጥቦች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፦



  1. ሳዳምጣቸው የኖርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች እኔ በትንቢት ቃል ላይ ለተፈጠሩብኝ ፈታኝና መሰረታዊ ጥያቄዎች አንጀት አርስ የሆነ፣ አመክንዮአዊ ትርጉም ያለው መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም። እንዲያውም ርእሰ ጉዳዩ ሲነሳ፣ ይባስ ብለው ለእውነት ቃል ብዙም ፍላጎት የሌላቸው አይነት ይመስሉ ነበር። ከዚያ ይልቅ ግን ያንንው የኖረ የቤተክርስቲያን ልማዳዊ አመለካከትና አቋም በተሳሳተ ስነ ሃቲት ለመከላከል የበለጠ ፍላጎት ይታይባቸው ነበር። እነርሱ አውድ ዘለል በሆነ ስነ ሃቲት የሙጥኝ ብለው ከያዙት ዳተኝነታቸው ጋር መቀምጥን በመረጡ መጠን እኔ ደግሞ ከጥያቄዎቼ ጋር መቆየትን አልፈለግሁም። መልስ እሻ ዘንድ ብዙ ደከምሁ። መከተልም ያለብኝ እንደ እኔ በጎች ብቻ የሆኑትን ሳይሆን ራሱን የበጎቹን እረኛ ለመከተል እፈልግና አዘነብል ነበር። ፍላጎቴም ለእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነት መወገን እንጂ ለኖርኩበትና ላደግሁበት ተቋም መወገን አልነበረም። መልሴን ያገኘሁት በዚህ መስመር ነው። 
  2. እንደ ቃሉ ወዳጅ እና ተማሪ በተለይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለትንቢት ፍጻሜ ቀነ ቀጠሮውን በሚያመለክቱበት ልክ በግልጽ የተቀመጡትን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባትና ጥቅሶችን “ባላየ ማለፍም” አልሆንልኝም። በበዛ መቀመጥ ቃሉን እያጠናሁ ሳለ እነዚያ በትንቢት የተነገሩ ክንውኖች ለፍጻሜአቸው የተመደበውን ጊዜ በተመለከተ፣ ራሳቸው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በሕይወት በነበሩበት ዘመንና በትውልዳቸው ውስጥ የተገደቡ መሆናቸውን የሚያመለክቱ በቁጥር ከ100 በላይ የሆኑ ጊዜ ተኮር ንግግሮችን ምንም ሳልቀባባ እንዳለ ለመውሰድ በጎ ሕሊና ይኖረኝ ዘንድ ተግቻለሁ። ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድን የሚፈጸም ኹነት ሲናገር የሚፈጸምበትንም ጊዜ የሚናገር የታመነ አምላክ ነው። ፊት ለፊት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ከ100 በላይ የሚቆጠሩ የኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ጊዜ ተኮር ንግግሮች ችላ በማለት ድንቁርና ውስጥ እንዳልወድቅም ጸልያለሁ።
  3.  “የመጨረሻውን ቀን” ወይም “የዘመን ፍጻሜን” አስመልክቶ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ቋንቋ የተነገሩ ከአሥራ አምስት በላይ የሆኑ ልዩ ጥቅሶች አውደ ምንባባቸው ላይ የፍታቴ ጥሰት እና ድፍጠጣ ሳይፈጸም መቼታቸው ሲመረመር በመለኮት የተያዘላቸው የፍጻሜ ቀነ ቀጠሮ ከመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን በላይ የሚሻገር እና ሁለትና ሶስት ሺህ አመት የሚጠበቅ ፍጻሜ እንደሌላቸው የሚያመለክቱ መሆናቸውን ተረድቻለሁ። ስለዚህም አሁን በእኛ ዘመን ወይም ከእኛ ዘመን በኋላ በቅርብ ወይም በርቀት ላለ የዘመን ቁጥር የተቀጠረ ምንም የትንቢት ፍጻሜ አለመኖሩን የልቁንም የትንቢት ፍጻሜ ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስራኤል እና ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተገንዝቤአለሁ።
  4. ታሪክን በወጉ እንደማላውቅ፣ ይልቁንም በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ላይ ስለተከሰተው ነገር፣ እነዚህም ክስተቶች ከትንቢት ፍጻሜ አንጻር መታየት እንዳለባቸው የያዙትንም ሥነ-መለኮታዊ ፋይዳና ጠቀሜታ በአግባቡ እንደማልረዳው የገባኝ አርፍጄ ነው። ታሪክንም ለማንበብ እድሉንና አጋጣሚውን ባገኘሁ መጠን እምነቴን የሚያስጥለኝ እየመሰለኝ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ እገባ ነበር። ምናልባትም ኤን.ቲ.ራይት “አብዛኛው ክርስቲያን ታሪክን ይፈራል፣ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የሆነውን ነገር በትክክል ካወቅን እምነታችን ተንኮታኩቶ ይወድቃል ብሎ ይፈራል።” ሲሉ እንደተናገሩት ሳይሆን አይቀርም። እኔም ጌታ ኢየሱስ በየሩሳሌምና በጠቅላላው በዚያ አሮጌ ስርዓት (sistem) ላይ ፈጥኖ ሊደርስ ስላለው ጥፋት የተናገረውን ትንቢት ከዚህ ታሪካዊ ፍጻሜው ለይቶ የማየት ነገር ልማድ ያቀበለኝ ኣባዜ ነበርብኝ። አሁን ግን ከብርድ የማያስጥለኝን ይህን ድሪቶ አውልቄ ጥየዋለሁ።
  5. የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በሙሉ ማለት በሚቻልበት መልኩ ፍጻሜአቸውን የሚያገኙት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በኖሩበት በራሳቸው ትውልድ ማለትም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እንደሆነ ስረዳ በእውነቱ ድንጋጤዬና ያሳለፍኩት ይህንን ያለማወቅ ወራት በተመለከተ የተሰማኝ ኃፍረት ልክ አልነበረውም።
  6. ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ራሳቸው ዘመን እና በትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸሙ በተነገሯቸው ትንቢታዊ ክንውኖች፣ ጊዜውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ተሳስተው ከነበረ እንግዲያውስ ኢየሱስም ሐሰተኛ ነቢይ፣ ደቀ መዛሙርቱም ሐሰተኛ ምስክሮች ናቸው በሚል በከሃዲዎችና በማያምኑ ሊቃውንት በክርስትና ላይ የሚቀርበው ክስና ትችት ልክ ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለውን የተቺዎችን ክስና ነቀፋ በብቸኝነት መከላከል የሚቻለው እና ለተቃዋሚዎች ብረት መዝጊያ የሆነ መልስ ለመስጠት አቅም ያለው የፕሪቴሪስት እይታና መረዳት ብቻ ነው። ፕሪቴሪዝም በሚያቀርበው የትንቢት ትርጉም ብቻ ኢየሱስ ቃሉን እንደጠበቀ፥ ሐሰተኛ ነቢይም እንዳልሆነ፣ እመለሳለሁ ባለበት ጊዜም ተመልሶ እንደመጣ ማስረገጥ ይቻላል። አዎ፣ ፕሪቴሪዝም በሚሰጠን ብርሃን ብቻ፦ “ቃሉን ከቶ የማያጥፍ ታማኝ አምላክ ነውና፣ የነገረንን ሁሉ ፈጽሞት አይተናልና፥ ከፍ ከፍ እናደርገዋለን በምስጋና” ብለን መዘመር እንችላለን። ከዘላለም ከአብ ጋር የነበረ ቃል የሆነ እርሱ የመመለሻው ጊዜ በገዛ ራሱ ትውልድ መሆኑን አስረግጦ መናገሩን በምንም ልናስተባብለው የማይቻለን ያፈጠጠ እውነት ነው። እርሱ ለተናገራቸው ለነዚህ ቃላት ምንም አይነት ሰበብ እና ማመካኛ አቅርበን ቃሎቹን በማስተካከል ፈተና ውስጥ አንገባም። እነዚያን ፈታኝ እና አዕምሮን ወጥሮ የመያዝ አቅም ያላቸውን ቃላት እና አንቀጾችም ላይ ምንም አይነት “ምሁራዊ” የደናቁርት ማመቻመች አናደርግም። ለዘላለም ሕይወት ያመነውን ጌታ የመመለሻውን ጊዜ አስመልክቶ ተሳስቶ ነበር የሚለውን አጉል የምሁራን ድምዳሜም አንታገስም።
