Sunday, February 2, 2025

የነገረ ፍጻሜ አቋማችን፣ ፕሪቴሪዝም!

የነገረ ፍጻሜ አቋማችን 

(ፕሪቴሪዝም)

  • መግቢያ

የአለም ፍጻሜ ቀርቦአልን? የምንኖረውስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ወይም በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነውን? የክርስቶስ መመለሻስ ቀርባልን? ከዚህስ በኋላ ቶሎ የሚሆን ይመስላችኋልን? በግምት ላለፉት 150 አመታት በምእራቡ አለም አብያተ ክርስቲያናት ያለማቋረጥ የተስተጋባ አንድ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም፣ የምንኖረው በአለቀና በተሟጠጠ ዘመን ውስጥ እንደሆነ ሲነገረን የኖረው ጉዳይ ነው። ክርስቶስም ተመልሶ ሊመጣ በደጅ እንደቀረበና ጊዜው እንደደረሰ በብዙዎች ዘንድ የተያዘ እምነት ሆኖ ኖሯል። በእኛም አገር አስራ አንደኛው ሰአት ላይ ነን የሚሉ መምህራን በየአትሮንሱ ላይ ተሰይመው ይደመጣሉ። በክርስቲያኑ ማህበረሰብ ላይ ተጭኖና ተተብትቦ ከኖረው ልማዳዊ አመለካከት የተነሳ፣ ሳይሳኩ መና ሆነው የቀሩ በትንበያ ላይ ትንበያ፣ በሃሰተኛ ተስፋ ላይ ሌላ ሃሰተኛ ተስፋ የመጨማመሩ አባዜ "አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው" ጉዳይ ነው። ከዚህ አይነቱ አዙሪት የተነሳ በርካታ የተታለሉ ክርስቲያኖች ከነዚህ አጉል ትንበያዎችና ኃሰተኛ ተስፋዎች የተነሳ ተጭበርብረው ሀብት ንብረቶቻቸውን የተዘረፉ ሲሆኑ፣ ከዚህ በከፋ ሌሎቹ ደግሞ እምነትን እስከመተው የደረሱና በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ከህይወት ቃል እስከማጉደል ድረስም መጨረሻቸው የማያምር ሆነዋል። ይህም በአብያተ ክርስቲያናት ሰፊ መሰረት ያለውና ከቁጥጥር ውጭ የወጣው የመጨረሻው ዘመን መላምታዊ አስተንትኖ ለበርካታ ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት ብዙዎችን ዳርጓል። አዘውትረው ስህተትን የሚፈልጉ አለማዊ የመገናኛ ብዙሃንም ክርስትናን የሚያሳጡበት፣ የሚያጠለሹበትንና የሚያዋርዱበትን የስድብ ምክንያት አግኝተዋል። 

በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የትንቢት አስተምህሮ ልማዳዊ አመለካከት ዙርያ በተርጓሚዎች ዘንድ አንድ የተሳሳተ ነገር መኖሩ ግልጽ ነው። ያ ችግር ምን ይሆን? እምነታችንን ከስድብና ከነቀፋ ለመከላከል ሲባል የመጨረሻው ዘመን ነገረ ፍጻሜአዊ የሆኑ አጠቃላይ ጉዳዮችን፣ የኖረውን አስተምህሮታዊ አቋምና ልማዳዊ አመለካከቶቻችንን እንደገና ማየት፣ መከለስ፣ መፈተሽና እርማት ማድረግ ለይደር የሚቀመጥ ጉዳይ አይደለም። 

መጽሐፍ ቅዱስም፦

(ማቴ 13፥ 11)"ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም" 

ይላል፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የትንቢት ቃል መረዳትና ማወቅ በእውነትም ለተጠሩትና ለተመረጡቱ የሚቻል ነው። መጻኢያን (Futurists) የሆኑ ተርጓሚዎች ግን ከሚከተሉት የትርጉም አካሄድ ስህተት የተነሳ፣ ማለትም፦ ጽንፍ በያዙበት የተዳሳሽ ወይም በቁሙ የሆነ አቀራረባቸው የተነሳ፣ በምሳሌአዊ ወይም ምስል ከሳች በሆነው ቋንቋ እና በቁሙ በሚወሰድ የቋንቋ ዘይቤ መካከል ልዩነት ለማድረግ ካለመቻላቸው የተነሳ፣ እንዲሁም የትንቢቶችን ታሪካዊ - ሰዋሰዋዊ - ባህላዊ የሆነውን አውዳቸውን (በተለይም ለበኩረ ተደራስያኖቻቸው ምን ማለት እንደነበሩ) በትክክል ወስዶ ለመተርጎም ካለመቻላቸው የተነሳ ትንቢትን በወጉ መተርጎምና መረዳት ከቶ አልሆነላቸውም። ባደመጥናቸውና የጽሁፍ ሥራዎቻቸውን ባነበብን ቁጥር ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት ዝቅ አድርገው የሚያዋርዱ ትንታኔዎቻቸውን እስክናፍር ታዝበናል። 

ከዚህም ግራ የገባው ትምህርት የተነሳ በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነገረ ፍጻሜ አስተንትኖ እርስ በርሳቸው የተለያዩ ለቁጥር የሚያታክቱ አመለካከቶች ተፈልፍለዋል። በአብዛኛው ታዋቂ ከሆኑት መካከል፦ የአልቦ ሺህ አመት መንግስት (Amillennialism) አመለካከት፣ የድህረ ሺህ አመት መንግስት (Post Millennialism) አመለካከት፣ የታሪካውያን (Historicism) አመለካከት፣ የታሪካዊ ቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Historic Premillennialism) አመለካከት፣ የዘመን ቆጣሪው የቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Dispensational Premillennialism) አመለካከት፣ የቅድመ መከራ ንጥቀት (Pre- Tribulation Rapture) አመለካከት፣ ወይም የቅድመ ቁጣ ንጥቀት (Pre Wrath Rapture) አመለካከት፣ የከፊል ንጥቀት (Partial Rapture) አመለካከት፣ በመከራው መካከል የመነጠቅ (Mid Tribulation Rapture) አመለካከት፣ የድህረ መከራ ንጥቀት (Post Tribulation Rapture) አመለካከት ወዘተ.. የሚጠቀሱት ናቸው። ማለቂያ የሌለው የነገረ ፍጻሜ የአመለካከት ልዩነቶች ቀድሞም ነበሩ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለአተረጓጎማቸው ካልተጠነቀቁ እንዲህ ያሉ የአስተምህሮ ህጸጾች ወደፊትም ይኖራሉ። ያው ዞሮ ዞሮ ግን ሁሉም ማጠቃለያቸው መጻኢነት መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉንም በተወሰነ ዝርዝር አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን የዳሰስኩበትን ጽሁፍ ሊንኩን ተጭናችሁ ልትመለከቱ ትችላላችሁ፦

https://m.facebook.comstoryphp?story_fbid=1932248943670209&id=1889309531297484

ወደተነሳሁበት ሃሳብ ስመለስ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን የምናጠናበትና የምንተረጉምበት አቀራረባችን በእውነት ትክክለኛና ተገቢ ከሆነ፣ በጣም ከባድና አስቸጋሪ የሚመስሉ ትንቢታዊ ምንባባት እንኳ መልእክታቸው ግልጽ ይሆንልናል። ስለዚህም አቋሞቻችንን እና እድሜ ጠገብ የሆኑ ልማዳዊ አመለካከቶቻችንን የምንፈትሽባቸው አንዳንድ አማራጮችን ለመመልከት አሁን ጊዜው ነው። የኃላፋውያን (Preterists) ምልከታ ደግሞ አማራጫችን ብቻ ሳይሆን እምነታችንን ከጥቃት ለመከላከልና በነገረ ፍጻሜ አስተንትኖ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሆኖ ለመገኘት በጣም ወሳኝ የሆነ አስተምህሮ ነው። በዚህ ጥናት የነገረ ፍጻሜ አቋማችንን የሚመለከት ትምህርት እንማራለን፤ ይኸውም ኃላፋዊነት (Preterism) ይሰኛል። ከዚያ በፊት ግን እስቲ በጥቂቱ ስለ ኢስካቶሎጂ እንነጋገር። እንደው ለመሆኑ ኢስካቶሎጂ ምንድን ነው? እንዴት ትገልጹታላችሁ?

  • ትርጉም

የሜሪይየም-ዌብስተር መዝገበ-ቃላት Definition of eschatology ብሎ በዚህ መንገድ ይገልጸዋል፣ እንዲህ ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፦

1ኛ በዓለም ወይም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጨረሻዎቹን ክስተቶች ወይም ኩነቶች የሚመለከት አንድ የስነ-መለኮት ጥናት ዘውግ ነው ይለዋል። [ይህ ግን ከመሰረቱ ስህተት የሆነ ትርጓሜ ነው፣ ምክንያቱም መጽሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ስለ “ዘመን” የመጨረሻ ክስተቶች እንጂ ስለ ግኡዙ ዓለም መጨረሻ አይደለምና ነው።] በመቀጠልም መዝገበ ቃላቱ 2ኛ ስለ ሞት፣ ስለ አለም ፍጻሜ፣ ወይም የሰው ልጅ የመጨረሻ እጣ ፈንታን በተመለከተ ያለ እምነት ነው ይላል፤ [ይህም ስህተት ነው፣ ምክንያቱም የዘመኑ ፍጻሜ የሚባል ትምህርት እንጂ የአለም ፍጻሜ የሚባል የነገረ መለኮት ጥናት የለምና ነው]። መዝገበ ቃላቱ አክሎም፥ በተለይ፡ ስለ ዳግም ምጽአት፣ ስለ ሙታን ትንሳኤ፣ ወይም ስለ መጨረሻው ፍርድ ማንኛውም አይነት የክርስትና አስተምህሮዎችን የሚተነትን ትምህርት ነው ይላል።

ዞንደርቫን አካዳሚክ የተሰኘ የድረገጽ መረጃ ደግሞ እንዲህ ሲል ይተረጉመዋል፣ “ኢስካቶሎጂ ስለ መጨረሻዎቹ ነገሮች ያለ ጥናት ነው። ይህም የኢየሱስን ዳግም ምጽአት የሚመለከቱ ዅነቶችን፣ ማለትም የኢየሱስ ዳግም ምጽአት ከመሆኑ በፊት የሚከናወነውን እና የኢየሱስ ዳግም ምጽአት ከሆነ በኋላ የሚከናወነውን ጉዳይ ያካትታል” ይላል። [ይህ ጥሩና ተገቢ የሆነ ትርጓሜ ነው።]

ኢስካቶሎጂ የተሰኘው ቃል የመጣው eschatos ከሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "የመጨረሻ" ወይም "የፍጻሜ" ማለት ነው፤ እሱም የነገሮችን የመጨረሻ ወይም የፍጻሜ ጥናትን ይመለከታል።

  • የኃላፋውያን አመለካከት ምንድን ነው? 

ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መጨረሻው ቀንና ስለ ፍጻሜ ጉዳዮች ያስተማሩት አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ያኔ በዚያው ትውልድና ዘመን ውስጥ ሁሉ ተፈጽሟል ብሎ የሚያምነውና የሚያስተምረው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ኃላፋዊነት (preterism) ይሰኛል። preterist የተሰኘው ቃል የተወረሰው praeter ከተሰኘው የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም "አልፎአል"፣ "አልፎ ሄዶአል" ማለት ነው። "ኃላፋዊ" ማለት የትንቢት ፍጻሜ አልፎአል፣ ካለፈም ቆይቶአል ማለት ሲሆን፤ መጻእያን ማለት ደግሞ የትንቢት ፍጻሜ ገና ወደ ፊት የሚጠበቅ ነው ማለት ነው። በመሰረቱ የኃላፋዊነት አመለካከት ማለት በሁሉ ረገድ የመጻኢነት አመለካከት ተቃራኒው ማለት ነው። መጻኢያን፣ አብዛኛዎቹ የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች (በተለይም ዋና ዋና የሆኑቱ) ገና ወደ ፊት ይፈጸማሉ እንጂ እስካሁን አልተፈጸሙም ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉም። ኃላፋውያን ደግሞ በበኩላቸው ሁሉም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች በክርስቶስና ቀጣይ በሆነው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እድገትና መስፋፋት ውስጥ ተፈጽመዋል ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉ።

ኃላፍያን የተሰኘው ስምም ሆነ ኃላፊ የተሰኘው ግስ ለኃላፊ ጊዜ አነጋገር የሚያገለግል ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የነገረ ፍጻሜ ጥናትን በተመለከተ የኃላፋውያን እይታ፣ የጌታን ዳግም ምጽአት ጨምሮ ሁሉም ትንቢት፣ የሙታን ትንሣኤና ፍርድ እኛ እየኖርንበት ካለነው ከዚህ ዘመን በፊት አስቀድሞ ድሮ ገና ተፈጽሞአል ብሎ ያስተምራል። ፕሪተርሪዝም በፍጻሜው ዘመን ሊከናወኑ በትንቢት የተነገሩ ክስተቶች ሁሉ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈጽመው እንዳለፉ የሚያምንና የሚያስተምር የኢስካቶሎጂ ምልከታ ነው። ለኃላፍዊው ነገረ ፍጻሜ ትንቢት ሁሉ ያለፈ ታሪክ ነው። ይህንንም ለማስረዳት የቅዱሳት መጻህፍትን አስተምህሮ ጠቅሶ የሚያቀርበው ማብራርያ ከየትኛውም የትርጉም መንገድ ይልቅ ጌታ ኢየሱስን እግዚአብሄር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው ነብይና እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያከብረው፣ የቅዱሳት መጻህፍትንም ተአማኒነት የሚያረጋግጥ፣ ቅዱሳት መጻህፍትም ለተሰጡበት አውድ ታማኝ ሆኖ የትርጉም ቀዋሚነትን (consistency) የሚጠብቅ እንደሆነ አይኑን ያልጨፈነ ሁሉ ሊያረጋግጠው ይችላል።  

ፕሪተሪዝም፣ የመጨረሻው ፍርድ፣ የሙታን ትንሳኤ እና የጌታ ዳግም ምጽአት እነዚህ በትንቢት የተነገሩ ትላልቆቹ ጉዳዮች በ70 ዓ.ም ላይ በሆነው በታሪካዊው የኢየሩሳሌም ጥፋት ወቅት እንደተፈጸሙ የሚገልጽ ትምህርት ነው። ፕሪተሪዝም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ መግለጫዎችን ፍፁም በሆነ ዋጋ ወስዶ ጌታ ኢየሱስ ልክ ራሱ በተናገረው መሰረትና እመለሳለሁ ባለበት ጊዜ በዚያው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በትውልዱ እንደተመለሰ ፍርጥም ብሎ ያምናል። በርካታ መጻኢያን ግን ከሚከተሉት የትንቢት ትርጉም አካሄድ የተነሳ፣ ክርስቶስ በመንግስቱ ምስረታ ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለታል ብለው በእውነት ለማመንም ሆነ ለመመስከር ይቸገራሉ።

የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት የኃላፋውያን ትርጉም ከመላው የክርስትና እምነት ጋር ተስማሚ የሆነና፣ ደግሞም ልባቸውን እልከኛ ካላደረጉ በቀር "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" (Sola Scriptura) የተሰኘውን የተሃድሶ አቋም ባነገቡ በሁሉም ቤተ እምነቶች ውስጥ ሊያዝና ሊንጸባረቅ ሰፊ እድል ያለው ደግሞም የሚችል እምነት ነው። እንደ Christianity Today, Christian News, World Magazine በመሳሰሉት እና በሌሎችም በበርካታ ታዋቂና ተነባቢ የህትመት ስራዎች ሲጠቀስ ኖሮአል። በመላው አለም በሚደመጡ የራድዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች የኃላፍያንን ምልከታ የሚያንጸባርቁ የትምህርት ስርጭቶች፣ በየወሩና በየሶስት ወሩ ታትመው ለንባብ የሚበቁ በርካታ የህትመት ውጤቶች አሉት። በርካታ የኃላፋውያን መጻህፍት፣ በራሪ ወረቀቶች፣ የቪድዮና የኦዲዮ ትምህርቶች ተዘጋጅተው የሚበዙት ስራ ላይ ውለዋል። የኃላፍያንን መጻህፍት ጽፈው የሚያዘጋጁ ጸሐፍያን በተለያዩ የሬድዮ ማሰራጫዎች እየቀረቡ ለብዙ ጊዜያት ቃለ ምልልስ ተካሂዶላቸዋል። የኃላፋውያን አመለካከት በመላው የምእራቡ አለም የሥነመለኮት መምህራንና ተማሪዎች ዘንድም ብቻ ሳይሆን፣ በክርስቲያናዊው ማህበረ ሰብ ውስጥ ወደታች ወርዶ ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ ያለና፣ በተለይ በድረ ገጽ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን (በዩቲዩብ፣ በፌስ ቡክ) እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለ ጉዳይ ነው።

  • የነገረ ፍጻሜ ትምህርት አስፈላጊነት

የነገረ ፍጻሜ ትምህርት አስፈላጊ ነው ወይ? ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ጥያቄ ከተለያዩ ሰዎች ይቀርብልኛል፤ በተለይ በነገረ ፍጻሜ ምልከታችን የተፈጸመውን ወንጌል ስናበስር እና ከተለመደው የአብያተ ክርስቲያናት የቆየ ምልከታ ጋር በአቋማችን ስንለይ የሙግታችንን ጭብጥ መመከት የተሳናቸው ወገኖች ከክርከሩ ለማፈግፈግ የሚዳዳቸው “ኢስካቶሎጂ ያን ያህል አስፈላጊ ነው ወይ?” በሚል ጥያቄ ነው። "ይህ ለምን ያስፈልጋል? የነገረ ፍጻሜ ትምህርት ለምን አስፈላጊ ይሆናል? ያን ያህል ዋነኛ ጉዳይኮ አይደለም" ሲሉም ይደመጣሉ። የእኔ መልስ ግን ሁሌም ጥያቄውን በጥያቄ የሚያስተናግድ ነው፤ "እውነት አስፈላጊ ነው ወይ?" ብዬ እጠይቃለሁ። በእውነቱ እንደዚያ ካልሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትም አያስፈልገንም ማለት ነው። ነገር ግን እውነት አስፈላጊ ከሆነ፥ እንግዲያውስ የነገረ ፍጻሜ ትምህርትም አስፈላጊ ነው።

የኢስካቶሎጂ ጉዳይ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ትልቍ ሥነ-መለኮታዊ ጉዳይ በመሆኑ ርዕሰ ጉዳዩ ዋና አስፈላጊ ጉዳይ ነው። አር.ሲ. ስፕሮል ሲያስተምሩ የአዲስ ኪዳን ሁለት ሦስተኛው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ነገረ ፍጻሜአዊ ነው ይላሉ። ሌሎች የጥናቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ደግሞ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ነገረ ፍጻሜአዊ ነው ይላሉ።

ጄምስ ቦይስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- “በመላው አዲስ ኪዳን ከሃያ አምስት ቁጥሮች ውስጥ አንዱ ቁጥር የጌታን ዳግም ምጽዓት የሚናገር ጥቅስ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሚገኙ 260 ምዕራፎች ውስጥ 318 ጊዜ የተጠቀሰው ይኸው የጌታ ዳግም ምጽአት ነው። ይኸውም የተለየ የአስተምህሮ ተግዳሮትን ከሚዳሠው ለገላትያ ሰዎች ከተጻፈው መልዕክትና፣ እንደ 2ኛና 3ኛ ዮሐንስ እንዲሁም እንደ ፊልሞና ባሉ በጣም አጫጭር በሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካልሆነ በቀር፣ በሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በሰፊው ተጠቅሷል፣ " [The Epistles of John (Zondervan), ገጽ 96]

ሬይ ስቴድማን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- “ምናልባት ይህ ርዕሰ ጉዳይ በመላው አዲስ ኪዳን ውስጥ በእጅጕ እየተደጋገመ የተጠቀሰ እውነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በማንበብ ተረድታችሁ ይሆናል። ይህ በአዲስ ኪዳናችን በሁሉም ገፆች ላይ የሚገኝ ታላቅ ተስፋ፣ እርሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም መገለጥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ሁሉንም እውነቶች አጽንቶ የሚመሰርታቸው ነው ማለት ይቻላል።

የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ልንረዳውም የሚገባን ጉዳይ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰውን እንዲህ ያለውን ጉዳይ እንዴት ቸል ልንል እንችላለን? በአዲስ ኪዳን 260 ምዕራፎች ውስጥ 318 ጊዜ የተገለጸውን ነገር ለመረዳት እንዴት አይገደንም?