  7. ስለ መጨረሻው ቀን ምልክቶች፣ “ጨረቃ ወደ ደም ይለወጣል”፥ “በደመና የሚመጣ”፣ “የሰማያት ሃይሎች ይናወጣሉ” ወዘተ የመሳሰሉትን ንግግሮች በተመለከተ ቋንቋዎቹን በጥሬው ተርጉሞ መረዳት እንደሚገባ በርካታ ክርስቲያኖች ሲከራከሩ አድምጫለሁ፤ እንዲህ ያለ አቋም ከያዙቱ መካከል አንዳንዶቹ ብዙ ተምረዋል፣ መጻህፍትም አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል፣ በየመድረኩም ዝናን ያተረፉ ሰባኪያንና መምህራን ናቸው ከሚባሉት መካከል ይቆጠራሉ። አለማፈራቸው ያሳፍረኛል። የጠቀስኳቸውን እነዚህንና መሰል የኮስሞሎጂ ነውጥ አመልካች የሆኑ ሀረጎች እና ቃላት እንዳለ በጥሬው እና ቃል በቃል በሆነ ይዘታቸው መተርጎም የሚገባቸው በመሆን አለመሆን ላይ ሁል ጊዜ ስጠራጠር እና ስጠይቅ ኖሬአለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል የንግግር ዘይቤዎቹንም በጥልቀት ለመረዳት ባደረግኩት ጥናት ይህ ጥርጣሬዬ ተገቢ መሆኑን አረጋግጫለሁ። እንደነዚህ ያሉት ሐረጎች በታሪክ ውስጥ በከተሞች ላይ ወይም በልዩ ልዩ ሕዝቦችና መንግስታት ላይ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፥ ይኸውም ፍርዱ ማለት ነው፥ ያንን የፍርድ አሰራር ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ በጥሬው የማይተረጎም ትዕምርታዊና ምሳሌአዊ የሆነ የዕብራይስጥ አቡቀለምሲሳው የስነጽሁፍ ዘይቤ ንግግሮች ናቸው።
  8. መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ገጹ ላይ ስለዚህ ተዳሳሽ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ወይም ስለ ፕላኔት ምድር ፍጻሜ ምንም እንደማይናገር ተገነዘቤአለሁ። በእርግጥም ይህ ግዑዝ አለም ያልፋል የሚልን ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ አምጥቶ የሰነቀረው የኖረ ልማዳዊ የቤተክርስቲያን አመለካከት ነው እንጂ እንዲህ ያለው ርዕሰ ጉዳይ በቃሉ ውስጥ ፈጽሞ ምንም መሰረት የለውም።  
  9. ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ በየዕለቱ በሚወጡት ትኩስ የዜና ክንውኖች መነጽር፣ በተለይም የመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ ወጥረት ላይ አይናቸውን ተክለው የማንበብና የመተርጎም ዝንባሌ እንዳላቸው አስተውያለሁ። ከዚህም የተነሳ ላለፉት 2,000 ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ዓለም ፍጻሜ የለየለት ውሸትና በርካታ አሳፋሪ ትንበያዎች ሲነገሩ ቆይተዋል። እጅግ ከማከብራቸውና በተለያዩ ስራዎቻቸው ከተጠቀምኩባቸው አስደማሚ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና በታሪክ ሰመ ጥር ከሆኑቱ መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ጉዳይ የፈጸሙት ስህተት ታሪክ በትዝብት ሲያወሳው ይኖራል። በምትኩ ግን ቃሎቹን በዋናዎቹ በኩረ ተደራሲያን አውድ መነፅር የሚያነቡ ቢሆን ኖሮ ስለሚያነቡት የትንቢት ቃል የተለየ ሥዕል ባገኙ ነበር። ስለዚህ ከመጽሓፉ ትንቢት ተነስቶ የአለምን ፖለቲካ እና ዘመናዊ ክስተቶችን መተንተን እንደማይገባ ሁሉ፤ ከአለም ፖለቲካና ከዘመናዊ ክስተቶች እየተነሳን የመጽሓፍ ቅዱስን ትንቢት ብንተረጉም ተመሳሳይ ስህተት ይሆናል። ቃሉ ራሱን እንዲተረጉም አውደ ምንምባቡ መጠበቅ አለበት።
  10. ከመቶሰላሳ በላይ የሆኑ የስነ መለኮት ሊቃውንት የራዕይ መጽሓፍ የተጻፈው ከ70 ዓ.ም በፊት እንደሆነ በማስተማር ይታወቃሉ። የራዕይ መጽሓፍ ቀደም ባለው ጊዜ ይኸውም ከ70 ዓ.ም በፊት ተጽፏል የሚለው እይታ አዲስና እንግዳ ግኝት አይደለም። የራዕይ መጽሓፍ በአብዛኛው የሚያወሳው ከ66-70 ዓ.ም በአይሁድ-ሮማውያን ጦርነት ወቅት በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ስለደረሰው ጥፋት መሆኑን ስንረዳ ትንቢቱ የሚያወራው ስለ አለም ምጨረሻ ሳይሆን እግዚአብሔር ያንን ጦርነት ተጠቅሞ እስራኤልን እንደሚያጠፋት፣ ይህም ከመሆኑ 5 እና 6 አመታት ቀደም ብሎ የተነገረ ትንቢት መሆኑን እናስተውላለን።
  11. በራዕይ መጽሓፍ ውስጥ (ሀ) ራዕዩ ከተፃፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቶሎ ፍጻሜውን የሚጠይቅና የሚጠበቅ ጉዳይ እንዳለ፣ እንዲሁም (ለ) የራዕይ መጽሓፍ አዲስና እንግዳ ጽንሰ-ሀሳቦችን እንደማያስተዋውቅ፥ ይልቁንም እነዚያ ይሆናሉ ተብለው የተገለጹትን ክስተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ቦታ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን የሚያስረዱ ከ30 በላይ ምንባቦች ያሉ እንደሆነ አስተውያለሁ።
  12. በፕሪቴሪዝም ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች ምንም ጥልቀት የሌላቸው፣ መያዣ መጨበጫቸው የማይታወቅ፣ አድሏዊነት እና ወገንተኝነት የተጠናወታቸው፣ በዘፈቀደ ትርጉም የሚለፈለፉ እና ወጥነት የሌላቸው መሆናቸውን አስተውያለሁ። ፕሪቴሪዝምን እንቃወማለን የሚሉ ሰዎች በሚያቀርቡት ትችት በአመዛኙ ሆነ ብለው ቁልፍ የትንቢት ምንባባትን ሲያጣምሙ ይስተዋላሉ። እውነታን ላለማየትም አይናቸውን አሳውረዋል፥ ስለጉዳዩም ተገቢውን ምርመራ ሳያደርጉ በአብዛኛው ሲናገሩ የሚደመጠው ጉዳዩን በትክክል ካላጠኑ ሰዎች የሰሙትን ነገር እንደ በቀቀን ሲደግሙ ነው። የደብረ ዘይቱን ፍካሬ አንድ ምዕራፍ ለማንበብ አቅምና ጊዜ የሌለው ሰው አስቦበት እንኳ በማያውቀው የነገረ ፍጻሜ ረዕሰ ጉዳይ አዋቂ ተናጋሪ ሆኖ ሲቀርብ ያሳፍራል። 


እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ለፕሪቴሪዝም አስተምህሮ ፍላጎት እንዳሳይና አመለካከቴን፣ እምነቴንና አስተምህሮዬን እንዳርም ምክንያት የሆኑኝ ነጥቦች ናቸው። ለኔ ታላቅ መጽናናትን ያጎናጸፈኝ የተፈጸመው ወንጌል ለሌሎችም እንዲሁ እንዲሆንላቸው ከመጸለይ፣ ለሚጠይቁኝም መልስ ለመስጠት ዘወትር እየተዘጋጀሁ በእግዚአብሔር ቃል ከማስረዳት በቀር ምንም ፍላጎት የለኝም። ብትወዱ ጉዳዩን ትመረምሩና የህሊናችሁን ፍርድ ትሰጣላችሁ እንጂ በጌታ ወንድማችሁ ከመሆን ጸጋ አታቅቡኝ። ደግሜ እላለሁ ባነሳኋቸው ጉዳዮች ምክንያታዊነት የምትበሳጩና ቁጣ የሚሞላባችሁ ብትሆኑ፣ ወይም ቃሎቼ ቢያስፈራችሁ እና ተስፋ ቢያሳጣችሁ አልያም ይሄ ደግሞ ምን ይቀባጥራል ብትሉ፥ ምክሬ ግን አንድ ነው፤ በተቻላችሁ መጠን ኢ-ምክንያታዊ ከመሆን ተቆጠቡ። ጉዳዩን በራሳችሁ አይን ከቃሉ እስክታዩት ድረስ እባካችሁ የኔን ቃል እንዳለ አትውሰዱት፤ ሰነፍ ፈራጅም አትሁኑ። አስቀድማችሁ ግን በዚህ አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተገቢውን የቤት ስራችሁን ስሩ። እኔም በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ጊዜ ወስጄ እንዳሰብኩበት የሚያሳዩአችሁን የተለያዩ ጥሁፎቼን ታዩ ዘንድ ብሎገሬን ለመጎብኘት አትታክቱ፤ መክፈቻው እነሆ 