  • እኔና ፕሪቴሪዝም

ከሁለት አስርት አመታት በፊት ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት እንደገና በወጉ ማሰብ የጀመርኩበትን ወቅት አስታውሳለሁ። በጊዜው በመካነ የሱስ ሴሚናሪ የስነ መለኮት የማታው ትምህርት ፕሮግራም እየተከታተልሁ ቄስ ሆኜ እንዳገለግል በጠራችኝ ማሕበረ መእመናን ወንጌልን አገለግል ነበር። የኖርኩበት ሉተራዊ እምነቴ በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮቱ የአልቦ ሺህ አመት አመለካከትን እንደሚቀበል እረዳ የነበረው በጥቂቱ ቢሆንም፣ በመላው የአገራችን ቤተክርስቲያን የናኘው የዘመን ቆጣሪያን (Dispensationalist) አመለካከት ግን ተጽእኖ አሳድሮብኝ ኖሯል። ነገረ ፍጻሜም ያን ያህል የሚያሳስበው ባልሆነ ማህበረ ሰብ መካከል በመኖሬ በግሌ የተፈጠሩብኝን በርካታ ሥነመለኮታዊና መጽሓፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎቼን ማስተንፈስ የምችልበት እድልና ሁኔታ አልነበረኝም። በሴምናሪ በነበረኝ ቆይታም በቤተ መጻህፍቱ ለመጠቀም በነበረኝ ዕድል በውስጤ ይላወስብኝ ከነበረው እረፍት አልባ ሙግት ጋር የሚፋጠጡ መጻህፍትን ለማንበብ ሞክሬአለሁ። የሉተራውያኑም የነገረ ፍጻሜ አቋም ሊሻል ይችላል ብዬ አርፌ በተቀመጥኩበት አንድ አጋጣሚ ግን አንድ ወዳጄ የወንጌላዊ ጆን ኤል ብሬይን “Jesus is Coming soon” የተሰኘች አንዲት ትንሽዬ ቡክሌት አዋሰኝና አነበብኳት። እጥር ምጥን ብላ የተዘጋጀችው ያቺ ቡክሌት ልቋቋመው የማልችለውን ብርቱ ሙግት ብትገጥመኝም ወንጌላዊው የሚያስተምሩትን ጉዳይ የበለጠ ለማወቅ ግን ረሃቤን ቀሰቀሰችብኝ። ቡክሌቷ ላይ ባገኘሁት መረጃም ከሚልተን ተሪ ጋር ተዋውቅሁ፤ ወደቤተ መጻህፍት ሄጄም ስጎረጉር አቧራ የጠገበና ብዙም ሳይነበብ መደርደሪያው ላይ የተረሳ “Biblical Apocalyptics” የተሰኘ ዳጎስ ያለ ጥራዝ አግኝቼ በውሰት ወሰድኩትና ያን ሁሉ ገጽ ፎቶ ኮፒ አስደርጌ በርጋታ ማንበቤን ቀጠልሁ፤ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ትንቢትን ለመረዳት ከዚህ በፊት ያልነበረኝን ጥልቅ ፍላጎት ያጫረብኝ ከመሆኑም በላይ የቀደመውን አመለካከቴን እና አስተሳሰቤን መለወጥ አስችሎኝ ነበር።     

ቀድሞ በነበረኝ መረዳት እንደ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች፣ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ምድርን የሚቀይር አካላዊና ተዳሳሽ ክስተት ነው ብዬ አምንም እጠባበቅም ነበር። ይኸውም የዚህ የምናውቀው ተዳሳሽ ዓለም ፍጻሜ፣ አስደንጋጭ የምድር ቃጠሎ፣ አጠቃላይ የሕይወት ውድመት ሆኖ ይታየኝ ነበር። አስተሳሰቤን የለወጠው ግን የዳግም ምጽአቱን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ የአዲስ ኪዳን ምንባባት ናቸው። ብበመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴም የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻህፍት ስለ ዳግም ምጽአቱ በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ “ጊዜ ጥቋሚ” የሆኑ ንግግሮችን እንደሚጠቀሙ በጉልህ ማየት ጀመርኩ። ዳግመኛ ምጽአት በእነዚያ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩ አማኞች የሕይወት ዘመን፣ እንዲያውም በዚያ ከኢየሱስ ጋር ቆመው የነበሩት አንዳንዶቹ ገና በሕይወት እያሉ (ማቴ. 16፥ 28) ተፈጽሟል፣ ሆኗልም ብዬ እንዳምን የሚያስገድዱኝን የቅዱሳት መጻህፍት ቃላት ለዘመናት ከያዝኩትና በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከሚታወቀው የተለመደ ትምህርት በላይ ማክበር ነበረብኝ። እነደ አዲስ ኪዳን ትምህርት ከሆነ፣ ያ የኢየሱስ ትውልድ ገና ሳያልፍ፣ ለዚያው ትውልድ ቅርብ በነበረ መጨረሻ ኢየሱስ ለእነርሱው ቶሎ ይመጣል ብሎ ለማመን የሚያስችለኝን እውነት ማየት የቻልኩትን ያህል፣ ኢየሱስ አሁን በእኛ ዘመነም ይሁን ገና ወደፊ ተመልሶ ይመጣል በሚል አምነው የነበረው አስተሳሰቤን የሚደግፍልኝ አንድም ጥቅስ ማግኘት ተሳነኝ።

  • አውደ ምንባባዊ አግባብ

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ የበኩረ ተደራስያኑን አውድ ዋጋ የሚሰጥ የትርጉም መርሆን በአእምሯችን መያዝ አለብን። ይህ አስፈላጊ አካሄድ እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ተደራስያን አንድን የንባብ ክፍል ምን ማለት እንደሆነ በአውዳቸው የተረዱበትን መንገድ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። ወንጌል አማኝ የሆነ የቅዱሳት መጻህፍት ተርጓሚ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ የአንድን የንባብ ክፍል ሰዋሰው ከበኩረ ተደራሲያኑ ታሪካዊ ሁኔታዎች እና ከአውዳቸው አንፃር መረዳት ነው።

የዳግም ምጽአቱ ጊዜ ያኔ ገና በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ “ቅርብ” ነው ከተባለ፣ “ቶሎ” ነው፣ “በደጅ ነው” ከተባለ፣ እንግዲያውስ የዳግም ምጽአቱ ተፈጥሮ ሥጋዊ፣ አካላዊና ተዳሳሽ መሆን የለበትም። ይህንንም የምናውቀው አካላዊና ተዳሳሽ ለውጥ ባለመኖሩ ነው። ለምሳሌ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ላይ፣ ዳግም ምጽአቱን በተመለከተ የሚናገረው ሥጋዊ ወይንም ተዳሳሽ በሆነ መልኩ አድርጎ እንዳልነበር እናያለን። አንዳንድ አውድ ለማግኘት ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የጻፈውን ሁለተኛ መልእክት በመጠኑ ማየት እንጀምር።

2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 4 “ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን”

ጳውሎስ ይህንን መልእክት በተሰሎንቄ ላለች ቤተ ክርስቲያን በ50-51 ዓ.ም. በጻፈበት ጊዜ፣ የተሰሎንቄ አማኞች በክርስቶስ ስላላቸው እምነት መከራ ይቀበሉ የነበረበት ጊዜ ነው። ስለዚህም ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያጽናናቸዋል።

2ተሰሎንቄ 1፥ 6-8 “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤”

ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ሲገለጥ (ማለትም፣ ዳግም ሲመጣ) ያኔ እረፍትን ሊያገኙ ነው። The NIV Cultural Background Study Bible የተሰኘ የማጥኛ መጽሃፍ የዚህን ደብዳቤ ጭብጥ ሲያብራራ፡- “ከአዲሶች አማኞች ጋር በአካል አብሯቸው መሆን ያልቻለው ጳውሎስ እምነታቸውን በዚህ ቃል ያበረታታል፣ እንዲሁም የክርስቶስን መምጣት በቅርቡ በመመልከት ተስፋቸውን ያጠናክራል” ይላል።

ይህ ደብዳቤ የተፃፈው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በተሰሎንቄ ለነበሩና መከራን እየተቀበሉ ላሉ አማኞች ነው፣ እነርሱም በዳግመኛ ምጽአት ጊዜ ስለሚቀቡሉት እረፍት ተስፋቸውን የሚነግራቸው ቃል ነው። እንግዲህ የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ገና አሁንም ወደፊት የሚጠበቅ ከሆነ፣ ይህ ተስፋ ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በከባድ መከራ ውስጥ እያለፉ ለነበሩት በተሰሎንቄ ላሉት አማኞች እረፍትን ሊሰጣቸው የሚችለው እንዴትና በምን አግባብ ነው? እነዚያ አማኞች እረፍታቸው በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ብቻ ነበር። ክርስቶስ ስላልመጣ እነርሱ እስካሁን አላረፉም ማለት የነበራቸውን ተስፋ ሃሰተኛ ተስፋ አያደርገውምን? ቀጥሎ ጳውሎስ፦ 

2ተሰሎንቄ 2፥ 1-2 “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።” ይላል

ጳውሎስ በምዕራፍ 1 ላይ ስለ ዳግም ምጽአቱ እየተናገረ ነበር፣ አሁን ደግሞ “ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት” ይላል። አሁንም ከዚያው ርዕሰ ጉዳይ ሳይወጣ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ መናገሩን እንደቀጠለ ነው። The Complete Jewish Bible ቁጥር 2 ላይ ያለውን በዚህ መንገድ ያስቀምጣል። “not to be easily shaken in your thinking or anxious because of a spirit or a spoken message or a letter supposedly from us claiming that the Day of the Lord has already come” (ሲተረጎምም፣ “የጌታ ቀን መጥቶአል በምትል ከእኛ በተጻፈች መልእክት ወይም በሐሳባችሁ በቀላሉ አትናወጡ ወይም አትጨነቁ” የሚል ነው።) ሕያው ቃል አዲስ ኪዳን ትርጉምም “አንዳንድ ሰዎች ጊዜው ደርሷል በማለት በሚያወሩት ወሬ አትታወኩ፣ ሥጋትም አይግባችሁ” ይለዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጉምም “የጌታ ቀን ደርሷል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሮአችሁ አትናወጡ፣ አትደንግጡም” ይለዋል።