http://gizachewkr.blogspot.com/2025/02/blog-post.html


ይህንንም ሆነ ማናቸውንም ጽሁፎቼን ሌሎች ይማሩበትና የጠቀሙበት ዘንድ ላይክ እያደረጋችሁ ልታጋሩት ኮፒ አድርጋችሁ ልትይዙት፣ አስተያየታዊ ትችቶቻችሁን እና ሙግቶቻችሁን እያቀረባችሁ ልትጠይቍ መብታችሁ ነው።

 ግዛቸው።




From Blogger iPhone client

Friday, August 22, 2025

የዳግመኛ ምጽአቱ ሰበብ




የዳግመኛ ምጽአቱ አይነተኛ ሰበብ 


ዳግመኛ ምጽዓት ሊፈጸም የተቀጠረለትን ትክክለኛውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት፣ የዳግመኛ ምጻቱን ተፈጥሮ ከመረዳት ባልተናነሰ የዳግመኛ ምጽአቱን አይነተኛ መግፍኤ ምክንያትም በወጉ መረዳት ያስፈልጋል። በአመዛኙ ኢየሱስ ስለ ብድራት፣ ስለፍርድ፣ ስለ ቁጥጥር ቀን ባስተማረበት ምሳሌዎቹ ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን ሰበብ እንመለኩታለን። ኢየሱስ ስለ ክፉዎቹ የወይን እርሻ ገበሬዎች በተናገረው ምሳሌ ላይ ይህን ጉዳይ በግልጽና በቀጥታ አስተምሮታል።


“ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው [እግዚአብሔር] ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎችር [እስራኤል] አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን [መልካምን ስራ] ሊቀበሉ ባሮቹንል [የብሉይ ኪዳን ነብያት] ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን [ኢየሱስ] ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት [ስቅለቱ]። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜቱ [የኢየሱስ ዳግም ምጽ አጽአት] በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? እነርሱም፦ ክፉዎችን [እስራኤል] በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች [ክርስቲያኖች] ይሰጠዋል አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተች [ከእስራኤል] ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ [ለክርስቲያኖች] ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤” (ማቴዎስ 21፥ 33-45)