እንግዲህ እነዚያ የተሰሎንቄ ሰዎች የዳግመኛ ምጽአት ተፈጥሮው ምድርን ቡን አድርጎ የሚያቃጥል፣ ምድርንም ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ አይነት አመጣጥ ነው ብለው የሚያምኑ ከነበሩ፣ም ይህ ሁሉ የምድር ውድመት ሳይሆን በፊት “መጥቶአል” በሚል ቃል ስለ መምጣቱ እንዴት ሊታለሉ ይችላሉ? የዳግም ምጽአቱ ተፈጥሮ ዛሬ ብዙዎች እንደሚመለከቱትና እንደሚጠባበቁት አይነት ከሆነ፣ ጳውሎስ ምን ብሎ ሊጽፋቸው ይችል እንደነበር አስቡ፡- “እስቲ በመስኮት ተመልከቱ፣ ምድር እንደሆነ አሁንም አለች፣ ገና አልጠፋችም፤ ስለዚህም ጌታ አልመጣም ማለት ነው”። እነዚያ የተሰሎንቄ ሰዎች የጌታ ቀን አስቀድሞ የሆነ መስሏቸው ስለነበር ዛሬ ብዙዎቹ ሰዎች ከሚያዩበት በተለየ መልኩ ሳይመለከቱት አልቀረም። በዚህ ትስማማላችሁ? ለዚህ ምድር ፍጻሜ የሚሰጥ የዳግም ምጽአት ምሳሌ የሌለ መሆኑን ለማሰብ በጥቂቱ መፍቀድ ከቻልን፣ ምናልባት የዳግመኛ ምጽአቱን መጽሓፍ ቅዱሳዊ እውነታ መረዳት ልንጀምር እንችላለን።


መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እኛ ካለንበት ዘመን ራቅ ባለ ጊዜ እና ለእኛ እንግዳ በሆኑ ባሕሎች ውስጥ እንደተጻፈ መረዳት አለብን። ጸሐፊው ምን እያለ እንደሆነ የንግግሩን ትርጉም ለማወቅ በምንሞክርበት ጊዜ፣ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች እንደ አንዱ ሆነን ጽሑፎቹን ማንበብና መማር አለብን። ይህንንም ለማድረግ እነርሱ ታናካህን (የአይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍትን) እንደሚረዱት ሆነን መረዳት አለብን። ለምሳሌ፣ ራዕይ 1ን እንመልከት።

ራእይ 1፥ 7 “እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።”

አብዛኞቹ የዘመናችን ክርስቲያኖች ይህንን አይነቱን አመጣጥ እንደ አካላዊና ተዳሳሽ መምጣት አድርገው ይመለከቱታል። ታናካህን (የአይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍትን) ግን የምናውቅ ከሆነ ግን ከዚህ በተለየ ጌታ ብዙ ጊዜ በደመና ላይ ተቀምጦ የሚጋልብ እነደሆነ እናውቃለን (ለምሳሌ፣ መዝሙር 18፥ 7-15፤ 68፥ 4፤ 104፥ 3፤ እንዲሁም ናሆም 1፥ 3 ተመልከቱ)። መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ምስል በጥንታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ግንዛቤ ውስጥ አድርገን ስንመለከተው፣ የእግዚአብሔር ደመና እርሱ የሚጋልበው ሰረገላው እንደሆነ እንገነዘባለን። ተመልከቱ፦

ኢሳይያስ 19፥ 1 “ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል”

እግዚአብሔር አሦራውያንን በግብፅ ላይ የቁጣው መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመባቸውና እንዳመጣባቸው ከምዕራፍ 20 እናውቃለን፣ ነገር ግን ይህንን ፍርድ “እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጧል… ግብጽም በፊቱ ትንቀጠቀጣለች” በሚል አገላለጽ ያቀርበዋል። አዎ እግዚአብሔር ለፍርድ ወደ ግብፅ መጥቷል። ዳሩ ግን በአካልና በተዳሳሽ መልኩ ነው ወደ ግብፅ የመጣው? በጭራሽ አይደለም። ታዲያ እንዴት ነው ወደ ግብፅ “የመጣው"? በፍርድ መጣ፣ ማለት መገኘቱ በፍርዱ ታወቀ ማለት ነው። ነገር ግን ቃል በቃል በዚያ የተገኙት የእግዚአብሔር የፍርድ መሳሪያዎች ግን አሦራውያን ነበሩ።

ልክ እንደዚሁ፣ አዲስ ኪዳንም ኢየሱስ በደመና ላይ ሲመጣ ያለው ስዕል፣ ይህ ተፈጥሮአዊ የዝናብ ክምችት በሰማይ ላይ የሚፈጠረው ነጭ፣ ለስላሳና የጥጥ ባዘቶ መሳይ የደመና ክምችት እንዳልሆነ እንረዳለን። ከዚህ ይልቅ ግን በተቃራኒው በፍርድ የሚገለጥበትን የጭፍራ ማዕበል የሚወክል ደመና ነው። ታናካህን (የአይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍትን) የበለጠ በተረዳን መጠን በዚያው ልክ የአዲስ ኪዳንን ቋንቋ በደንብ እንረዳለን።

  • የምጽአቱ ጊዜ እና ተፈጥሮው

የጌታ ዳግም ምጽአት ተስፋ ለተሰጣቸው ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በትውልዳቸው ወስጥ ቶሎ ለመፈጸም የተቀጠረ ከሆነና ጌታችንና ሐዋርያቱ ዳግመኛ ምጽአቱ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ እንደሚሆን በግልጽ ካስተማሩ እንግዲያውስ የዳግም ምጽአቱ ተፈጥሮ ሥጋዊ አካላዊና ተዳሳሽ ሳይሆን መንፈሳዊ መሆን አለበት ማለት ነው። አዲስ ኪዳንም ስለክርስቶስ መምጣት መቃረብ እንደሚናገር ግልጽ ነው።

አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የምድርን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያመለክታል ብለው የሚያስቡት የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ መጽሐፍ በተለይ የዮሓንስ ራዕይ መጽሐፍ ነው። ነገር ግን መጽሐፉ በትክክል ለሚናገረው ነገር ትኩረት ሰጥታችሁ ብትከታተሉት፣ በግልጽ የሚናገረው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሊሆኑ ስላሉ ነገሮች እንደሆነ ግልጽ ይሆንላችኋል።

ራእይ 1፥ 1-3 “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።”

የራእይ መጽሐፍ በቀጥታ የተጻፈው ለማን ነው? ዛሬ ዛሬ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በቀጥታ ለእነርሱ የተጻፈላቸው ይመስላቸዋል። ልክ አሁን የደረሰ ትኩስ ዜና እንደሚያስነብብ ጋዜጣ ነው የሚመለከቱት። ነገር ግን ዮሐንስ በትንሿ እስያ ያሉትን ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ጠቅሶ ለማን እንደጻፈው በግልፅ ይነግረናል።

ራእይ 1፥ 4-5 “ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን”

እነዚህ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በትንሿ እስያ የነበሩ ሰባት እውነተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ። በምዕራፍ 1 ላይ ሰባቱንም አብያተ ክርስቲያናት በስም ይጠቅሳቸዋል።

ራእይ 1፥ 10-11 “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ እንዲሁም፦ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ።”

አስተውሉ ዮሐንስ በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ በአዲስ አበባ ለምትገኝ ለየትኛዋም ቤተክርስቲያን መለልእክት እንዲልክ አልተነገረውም። ይህ መጽሐፍ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በትንሿ እስያ ላሉ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የተላከ ለመሆኑ የደብዳቤው ተቀባዮች የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናት በስም ጠቅሷል። ለምሳሌ

በትያጥሮን ላለችው ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር።

ራእይ 2፥ 25 “ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ”

ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን ይኖሩ የነበሩትን አማኞች “እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ” ብሏቸዋል። ቋንቋውን ካላወሳሰብነው በቀር “እስክትሞቱ ድረስ አጥብቃችሁ ያዙ” ጨርሶ አይልም። ቋንቋው ለማንኛውም ትርጉም የተጋለጠና እኛን የመሰለንን የትኛውንም ነገር ማለት ከሆነ እንግዲያውስ ይህ በየትኛውም የሕይወት ዘመን ውስጥ እርሱ ይመጣል ማለት ይሆናል፣ ይህ ግን እንደርሱ ማለት አይደለም? ራዕይን እንተነትናለን የሚሉ አብዛኞቹ ተንታኞች የበኩረ ተደራስያኑን አስፈላጊነት እና አግባብነት ያለውን መሠረታዊ የትርጓሜ መርሆ ብዙ ጊዜ ሲጥሱ ይደመጣሉ። 

በራዕይ 1፥ 1 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው፣ ዮሐንስ በተለይ የራዕዩ ትንቢቶች መፈፀም የሚጀምሩት በ”ቶሎ” እንደሆነ ተናግሯል።

ራእይ 1፥ 1 “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥”

ይህንን በቶሎ የተሰኘ እውነታ በተለያዩ መንገዶች ተመሳሳይ ቋንቋን እየተጠቀመ አጽንኦት ይሰጠዋል። ተመልከቱ በጉዳዩ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ግራ መጋባት ለማስወገድም የአገላለጾቹን መንገድ በጥንቃቄ ይለዋወጣል። በራእይ 1፡1 ላይ “ቶሎ” በሚል የተተረጎመው የግሪክ ቃል ‘tachos’ ይሰኛል። እንደ አርንድት እና ጊንሪች ሌክሲከን (የግሪክ መዝገበ ቃላት)፣ይህ ‘tachos’ የተሰኘ ቃል በሰባ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን ትርጉምና በአንዳንድ ቀኖናዊ ባልሆኑ ጽሑፎች ውስጥ “ፍጥነት፣ ፈጣንነት፣ ፍጡንነት፣ ችኩልነት” በሚል አግባብ ጥቅም ላይ ውሏል። ዮሐንስም በራዕይ 2፥ 16; 3፥ 11; 22፥ 6፣ 7፣ 12፣ 20 የተጠቀመው ተመሳሳዩን ቃል ነው። ዮሐንስ በራእይ 1፥ 3 እና 22፥ 10 ላይ “ቀርቧል” ተብሎ ለተተረጎመው ቃልም ‘engus’ የተሰኘውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። 

ራእይ 1፥ 3 “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው”

ይህ ቃል የሚያመለክተው ጊዜያዊና ወቅታዊ መቃረብን ነው። ዮሐንስ የመጽሐፉን መልዕክት ለማያያዝ ይጠቀምበታል። በመጽሐፉ ውስጥ የምናየው ጊዜ አመልካች የሆነው ሦስተኛው የግሪክ ቃል ‘mello’ ነው። ይህም በራዕይ 1፥ 19 እና 3፥ 10 ላይ “ሊሆን ያለው” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ በምዕራፍ 1፥ 19 ላይ ያለው ሀረግ፡ ፊት ለፊት ባለው ትርጉሙ በጊዜው ቅርበትና በዚያ አይነተኛ ወቅት ውስጥ “ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮች” መሆኑን ያመለክታል። 

ራእይ 1፥ 19 “እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ”

ይህ ሜሎ የተሰኘው ቃል በራእይ 3፥ 10 ላይም በድጋሚ ይከሰታል፤ እንዲህ ሲል፦

ራእይ 3፥ 10 “የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።”

“በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ያለው” የሚለው የአማርኛ አረፍተ ነገር ‘ሜሎ’ የተሰኘውን የግሪክ ቃል በመተርጎም ረገድ ምናልባትም ከአንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች በተሻለ ይገልጠዋል። ቃሉን ስንተረጉም የቡኩረ ተደራስያኑን አግባብነትና ጠቀሜታ የትርጉም መርህ በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለን እነዚያ የመጀመሪያዎቹ የመልክቱ አንባቢዎች ይህንን ቃል ሲያነቡ ምን ሊያስቡ እንደሚችሉ እናስተውል ነበር። ዮሐንስ እነዚህን ቃላት በመጽሐፉ መግቢያና በመደምደሚያው ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞባቸዋል። ዮሐንስ ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት ሲያስጠነቅቅ እነዚህ ይፈጸማሉ፣ ይሆናሉ የተባሉ ነገሮች እነርሱ በነበሩበት ወቅትና አውድ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችሉ እንደሆነና ተግተው እንዲጠብቁአቸው እየነገራቸው ነበር። ይህንን ‘mello’ የተሰኘው የግሪክ ቃል ከትንቢት ፍጻሜ ጠቀሜታው አንጻር በዝርዝር የተመለከትንበትን ጥናት ማንበብ ቢያስፈልጋችሁ በብሎገሬ የተለጠፉውን ጽሁፍ እንድታዩ እጋብዛለሁ፤ ሊንኩም፦ https://gizachewkr.blogspot.com/2021/09/blog-post_26.html?m=1

ስለዚህ፣ በእነዚህ ጊዜ ጠቋሚ በሆኑ መግለጫዎች እና ሌሎች በርካታ ነገሮች ላይ በመመስረት፣ ኢየሱስ እንደተናገረው ተመልሶ የመጣው በ70 ዓ.ም ላይ እንደሆነ ለማስተዋልና እንደዚያ ለማመን አይጎረብጠንም። ከፊል ሀላፋውያን ይህንን የ70 ዓ.ም መምጣት ከመምጣቶች አንዱ እንደሆነ እንጂ እውነተኛውና የመጨረሻው የትንቢት ፍጻሜ የሆነው ዳግመኛ ምጽአቱ እንደሆነ ለማመን ስለሚቸግራቸው አሁንም ገና ወደፊት የክርስቶስን ዳግመኛ መምጣት ይጠባበቃሉ። ነገር ግን ይህ በራእይ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ተመሳሳይ ጊዜ ጠቋሚ የሆነው ቃል በመጽሐፉ መጨረሻም ላይ ጥቅም ላይ መዋሉን ማስተዋል ከቻሉ መጽሐፉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያወራው ስለ አንዱ ፍጻሜና ስለ አንዱ ምጽአት እንደሆነ ማየት ይችላሉ። ተመልከቱ በመጽሐፉ መዝጊያም ላይ እንዲህ ይላል፦

ራእይ 22፥ 6-7 “እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።”

ራእይ 22፥ 10 “ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።”

ራእይ 22፥ 12 “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።”

በመጨረሻዎቹ 16 ቁጥሮች ውስጥ ብቻ በትንሿ እስያ ላሉ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በቅርቡ ወደ እነርሱ እንደሚመጣ አምስት ጊዜ ያህል እያከታተለ ይነግራቸዋል። ከፊል ሀላፋውያን ይህ እንደሚያስቸግራቸው ግልጽ ነው። እኔም ብሆን ከፕሪቴሪዝም ጋር ስተዋወቅ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት አመታት ይህንን በእግዚአብሔር ቃል ማየት ስለተሳነኝ ሙሉ ሀላፋዊነትን ለመቀበል ያስቸግረኝ ነበር። አንዱም ምክንያት እንደዚህ የሚያምንና የሚያስተምር ሌላ ሰው አለማወቄ ነበር

ደግሜ እላለሁ፣ እነዚህ የመጨረሻዎቹ ጥቅሶች ለከፊል ሀላፋውያን በጣም ከባድ መሆን አለባቸው። ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ እነዚህ መግለጫዎች ጠቅላላውን ይህንን መጽሐፍ በቅንፍ የሚያደርጉት ሲሆን፣ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ነገሮች ማለትም ዳግም ምጽአትን፣ አጠቃላዩን ፍርድንና የሙታን ትንሳኤን ሁሉ ያጠቃላሉ። ለነዚያ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ተደራስያን ሁሉም ነገር በቅርቡ የሚፈጸሙና በትውልዳቸው ቀነ ቀጠሮ የተያዘላቸው ነበሩ። ከፊል ሀላፋውያንን የሚገልጽ አንድ ቃል ይገኝ ከሆነ ያው መጻኢነት ነው። ከፊል ሀላፋውያን ማለት እነርሱም ጠባቂ መጻእያን ናቸው። 

  • የጥንት ክርስቲያኖችና ምጽአት

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ የበኩረ ተደራስያኑን አውድ ያገናዘበ የትርጉም መርሆን በአእምሯችን መያዝ አለብን። መፅሃፍ ቅዱስ "ለእኛ" (for us) ተብሎ እንደተፃፈ መረዳት አለብን እንጂ በቀጥታ "ለእኛ" (to us) አልተጻፈም። የትኛውም የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባብ ከሁሉ አስቀድሞ ለበኩረ ተደራሲያኑ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አጥብቀን መፈለግ አለብን፤ ከዚያ በኋላ የህይወት ተዛምድውን ወስደን በራሳችን ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። 

የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ በእነርሱ የህይወት ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የነበራቸው መጠባበቅና፣ ይህንን አይነት መጠባበቅ እንዴት ሊኖራቸው እንደቻለ፣ ከየትስ እንዳገኙት ሁልጊዜ ሲያስገርም የሚኖር ጉዳይ ነው። ለጥንት ቤተክርስቲያን ሰዎች ክርስቶስ በትውልዳቸው ተመልሶ እንደሚመጣ በቃል የተነገራቸውም ሆነ በመልእክት የተጻፈላቸው ቃል በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ንግግርና ጽሁፍ የሆነውን ያህል፣ እንዲሁ እነዚያው የጥንት ክርስቲያኖች የጌታን ቀን ይናፍቁና ይጠባበቁ የነበረበት ያ ተስፋ፣ እምነትና ናፍቆት በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ነበር። ክርስቶስ ተመልሶ የሚመጣው መቼ እንደሆነ ክርስቶስ ራሱና ሐዋርያቱ ተናግረው ነበር ወይ? ታዲያ መቼ ነው ተመልሶ ይመጣል ያሉት? 

ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥቅሶች ስትመለከቱ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችሁን ጠይቁ፡ ይህ የተፃፈው ለማን ነው? መቼስ ነው የተጻፈው? እነርሱስ ክርስቶስ መቼ ይመጣል ብለው ጠብቀው ነበር?

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦

ማቴዎስ 10፥ 23 “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።

ማቴዎስ 16፥ 27-28 “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።”

ማቴዎስ 24፥ 34 “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።

ኢየሱስ ለጴጥሮስ ይህንን ብሎት ነበር፦

ዮሐንስ 21፥ 21-22 “ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው። ኢየሱስም፦ እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው።”

ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ይህንን ብሎ ነበር፦

ሮሜ 13፥ 11-12 “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።”

ሮሜ 16፥ 20 “የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስትያኖች እንዲህ ብሎ ነበር፦

1ቆሮንቶስ 1፥ 7-8 “እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል።”

1ቆሮንቶስ 7፥ 29-31 “ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”

1ቆሮንቶስ 10፥ 11 “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።

1ቆሮንቶስ 15፥ 51-52 “እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።

እዚህ ላይ “እኛ” የተባሉት ጳውሎስ እና በቆሮንቶስ የነበሩ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመንአማኞች ናቸው። 

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችም ይህንን ይላል፦

ፊልጵስዩስ 1፥ 6 “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤

ፊልጵስዩስ 4፥ 5 “ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው።”

ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩ ክርስቲያኖችም ይህንን ይላል

1ተሰሎንቄ 4፥ 15 “በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤

1ተሰሎንቄ 5፥ 23 “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስም እንዲህ ብሎታል፦

1ጢሞቴዎስ 6፥ 14 “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤

ጳውሎስ ለቲቶም እንዲህ ብሎት ነበር፦

ቲቶ 2፥ 12-13 “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤

ጳውሎስ ለእብራውያን ክርስቲያኖችም እንዲህ ብሏቸው ነበር፦

እብራውያን 9፥ 28 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።”

እብራውያን 10፥ 37 “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤

"ገና ጥቂት ጊዜ ነው" የሚለው እዚህ ላይ ያለው የግሪኩ አገባብ በጣም ገላጭ እና አጽንዖት የሚሰጥ ንግግር ነው። ጸሐፊው በንግግሩ “ጥቂት” ሲል “ሊመጣ ላለው”፣ “ለሚመጣው” ጉዳይ በልዩነት የቀረ “ትንሽ ጊዜ”ን የሚያመለክት ቃል ተጠቅሟል፤ ነገር ግን ይህንን የቀረ በጣም ትንሽ ጊዜ የበለጠ አጽንዖት ሲሰጠው “በጣም” የሚልን አጠናካሪ ተቀጥላን ያያይዛል። ትርጉሙም ላቅ ያለ ነውና “በጣም” በማለቱም የቀረውን ጊዜ አጭርነት የበለጠ አጠናክሮታል። ስለዚህም ይህንን ሐረግ ቃል በቃል፡- “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ አለ፥ የሚመጣውም ይመጣል” ሲል ይገልጸዋል። ይህም “ለሚጠባበቁት” ወይም ይጠባበቁት ለነበሩት ነው።

ጴጥሮስም ለክርስቲያኖች ሲጽፍ የሚከተለውን ይላል፦

1ጴጥሮስ 1፥ 13 “ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።

1ጴጥሮስ 4፥ 7 ”ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥”

1ጴጥሮስ 4፥ 17 “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?