ይህ ምሳሌ እንደሚያሳየው፣ የእግዚአብሔር አላማና ፍላጎት እስራኤል ፍሬ እንዲያፈራለት (መልካምን ሥራ እንዲያደርግለት) ነው፣ ያንንም ይጠባበቅ ነበር። “ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ።” (ኢሳይያስ 5፥ 7) እንደተባለው፤ በአብዛኛው የእስእስራኤል ታሪክ ውስጥ የሆነው እግዚአብሔር ይጠባበቅ ከነበረው ፍጹም ተቃራኒው ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እስራኤል በዙርያዋ ካሉ አረማውያን ጎረቤቶቿ ይልቅ በክፋትና በአመጽ ብሳ ትገኛለች። (2ዜና 33፥ 9፣ ሕዝ. 5፥ 6)። እግዚአብሔር እስራኤልን ንስሐ እንዲገቡ ለማድረግ (ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ) በየጊዜው በርካታ ነቢያትን ልኮላቸዋል። እስራኤል ግን እነዚያን ነቢያት አሳደዱ፣ አንገላተውም ገደሏቸው። በመጨረሻም እግዚአብሔር “በእውነት ልጄንስ ያከብሩታል” (ማቴ. 21፥ 37) ብሎ የገዛ ራሱን ልጅ ላከው። እስራኤል ግን እርሱንም ገደለችው። (ቴክኒካሊ፣ ሮማውያን ኢየሱስን የገደሉት ቢሆንም፣ ያንን የፈጸሙት ግን በአይሁድ ልመናና ጥያቄ መሰረት ነው- ሉቃስ 23፥ 21፣ ዮሐንስ 1፥ 11 ተመልከቱ)። ይህ የመጨረሻው እድላቸው ነበር፣ የእግዚአብሔርም ትእግስት እዚህ ላይ አበቃ። ምሳሌው እንደሚለው፡- “የወይኑ አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ . . . እነዚያን ክፉዎች በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም እርሻ ለሌሎች ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ገበሬዎች ያከራያል” (ማቴ. 21፥40-41)።


ይህ እንግዲህ በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው የዳግም ምጽአት ትምህርት አንድ ሌላ ማጣቀሻ ነው!


ምሳሌው በመቀጠል “ስለዚህ እላችኋለሁ [እስራኤል]፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። (ማቴዎስ 21፥ 43) መንግሥቱ ለየትኛው “ህዝብ” ነው የተሰጠው? ለክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ነው፣ እርሷም ከእስራኤል ጻድቃን ቅሬታዎች (ጥቂት የተመረጡ) ጋር የአሕዛብ ጻድቃን ቀሪዎችን ያቀፈች ናት።


እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ለእስራኤል የነበረው አሳብ ለእርሱ ቅዱስ ሕዝብ እንዲሆኑለት ነበር። እግዚአብሔር አሮጌውን ቃል ኪዳን ሲያቆምላቸው (ይኸውም ከክልበ በ1500 ገደማ ነው)፣ ይህም በመሠረቱ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የተደረገ የቃል ኪዳን ስምምነት ውል ነበር - ያኔም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ” (ዘጸአት 19፥ 5-6,) እግዚአብሔር እስራኤል የተቀደሰ (የተለየ) ሕዝብ እንድትሆንለት ነበር የሚፈልገው፣ የቃል ኪዳኑም ግብ ይኸው ነበር። ቃል ኪዳኑ ግን የቆመበት ቅድመ ሁኔታ አለው እርሱም፡- “ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ... ለኔ ልዩ ርስት፣ የተቀደሰ ሕዝብም ትሆኑልኛላችሁ” ይላል። በሙሴ ቃል ኪዳን፣ በኦሪት፣ በሕጉ የተነገሩትት የብሉይ ኪዳን በረከቶች በእስራኤል መታዘዝ ላይ የተመሰረቱ ነበሩ። በሚያሳዝን ሁኔታ ኢየሱስ ስለ እነዚያ ክፉ የወይን ቦታ ገበሬዎች ከፍ ሲል በተናገረው ምሳሌ እንዳመለከተው እስራኤል በቃል ኪዳኑ የተሰጣትን ተስፋ እንዳታገኝ እነዚያን ቅድመ ሁኔታዎቹ መታዘዝ ተስኗታል። እስራኤል በህጉ ኖራ ልታቀርበው የሚገባትን የጽድቅ ፍሬ ማፍራት ተስኗታል። እግዚአብሔርም እርሷን ለማረም በየዘመኑ ነቢያትን ቢልክም እስራኤል ግን አልሰማቻቸውም፣ አሳዳም ገድላቸዋለች። በመጨረሻ የገዛ ራሱን ልጅ ኢየሱስን ቢልከው እስራኤል እርሱንም ገደለችው።


ስለዚህም በምሳሌው እንደተገለጠው የወይኑ እርሻ ባለቤት (እግዚአብሔር) በመምጣቱ እነዚያን ክፉዎች በክፉ ያጠፋቸዋል (ማቴ. 21፥ 40) መንግሥታቸውንም ነጥቆ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣል (ቁ. 41)።


የዳግመኛ ምጽአቱ አይነተኛ ምክንያትም ይህ ነው፣ የክፉዎች ፍርድ እና የጻድቃን ብድራት።


ከላይ እንደተገለጸው፣ ከእስራኤል የተነጠቀ መንግሥትን የተቀበለው አዲሱ ሕዝብ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ተብላ የምትጠራው ናት። እንዲያውም ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ እነርሱን እንዴት እንደገለጻቸው አስተውሉ:- “እናንተ ግን [ክርስቲያኖች] ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ይላል። ይህ አገላለጽ ቀደም ሲል በዘጸአት 19፥ 5-6 ባለው ላይ እግዚአብሔር እስራኤልን የገለጸበት መንገድ ነው፡ ቅዱስ ሕዝብ፣ የካህናት መንግሥት፣ ርስት። በሌላ አነጋገር የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን አዲሷ የእግዚአብሔር ቅድስት ሀገር ናት ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን አዲሷ የእግዚአብሔር እስራኤል ናት (ገላ. 6፥ 15-16)። ምንም እንኳን ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ለመግለጥ በዚህ መጠሪያ ባይጠቀሙም ቤተ ክርስቲያን ግን የአዲስ ኪዳን እስራኤል ልትባል ትችላለች።


ይህንን አትርሱ፣ ይህ አዲስ ህዝብ በመጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብሎ የተጠራው የእምነት ማህበረሰብ ነው (የሐዋርያት ሥራ 11፥ 26)፤ እርሱም ሁለቱንም ማለትም አይሁዳውያንና አሕዛብን ያቀፈ የአማኞች ስብስብ ነው። በመሠረቱ፣ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያ በተቋቋመችበት ጊዜ፣ “የእስራኤል ልጆች ቁጥር ምንም እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን ቅሬታው ይድናል፤ ጌታ ነገሩን ፈጽሞና ቆርጦ በምድር ላይ ያደርገዋልና ብሎ ስለ እስራኤል ይጮኻል” (ሮሜ. 9፥ 27) እንደተባለ ኢየሱስን የሚያውቁ እና የተከተሉትን አይሁዶችን ብቻ ያቀፈች ነበረች።  


በመጨረሻ ግን፣ “ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፥ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፥ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል።” (ኢሳይያስ 11፥ 12፤) በሚል በብሉይ ኪዳን አንድ ቀን እንደሚፈጸም እንደተነገረው የትንቢት ተስፋ አሕዛብም ወደ ቤተ ክርስቲያን መጨመር ጀመሩ። (በተጨማሪ ኢሳ. 55፥ 5፤ 65፥ 1 ተመልከቱ)። እንግዲህ በዚህ አዲስ ህዝብ ውስጥ፣ ማለትም በቤተ ክርስቲያን፣ በአይሁድ እና በአሕዛብ መካከል ምንም መለያየት የለም (ኤፌ. 3፥ 6)። ኢየሱስ በሁለቱ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በሞቱ አፍርሶታልና (ኤፌ. 2፥ 14)። አይሁድና አሕዛብም በክርስቶስ አንድ ናቸው (ገላ. 3፥ 28)። መንግሥቱን የተቀበለውም ይህ አዲስ ሕዝብ ነው!


ብዙ ዘመን ወደኋላ ሄደን ስንመለከት ይህ ክስተት እንዴት እንደተተነበየ መረዳት አስገራሚ ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ700 ዓ.ዓ ገደማ፣ ነብዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር፡- “እግዚአብሔር አምላክ ይገድላችኋልና፣ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል።” ጌታ ኢየሱስ ስለ ክፉዎቹ የወይን አትክልተኞች በተናገረው ምሳሌ ላይ የጠቀሰውም ይህንኑ ነው፡- “ጌታ [እግዚአብሔር] እነዚያን ክፉ ሰዎች በክፉ ያጠፋቸዋል [በመምጣቱ]... መንግሥቱንም ፍሬ ለሚያፈራ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣል (ማቴ. 21፥ 41-43) ምንም እንኳን ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ባሉ ረጅም ዘመናት መካከል በኖሩ ጸሐፍያን የተጻፉ ቢሆንም፣ ለዚህን ያህል ብዙ ዘመናት እርስ በርሳቸው የማይጣረሱ በአንድነት አንድን ነገር የሚናገሩ ስሙም መሆናቸው የሚያስገርም ተአምር ነው። በተለያዩ ቦታዎች የኖሩ ጸሐፍያን የጻፉት ይህ መጽሐፍ አንድነቱና እና ወጥነቱ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እና በታሪክ ላይ የእግዚአብሔርን እጅ የበላይነት ያሳያል።


የዳግም ምጽአቱን አይነተኛ ምክንያት የሚያሳየው ሌላው የማቴዎስ ምንባብ ማቴዎስ 23፡29-36 ያለው ነው። አሁንም ኢየሱስ እየተናገረ ነው፡-


“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦ በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።” (ማቴዎስ 23፥ 29-36)


ቀደም ሲል ልክ በክፉዎቹ የወይኑ ቦታ ሰራተኞች ምሳሌ ላይ እንደተነገረው ሁሉ፣ እዚህም ላይ ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔር በየዘመናቱ የላከላቸውን ነቢያት በመቃወማቸውና በግፍ በመግደላቸው ምክንያት እስራኤላውያንን ይወቀሳቸዋል። እዚህም ላይ በድጋሚ ፍርዱ “በትውልዱ ላይ” እንደሚመጣ ኢየሱስ ተናግሯል (ማቴ. 23፥ 36) ይህም በ70 ዓ.ም ላይ የመጣባቸውን ጥፋት የሚያመለክት ነው። ይህም የተነገረባቸው “የገሃነም ፍርድ” ነው [ገሃነም በትርጉሙ ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ያለ የቆሻሻ መጣያና ማቃጠያ እንደሆነ ያምናሉ። ስለዚህ ኢየሱስ የገሃነምን ፍርድ አንስቶ ሲናገር በ70 ዓ.ም ስለተፈጸመው የጠላቶቹ መጥፋት ትንቢት መናገሩ ነው።