እነዚህ ጥቅሶች የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ከኢየሩሳሌም ውድቀት፣ ከቤተ መቅደሱ ውድመት፣ እንዲሁም በ70 አ.ም ላይ ከሆነው የአይሁድ ህዝብ እልቂትና የብሉይ ኪዳን የመስዋዕቱ ስርዓት ፍጻሜ ጋር ባለው ግንኙነት አንጻር የሚናገሩና የሚያስተምሩ ናቸው። እነዚያ የቤዛነት ትእይንት የመጨረሻ ኹነቶች ልክ እርሱ ይሆናሉ ሲል እንደተናገረው ተፈጽመው አልፈዋል፣ ስለዚህ ጊዜን አመልካች የሆነውን የትንቢቶቹን አቀራረብ ቸል ብሎ፣ "ትንቢቱ ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስከ አሁን ገና አልተፈጸመም" ሲል፣ ሳይፈጸም እንደቀረ ወይም እንደዘገየ የሚያስተምረውን እድሜ ዘልዛላ አመለካከት ለማብራራትም ሆነ ለመተንተን መሞከር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ ጊዜው ያለፈበትና ምንም አስፈላጊነት የሌለው ነው።

ይልቁን ግን በኩረ ተደራስያኑ አንድን የንባብ ክፍል ምን ማለት እንደሆነ የተረዱበትን መንገድ ለማወቅ አውዳቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። ጌታ ለእነርሱ በቅርቡ እንደሚመጣ ተናግሯል፣ ስለ መምጣቱም ሲናገር እነሆ "በደጅ" ነው ብሏል። ስለዚህ የሚመጣው ወይም ሊመጣ ያለው በእነዚያ በሚናገራቸው ሰዎች የሕይወት ዘመን ነው ማለት ነው። "በትውልዳቸው ውስጥ" እንደሚመጣ ተናግሯቸዋል። ክርስቶስ በዘመናቸው በቅርቡ ተመልሶ ለመምጣት የሰጣቸውን ተስፋ እና እነርሱ የነበሩበትን የመጠባበቅ ሁኔታ፣ በመንፈስ ቅዱስም የተመራውን ናፍቆታቸውን አጥርታችሁ ሳታዩ አዲስ ኪዳንን ማንበብም ሆነ መረዳት አትችሉም። ለብዙዎች ችግር የሚፈጥርባቸውም ይህ ነው። ይህንንም ባለመረዳት በሥነ ፍታቴአቸውና እንከተለዋለን በሚሉት ሥነመለኮት ላይ ባቆሙት የነገረ ፍጻሜ አስተንትኗቸው ጌታ ኢየሱስን እና የአዲስ ኪዳን ጸሃፍያንን ለከሃዲያን ስድብ አሳልፈው ይሰጣሉ። 

ያዕቆብን ደግሞ ስሙት፦

ያዕቆብ 5፥ 7-9 “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።”

በኩረ ተደራስያኑ በቀጥታ ለእነርሱ የተጻፈላቸውን ጉዳይ የያዘ አንድን የንባብ ክፍል ምን ማለት እንደሆነና ምን ትርጉም እንደሰጣቸው እነርሱ የተረዱትን ለማወቅ የጽሁፉን አውደ ምንባብ እና የበኩረ ተደራሲያኑን አግባብነት ማስታወስ አለብን። ጌታ ቶሎ እንደሚመጣ ነግሯቸዋል፤ የእርሱ መምጣትም "በደጅ" መሆኑን ነግሯቸዋል፣ ሊመጣ ያለውም እነዚያ እርሱ የሚናገራቸውና ንግግሩን ቆመው ይሰሙ በነበሩ ሰዎች የሕይወት ዘመን መሆኑን ነግሯቸዋል። "በትውልዳቸው" እንደሚመጣም ነግሯቸዋል። እንግዲህ እነርሱ አዲስ ኪዳንን የጻፉልንና መልእክቶቻቸውን ያነበቡ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት የነበራቸውን የቅርብ ጊዜ ተስፋ እና ያንን በመንፈስ ቅዱስ የተመራ መጠባበቅ አጥርታችሁ ሳታዩ አዲስ ኪዳንን ማንበብም ሆነ መረዳት አትችሉም። ለብዙ ወዳጆቼ ችግር የሚፈጥርባቸው ይህ እንደሆነ እረዳለሁ። 

  • የክህደት ጥግ

በዚያው ትውልድ ውስጥ ለመመለስ የሰጠውን የተስፋ ቃል ኢየሱስ ጠብቋልን? ቃሉንስ አላጠፈምን? ሐዋርያቱስ ቢሆኑ ክርስቶስ በራሳቸው የሕይወት ዘመን በቅርቡ ተመልሶ እንደሚመጣ ሲናገሩ የነበረው ንግግራቸው ትክክል ነበርን? አልተሳሳቱም ነበርን? እነዚህ ከፍ ሲል ያየናቸውና ሌሎች መሰል ጥቅሶች ሁልጊዜም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚረብሹና ምቾት የማይሰጡአቸው እንደሆኑ ግልጽ ነው። የሥነ መለኮት "አዋቂዎች" ነን ለሚሉ የለዘብተኝነትን አቋም ለያዙ ሊቃውንት ነን ባዮችና ለከሃድያን ደግሞ የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነተኛነት ለመንቀፍና ስህተት የለባቸውም ስንል የምናምነውን የእኛን እምነት ለማጥቃት ይጠቀሙባቸዋል። "እነዚህ ምንባባት ይፈጸማሉ በተባሉበትና እንዲፈጸሙ በተነገረላቸው ጊዜ (በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት) አልተፈጸሙም፣ ስለዚህ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን በትንቢታቸው ወድቀዋል፣ በመሆኑም ቃሎቻቸውን በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡና ስህተት የሌለባቸው ናቸው ለማለት አንችልም" ሲሉ ይተቻሉ።

ራሱን “አምላክ የለሽ” ብሎ የሚጠራው በርትራንድ ራስል፣ “Why I Am Not A Christian” (ለምን ክርስቲያን አልሆንኩምም) በተሰኘው የክህደት መጽሐፉ ላይ ይህን ግልጽ መደምደሚያ ተጠቅሟል፡-

"በወንጌል ትረካ ውስጥ እንደተገለጸው በእጅጉ አሳሳቢ የሆነ የክርስቶስ ንግግር አለ፤ በዚያም በጣም ጥበብ የሚጎድላቸው የሚመስሉ ነገሮችን ማንም ሰው ሊያስተውል ይችላል። ዳግመኛ ምጽአቱን በተመለከተ እየደጋገመ በእርግጠኝነት የተናገረው በክብር ደመና ታጅቦ በዚያን ጊዜ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ከመሞታቸው በፊት እንደሚመጣ አስቦ ነበር። ይህን የሚያረጋግጡ ብዙ ምንባባት አሉ፣…. የጥንቶቹ ተከታዮች እምነትም ያ ነበር፣ ይህም ንግግሩ እርሱ ላስተማረው የጥሩ ሥነ ምግባራዊ ትምህርት መሠረቱ ነበር” (ገጽ 16)።

ራስል ኢየሱስ ከቃሎቹ የተነሳ የእግዚአብሔር ልጅ ሊሆን እንደማይችል ለማስረዳት በአዲስ ኪዳን ውስጥ “በቶሎ” ሊፈጸሙ የተሰጡ ትንቢታዊ ምንባባትን እንደ “ማስረጃ” አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል። የዘመናችን ክርስትናም፣ በአጠቃላይ፣ ከሃዲያን ከሆኑ አምላክ የለሾች እና በጥቅሉ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ለሚሰነዘሩበት ተቃውሞ በቂ ምላሽ መስጠት አለመቻሉ ያሳዝናል። ይልቁንም መጻኢነት ይህንን ክህደት ለመመከት በቆመበት የሸንበቆ ምርኩዝ በሆነው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮው ሲውተረተር ክርስትናንና ትምህርቱን ለማስቀጥቀጥ ዱላ አቀባይ ሆኖት አርፏል። አማኞች ግን ዛሬ ክርስቶስ ስለ ፍጻሜ ዘመን ያቆመውን አስተምህሮ ከጥቃት ለመመከትና በጥቅሉ በክርስትናው አለም ያለውን ሰፊ ​​ነገረ ፍጻሜአዊ አለመግባባት ለመፍታት በትምህርታቸውና በእምነታቸው ላይ የክለሳ ስራ ማድረግ አለባቸው።

ማቴ 24፥ 34 “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።

ኢየሱስ በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ እነዚያ የጠቀሳቸው ነገሮች በሙሉ በትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸሙ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ዐውደ-ምንባቡን በጥንቃቄ ካጠናችሁ ይህ በትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸም የነገራቸው ዝርዝር፣ የወንጌልን በዓለም ሁሉ መሰበክ፣ የጥፋት እርኩሰት መቆምን፣ የታላቁ መከራ ክስተትን፣ እና የክርስቶስ ዳግም ምጽአትን እንደሚጨምር ታያላችሁ። ይህ በጣም ግልፅ ከመሆኑ የተነሳ በልማዳዊው አስተምህሯቸው ውስጥ ሲያምኑትና ሲከተሉት ከኖሩት ስነመለኮታቸው ጋር ስለሚጣረስ የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ ለሚያቀነቅኑ ወገኖች ይህ በእጅጉ ያስቸግራቸዋል። ባወጣው ባወርደው አልገባህ፣ አልከሰትልህ ያለኝ አንድ ነገር፣ ኢየሱስ እንደተናገረው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ይጠባበቁት ለነበሩ ለትውልዱ ዘመን አማኞች በክብር እንደተመለሰ፣ በዚያው ዘመን አመጸኛይቱ እስራኤል ላይም በእሳት ፍርድ እንደተገለጠ፣ የዳግመኛ ምጽአቱም ተስፋ ያኔ እንደተፈጸመ መቀበል የሚቸግራቸው ወንጌል አማኝ መጻኢያንክርስቲያኖች በእውነት የሚያነቡት መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ነውን፣ ወይስ መጽሐፈ ደሮ?