ጌታ ኢየሱስ በማርቆስ ወንጌል ላይ ያችን ፍሬ ያላገኘባትን በለስ ሲረግም ያህንኑ ነጥብ በድጋሚ ተናግሯል። አንድ ቀን ኢየሱስ በተራበ ጊዜ ፍሬ ወደሌላት አንዲት በለስ ላይ ቀረበና እንዲህ አላት፡- “ማንም ዳግመኛ ካንቺ ፍሬ አይብላ…” በማለዳም በዚያ ሲያልፉ ዛፊቱ ደርቃ ሞታ ነበረ። ( ማርቆስ 11፥ 14-21 ) ኢየሱስ ይህችን ዛፍ የረገመበት ምክንያት ማድረግ የሚገባትን ያላደረገች፣ ይኸውም ፍሬ የማታፈራ የማትጠቅም ዛፍ ስለሆነች ነው። ይህች ከንቱ በለስ እስራኤልን ትወክላለች (ኤር. 8፥ 13፤ ሆሴ. 9፥ 10)። የጠወለገችውም ወዲያው (በማለዳ) ነው፤ ይህም የእስራኤል ፍርድ ፈጥኖ እንደሚመጣ ያሳያል! በተጨማሪም “ከዚህ ዛፍ ፍሬ የሚበላ ማንም የለም” ሲል ኢየሱስ እንደተናገረው፣ ይህ ፍርድ በአይነቱ ዘላቂም ጭምር ነው። እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የነበራት ልዩ መብት እና ያ የከበረ ግንኙነት አሁን (ኢየሱስ ይህንን ሲናገር) ሊያከትም ተቃርቧል ማለት ነው። ይህ ኢየሱስ በነዚህ ክፉ በሆኑ የወይን ቦታ ገበሬዎች ምሳሌ ላይ ከተናገረው ነጥብ ጋር ተመሳሳይ ነው። የወይን እርሻው ባለቤት በመጣ ጊዜ “እነዚያን ክፉ ሰዎችና ከተማቸውን ያጠፋቸዋል” ሲል ተናግሯል። “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች።” ( ማቴ. 21፥ 41-43 ) እንግዲህ ልብ አድርጉ በምሳሌው የተነገሩ ሁለቱም ታሪኮች አንድን ነጥብ ያመለክታሉ፣ ይኸውም በቅርቡ በእስራኤል ላይ አይቀሬ የሆነ አስከፊ ፍርድ እየመጣ መሆኑን፣ ፍርዱም የማይቀለበስና ዘላቂ መሆኑን ነው።


አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እስራኤላውያን አሁንም እንኳ - እንዲሁም ሁልጊዜም ቢሆን በእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቡ እንደሆኑ ይከራከራሉ። እነዚህ ተንታኞች በ70 ዓ.ም ላይ የተፈጸመው ፍርድ የአይሁድ መሪዎችን ብቻ የሚመለከት እንጂ በጠቅላላው የእስራኤልን ሕዝብ (ብዙሃኑን) የሚመለከት አይደሉም ሲሉ ለመከራከር ይጣጣራሉ። ይሁን እንጂ፣ ጌታ ኢየሱስ ስለ ክፉዎቹ የወይን ቦታ ገበሬዎች በተናገረው ምሳሌና እንዲሁም በበለሲቱ ዛፍ ታሪክ ውስጥ የተናገራቸው ቃላት በግልጽ የሚያስተምሩት ስለጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ ነው።


ለዚህ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነው ኢየሱስ ተይዞ በፍርድ ችሎት ላይ በቀረበ ጊዜ የሆነውን የህዝቡን ምርጫ ተመልከቱ። ሮማዊው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ሕዝቡን (ብዙሃኑን የአይሁድን ህዝብ) በየአመቱ እንደሚያደርገው እስረኛን የመፍታት ልማድ ይህንን እድል ለኢየሱስ ሊሰጠው አስቦ ማንን ልፍታላችሁ፣ ኢየሱስን ወይንስ ታዋቂውን ወንጀለኛ በርባንን? ብሎ ሲጠይቃቸው ሕዝቡ በአንድ ድምጽ በርባንን ፍታልን ብሎ እንደመረጠ እዩ! ጲላጦስም፡- “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው” ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ሁሉም በአንድነት፡- “ስቀለው”፣ ይሰቀል! የሚል ነበር መልሳቸው። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ፡- “ለምን፥ ያደረገው ክፋት ምንድር ነው?” ሲላቸው፣ እነርሱ ግን፡- “ይሰቀል! ይሰቀል! ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን እያሉ አብዝተው ጮኹ።” (ማቴዎስ. 27፥ 15-26,)


“ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” የሚለው ይህ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ሁሉንም ጠቅልሎ ለኢየሱስ በግፍ መገደል ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፤ እንጂ ተጠያቂዎች የሆኑት የአይሁድ መሪዎች ብቻ አልነበሩም። በአጠቃላይ አይሁድ በጋራ ስምምነት የኢየሱስን ደም እዳ በምርጫቸው የወሰዱ ነበሩ! የኢየሱስ መገደል በብዙሃኑ ህዝበ ውሳኔ የተቆረጠ ነበር። ሊመጣባቸው የሚችል ፍዳም ካለ ይሁን ሲሉ በቃላቸው ፈርመዋል። ሐዋርያው ​​ዮሐንስም “የእርሱ ​​ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፤” (ዮሐንስ 1፥ 11) በማለት አይሁድ መሲሀቸውን እንዴት እንደገፉት በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። እንግዲህ ለኢየሱስ ሞት ተጠያቂው ብዙሃኑ ነው፣ በ70 ዓ.ም ላይም በማይለወጥ ቋሚ በሆነ ፍርድ የተዳኙት ብዙሃኑ ነበሩ! መንግሥቱም ከእስራኤል ተወስዶ ለሌላ ሕዝብ ማለትም ለክርስቲያኖች ተሰጠ።