ሲኤስ ሉዊስ “The World's Last Night" በተሰኘው ድርሰቱ ስለ ማቴዎስ 24፥ 34 ሲናገር አንዲህ በማለት አንድ ተቃውሞ አቅርቧል፦

"የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አቡቀሉምሲሳዊ እምነቶቻቸው ሀሰት መሆናቸው ተረጋግጧል። ሁሉም ገና በሕይወት እያሉ ዳግመኛ ምጽአቱ እንደሚፈጸም ይጠባበቁ እንደነበር ከመላው አዲስ ኪዳን ግልጽ ነው። ይባስ ብሎም ለዚህ የተሳሳተ እምነት አብይ ምክንያት እንደነበራቸው፣ አንዱንና ዋናውን ጉዳይ ማየት ትችላላችሁ። ይህም በጣም አሳፋሪ የሆነው ነገር ይህንን እየደጋገመ ይነግራቸው የነበረው ጌታቸው መሆኑ ነው። እርሱ ግን ከማንም በላይ ስለ አለም ፍጻሜ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።"

ሉዊስ አክሎም እንዲህ ይላል

"ይህ በእውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት እጅግ አሳፋሪ ጥቅሶች መካከል አንዱና ዋናው ነው። ነገር ግን በተነገሩት ዝርዝሮች ውስጥ እንዲህ ያለው መሳቂያ የሆነ መግለጫ እንዴት እንደሚሰነቀር ተመልከቱ። ደግሞኮ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ይላል። አንደኛው የስህተት ማሳያ ሲሆን አንዱ ደግሞ የድንቁርና ኑዛዜ ሆኖ ጎን ለጎን በቅለው አብረው ይታያሉ” [Essay "The World's Last Night" (1960), found in The Essential C.S. Lewis, p. 385]

ስለዚህም ሉዊስ በድፍረት “ይህ ትውልድ” ሲል የተናገረውን የኢየሱስን ንግግር ጠቅሶ ቃሉ አሳፋሪና “ስህተት” ነው ሲል ያላግጣል። ሉዊስ እንዳለው ኢየሱስ ተሳስቶ ነበርን? እኔ በግሌ ጌታ ኢየሱስን ለዘላለም ሕይወት እንደተቀበለ አማኝ ያንን የሉዊስን የድፍረት ድምዳሜ መቀበል አልችልም? ይህ የሉዊስ እና የመሰሎቹ ምሁራዊ ቅርሻት በጌታዬ ፊት ላይ ሲተፋ ማየትም አይሆንልኝም። 

ደስ የሚለው ግን ክርስቶስ እንደተናገረው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ተመልሶ ለመምጣት የገባውን ቃል መጠበቁ ነው። የክርስቶስ ዳግም ምጽአት መንፈሳዊ በሆነ መልኩ ተፈጽሟል - እርሱም እመጣለሁ ባለበት መንገድ - በ70 ዓ.ም ላይ በሆነው በኢየሩሳሌም ጥፋት ተገልጧል። ይህም የተረጋገጠ ታሪካዊ ክስተት ለኃጢአት ፍጻሜውን የሰጠ፣ የዘላለም ስርየትን ያስገኘ ሲሆን፣ በትውልዶች ሁሉ ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖችም ከእግዚአብሔር ሳይለዩ በምድርም ሆነ በሰማይ ለዘላለም መኖራቸውን ያረጋገጠ ነው።

እዚህ ላይ አሁን የሚከተለውን ጥያቄ ታነሱ ይሆናል፡- ጌታ በ70 ዓ.ም ተመልሶ ከመጣ፣ ታዲያ ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ይህንን እንዴት ልታውቅ አልቻለችም? እንዴት ተመልሶ መጥቶ ሳለ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ያላወቀችው ከምን የተነሳ ነው? እኔ እንደሚገባኝ እዚህ ላይ ያለው አንዱ ትልቁ ችግር አስቀድሞ አእምሯችንን የገዛና ሲታሰብ የኖረው ሐሳብ ነው። እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የተሳነን ለዘመናት ተንጠላጥለን ካለንበት፣ እውነት መስሎን ከያዝነው ልማዳዊ አሳባችን አልወርድ ከማለታችን የተነሳ ነው። ምክንያቱም፣ እኛን ሲመስለን ዳግመኛ ምጽአቱ ምድርን ቡን አድርጎ የሚያቃጥል፣ ሰማይን እንደ ሰም የሚቀልጥ፣ ዓለምን በሞላው ከፍጥረቱ የሚቀይር ክስተት አድርገን እናስበዋለን። ስለዚህም ይህ አስቀድሞ ሊከሰት ካልቻለ ዳግመኛ ምጽአቱ ሊሆን አይችልም ብለን ባለማወቅ ላይ የቆመ ግምትና ግግምና ይዘናልና።

እኔ ግን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፣ የተሳሳተው ማን ነው? ቅዱሳት መጻህፍት ስህተት አለባቸው ለማለት እንደፍራለንን? ቅዱሳት መጻህፍቱ ጊዜ ጠቋሚ በሆኑ የንባብ ክፍሎቻቸው ስለ ዳግም ምጽአቱ የተናገሩት ስህተት ነበርን? ወይስ በተቃራኒው እኛ ስለ ዳግም ምጽአት ተፈጥሮ የነበረን እይታ ነው ስህተት? ከሁለቱ የትኛውን ትመርጣላችሁ፣ የትኛውስ ምቾት ይሰጣችኋል? በስህተት የተሞላው ልማዳዊ ምልከታችሁ ወይስ ስህተት የሌለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት?

  • ፕሪቴሪዝም የተፈጸመው ወንጌል

ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ መንግስቱን ሰጥቶናል። አሁን በክርስቶስ "የዘላለም ሕይወት" አለን። የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት እስከ ትንሳኤ እና የፍርድ ቀን ድረስ በሀደስ ውስጥ የቤዛነታችንን ቀን እየጠበቅን መቆየት አያስፈልገንም። ያ ያስፈልጋቸው የነበሩት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ነበሩ። እኛ ያመንን ግን በክርስቶስ ስራ ከፍርድ ወጥተን ወደ ዘላለማዊው መንግስት ሕይወት ተሸጋግረናል። እነዚህ በክርስቶስ አሁን ያሉን እና የተገኙ ከኛም ጋር በውስጣችን የሚኖሩ ባርኮቶቻችንና ጥቅሞቻችን ናቸው እንጂ፣ "ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋንም አላይ" አይነት፣ ተስፋችን የተራበ ሰው እንደሚጓጓለት ርቆ እንደ ተሰቀለ እንቁልልጬ ዳቦ አይደለም። ቅዱስ ቃሉ፦ "የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት" (ምሳሌ 13፥ 12) ይላልና። መላው የራእይ መጽሐፍም የተፈጸመ መጽሐፍ ሲሆን፣ የሚታየውም መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን፣ በጸሐፊውና በበኩረ ተደራስያኑ ታሪካዊ አውድ ብቻ ነው። የመጽሐፉ አጠቃላይ ተዛምዶም በክርስቶስ ካገኘነውና ከተካፈልነው ከመንግስቱ ጋር የተቆራኘ ነው።

ቀጥተኛውና ግልጹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ይህ ነው። ትንቢትም ትርጉም የሚሰጠን አቀራረባችን በዚህ መንገድና አተያይ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ አቀራረብ "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" (Sola Scriptura) በተሰኘው ብቸኛ የተሃድሶ ብርሃን እየተመራ በርካታ አወንታዊ፣ ገንቢና ተጨባጭ የሆነን ንጽረተ አለም ይሰጠናል። ይህ አይነቱ የትንቢት አቀራረብ በአቋሙ ወንጌላዊ የሆነውን ወግ አጥባቂነት የጨበጠ፣ በክርስቶስ ብዙ መጽናናትን የሚሰጥና ግርማ የሞላውን የክርስትናን የድልና የከፍታ ሕይወት የሚያለማምድ፣ በትርጉሙ ቀዋሚነት (consistency) ያለው፣ ብሩህ አመለካከትን ይዞ ጨለምተኛ ያልሆነ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚሰማው አቀራረብ ነው። ጣፋጩን የክርስትናን ሕይወት አጣጥሞ ከመኖርና አለምን በወንጌል ከመድረስና ከመለወጥ ያለፈ ሌላ ምኞትም ሆነ የተሰወረ ፍላጎት እንዳይኖረን የሚያደርገን ንጹህ ትምህርት ነው። በእግዚአብሔር መንግስት መንፈሳዊ ተፈጥሮ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ትርጉም ነው፣ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግስት በተዳሳሽ አካላዊነት፣ በቁሳዊነት፣ በፍልቅ ሞቅታና በስሜታዊነት ፍንደቃ አይለካም አይተረጉምም። ለሌላ ጊዜ በተላለፈና ገና ወደ ፊት እንደሚገባበት የገነት መንገድ ስሜታዊ በሆነ ደስታ ከሚያደክምና ከሚያሰለች ተስፋ ይልቅ፣ አሁን በክርስቶስ የሆነውንና የተገኘውን የተረጋገጠ መዳንን እና የቤተ ክርስቲያንን እውነታነት ያስተምራል። የትንቢትን ፍጻሜ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የታሪክ ሰነድ ገጾች ጋር እያገናዘበ ታሪክን የኋሊት ይመለከታል እንጂ ስለ መጻኢው ደንግጦ ባፈጠጠና በፈራ አይን ያንንም ይሄንንም እየገመተ "ምን ይመጣብኝ ይሆን" እያለ ራሱን በስጋትና በቁም ቅዠት አይጠምድም፤ የመጻኢነት ትንተናም እያቀረበ ማንንም አያሸብርም። ይህ አለም እንደሆነ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ (ካስፈለገም ለዘላለም) እንዲሁ እንዳለ ይኖራል። የምስራች ልንገራችሁ፣ እግዚአብሔር ይህንን ግዑዝ አለም ሊያወድም ምንም እቅድ የለውም። የሰው ልጆች ቢፈልጉ እንኳ፣ ቢቆጡና ቢሞክሩ ይህንን ግዑዝ የእግዚአብሔር አለም ሊያጠፉት አይችሉም። ስለዚህ "ይህ አለም ይጠፋል" በሚል ተላላነት እየተደናበርን፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖረን ከሚገባ ተሳትፎና በጎ ተጽእኖ በጨለምተኝነት ከማፈግፈግ፣ ብሎም ከዚህ ነባራዊ አለም ለመውጣትና ማምለጫን በመፈለግ በከንቱ ከምንደክም፣ ይህ አለም የእግዚአብሔርና የሰው ልጆች አለም ነውና፣ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የተሻለ የመኖርያ ስፍራ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታችንና አገልግሎታችንን በትጋት ብንቀጥል የእግዚአብሔርን ፈቃድ እናደርጋለን። 