ይህ ማለት ሁሉም አይሁዶች ኢየሱስን አልተቀበሉትም ነበር ማለት እንዳልሆነ ልብ አድርጉ። ከላይ እንደተገለጸው እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አይሁዶች ነበሩ። ሁሉም ሐዋርያት አይሁዶች ነበሩ። ጌታ ኢየሱስም ራሱ አይሁዳዊ ነበር። ያም ሆኖ እነዚህ ታማኝ የሆኑ አይሁዳውያን በተቀሩት አይሁድ መካከል የተገፉና ጥቂቶች ነበሩ፤ ለዚህም ነው ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን “አመንዝራ ትውልድ” (ማቴ. 12፥ 39) እና “የማያምን ጠማማ ትውልድ” (ማቴ. 17፥ 17፤ በተጨማሪም የሐዋርያት ሥራ 2፥ 40 እና ፊልጵ 2:፥ 15⁠ን ተመልከቱ) እያለ ይነቅፋቸው የነበረው። በተመሳሳይም በራእይ መጽሐፍ መልአኩ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የይሁዲነት እናት የሆነችውን ኢየሩሳሌምን የገለጸው “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት” (ራእይ 17፥ 5)፣ በማለት ነበር። ልብ አድርጉ፡- የራዕይ መጽሐፍ ኢየሩሳሌምን ሲገልጽ በተለይ “ምስጢረ ባቢሎን” እየሩሳሌም ሲል ይገልፃታል። እርስዋም ጌታ የተገደለባት ከተማ እየሩሳሌም ነበረች (ራእ. 11፥ 8)። እስራኤል እንደ ህዝብ የአመንዝራነት ሚና ነበራት፣ በታሪኳም ብዙ ጊዜ በነብያቷ “ጋለሞታ” ተብላ ስትጠራ ኖራለች። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሌሎች አማልክትን ትከተል ነበር (ሆሴ. 9፥ 1፤ ኤር. 2፥ 20-24፤ 3፥ 2-3፤ ዕዝ. 23፥ 14-20፤ ኢሳ. 23፥ 14-20፤ ኢሳ. 1፥ 21፤ 57፥ 9) ኢየሱስ ባገለገለበት ዘመንም ይሁን ራእይ በተጻፈበት ጊዜ የእስራኤል ሁኔታ እንዲሁ ነበር።


ምንም እንኳን ዘመኑ ታማኝነት ያጡ ትውልዶች የበዙበት የነበረ ቢሆንም፣ እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ ግን እግዚአብሔር ያኔም ጥቂት የታመኑ ሰዎች ነበሩት። በኖኅ ዘመን እግዚአብሔር በዚያ ክፉ ትውልድ ላይ የጥፋት ውሃ ፍርድን ሲያመጣ ጻድቁ ኖኅ እና ቤተሰቡ በጊዜው እግዚአብሔር ከጥፋት የጠበቃቸው ትሩፋን ነበሩ። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላም፣ ነብዩ ኤልያስ ብቸኛውና በህይወት የቀረው የመጨረሻው ታማኝ እስራኤላዊ እንደሆነ ባሰበ ጊዜ፣ ጌታ እንዲህ አለው፡- “በእስራኤል ዘንድ ጉልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውን ሁሉ ሰባት ሺህ ጠብቄአለሁ፣” (1 ነገ. 19፥ 18)። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመንም ጻድቃን የሆኑ ትሩፋን እነዚያ ጌታ ኢየሱስን የታዘዙቱ ነበሩ። ልክ እንደ ኖህ እና ቤተሰቡ ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖችም እግዚአብሔር ለድነታቸው ወዳዘጋጀላቸው ወደ መርከቡ ገቡ። ማለትም ኢየሱስ እንደነገራቸው በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን አጥፊ የአህዛብ ሠራዊት ባዩ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ፈጥነው እንዲሸሹ አመልክቷቸው ነበርና እንዳዘዛቸውም አደረጉ (ሉቃስ 21፥ 20-21። ራእ. 18፥ 4)። እነዚህ ክርስቲያኖች ለዚህ ሽሽትና ከፍርድ ማምለጥ ይመቻቸው ዘንድ አስቀድመው ንብረታቸውን ሸጠው ተዘጋጅተው ነበር (ሐዋ. 2፥ 45፡ ማቴ. 19፥ 21)፣ ስለዚህ ከኢየሩሳሌም የሸሹበት ሁኔታ ቅጽበታዊ ነበር። በውጤቱም ኢየሱስ በ70 ዓ.ም በክብር ደመና በመጣ ጊዜ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው አስከፊ ፍርድ ተርፈዋል።


From Blogger iPhone client