ባለፉት 300 አመታት ውስጥ አንዳንድ ታላላቅ የሥነ መለኮት ሰዎችና ሊቃውንት ይህንን አመለካከት ይዘው እንደ ነበር ግልጽ ነው፤ ነገር ግን የሚበዙት ክርስቲያኖች የሮማውን ካቶሊክ ጳጳስ ወይም ጳጳሳዊ ስርአቱን "የክርስቶስ ተቃዋሚው" ነው፣ ደግሞም የሮምን ቤተክርስቲያን የራእይ መጽሐፍ "ባቢሎን" ናት በሚል ወይም በሌላ አይነት የመጻኢነት አስተሳሰብና ትርክት ተይዘው ሲያስተምሩና ሲጽፉ ኖረዋል። በዋናነትም በታሪካውያን (Historicism) እና በአልቦ ሺህ አመት መንግስት (Amillennialism) የነገረ ፍጻሜ ተርጓሚዎች ዘንድ ይህ አይነቱ ትርክት የተለመደ ነው። ያ ግን አሁን ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ ሆኖ አጥብቀው በሚጠይቁና አድምተው በሚመረምሩ የቃሉ ተማሪዎች እየተተቸ በብዙ ተለውጦአል። አሁን ያለው ትውልድ (መደዴውን ማለቴ አይደለም) ከቀድሞው ይልቅ እምነቱንና አመለካከቱን አጥብቆ የሚጠይቅና የሚፈትሽ ነው ብዬ አስባለሁ። መቼም እነ ዊልያም ሚለር፣ ደርባይ፣ ረስል፣ ሩትፎርድ፣ ስኮፊልድ፣ ዋልቩርድ እና ሃል ሊንድሴይ በዘመን ቆጣሪነት (Despensationalism) ትርክት በብዙ ተታለው ሌሎችንም እንዳሳሳቱ እኛ በቀላሉ የምንሞኝ አይደለንም። በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ሲቆለል የኖረው የአስተምህሮ ውሸትና እስካሁንም ብዙዎች በትንቢት ትርጉማቸውና በአስተምህሮታቸው የሚያራግቡት የሃሰት ትንበያ የበለጠ ጠያቂና ጠርጣሪ አድርጎናል። ከቅዱስ ቃሉ በቀር እንደወረደ የምንቀበለው፣ ሳናላምጥ የምንውጠው፣ የማንጠረጥረውና የማንጠይቀው ነገር የለንም። "ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን?" (ሐዋ 17፥ 11) የሁልጊዜ ጥያቄአችንን ምርመራችን ነው።

ከመቶ አመታት በፊት በእንግሊዝ አገር የባይስወተር ማህበረ ምእመናናዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ የነበሩ ዶክተር ጀምስ ስቱዋርት ረስል (1816-1895) The Parousia - A Critical Inquiry Into The NT Doctrine Of Our Lord’s Second Coming በሚል ርእስ መጽሐፍ ጽፈው ነበር። ይህ መጽሐፍ አሁንም እንደገና በብዙ ቅጅ እየታተመ ሲሆን በአሜሪካን አገርና በሌሎችም አገሮች በበርካታ የክርስቲያን መጻህፍት መሸጫ ሱቆች ውስጥ በየሸልፉ ላይ ተሰድሮ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ ቆየት ካሉትና የኃላፋውያንን አመለካከት ደግፈው ከተጻፉት መጻህፍት መካከል ዋነኛው ነው። በአውሮፓ የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያናዊ የሥነ መለኮት ሰዎችም ተመሳሳይ አቀራርብን ይዘው ተስተውለዋል፤ በመሆኑም ከረስል ጋር በተመሳሳይ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ተርጓሚዎች ተመሳሳይ የሆነን ነገር ሲናገሩ ቢደመጡና ስለመጽሐፉም ጥሩ ጥሩ ነገር ቢናገሩ የሚያስገርም አይደለም፤ ለምሳሌ ኤፍ. ደብልዩ. ፌረር "ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀስና እንዲጠና የሚጠቆም" ብሎለታል። Biblical Hermeneutics የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉትና ከራስል መጽሐፍ ብዛት ያላቸውን ማጣቀሻና ማጣቆሚያ የተጠቀሙት የረስል ዘመን ሰው ሚልተን ቴሪ በስነ መለኮቱ አለም የነገረ ፍጻሜ ስነ ትርጓሜ ጥናት ዘርፍ ሰፊ ተቀባይነትን ባተረፉ ሥራዎቻቸው የረስልን የኃላፋዊ አቀራረብ ተከትለዋል። ስለ ረስል እና ስለ ኃላፋውያን አመለካከት ከተናገሩ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ሊቃውንት መካከል አንዳንዶች የተናገሩትን እዚህ ላይ በጥቂቱ ልጥቀስ፦

"አስቀድሞ አእምሮአችሁን ይዞት ከነበረው የነገረ ፍጻሜ ስርአተ ትምህርት ጋር የሚጣጣሙ ባለመሆናቸው የተነሳ፣ ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣበትን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትንና እንዲህ ያሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ለመተርጎም ምን ያህል ጊዜ ስትታገሉ ኖራችኋል? The Parousia የተሰኘው የረስል መጽሐፍ የክርስቶስን መመለሻ ጊዜ ቅርበቱን በሚናገርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በዋዛ የሚመለከተው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳለ በቁሙ እንተረጉማለን የሚሉ ሰዎች ሆን ብለው ወይም ሳያስቡት ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ከሚሉት በተቃራኒው ሌላ ትርጉም እየሰጡ የነዚህን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባትን ግልጽ ትርጉም ዘለው ያልፉታል። የራስልን መጽሐፍ ማንበብ ማለት በጭስ በታፈነ ክፍል ውስጥ ንጹህ አየር እንደ መተንፈስና በግልጽ የሥነ ፍታቴ መስታወት አጥርቶ እንደማየት ነው።" (Gary DeMar - Author of Last Days Madness)

"የራስል መጽሐፍ ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊው የነገረ ፍጻሜ ጥናት በአግባቡ የታየበት ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ተዘጋጅቶ ከቀረቡላት እጅግ አስፈላጊ ስራዎች መካከል አንዱ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የተገለጸውና የፓሮዥያውን የጊዜ ማእቀፍ አመላካች የሆኑ ጥቅሶችና ምንባባት በዚህ ጥራዝ ውስጥ ተነስቶ በወጉ የተባለው ነገር ሁሉ ጠቀሜታው ለነገረ ፍጻሜአዊ ጥናት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ፊት በተቀደሰው መጽሐፍ ንጽህናና ታማኝነት ላይ በተቃውሞ ለሚነሱ ክርክሮች ሁሉ ፍቱን መድሃኒት ነው።" (Dr. R. C. Sproul - Chairman, Ligonier Ministries)

"ምንም እንኳ የጄ. ስቱዋርት ረስል The Parousia የተሰኘው መጽሐፍ ከደረሰበት ድምዳሜ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ ባልልም፣ ነገር ግን ይህንን በወጉ የተደራጀና የተሰናሰለ፣ ክርክሩንም በጥንቃቃቄ ያቀረበ፣ ለእውነተኛና በሳል ለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጆችና አጥኝዎች የኃላፍያንን የነገረ ፍጻሜ ምልከታ በመከላከል የተጻፈ ዝርዝርና እምቅ የጽሁፍ ሃብት እንዲነበብና እንዲጠና በአንክሮ አሳስባለሁ። በነገረ ፍጻሜ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ካነበብኩአቸው መጻህፍት መካከል በእጅጉ አሳማኝ የሆነና የያዝኩትን አቋም በኃይል የተገዳደረ፣ በገዛ ራሴም የኖረና የቀደመ አስተሳሰቤ ላይ ታላቅ ተጽእኖን ያሳደረ አንዱ መጽሐፍ ነው። ይህ የረስል የአዲስ ኪዳን ነገረ ፍጻሜ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የሥነ መለኮት ጥናት የጥራት ደረጃ ከፍ አድርጎታል።" (Dr. Kenneth L. Gentry, Jr. - Author of Before Jerusalem Fell)

በእርግጥም የራስል መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትንቢት ለመረዳት እጅግ የሚረዳ ሃብት ነው፣ ብዙዎች ግን ይህንንም መጽሐፍ ሳያነቡ በገዛ ራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በግላቸው እያነበቡና እያጠኑ ወደ ኃላፍያን ምልከታ እንደደረሱ እናውቃለን። እነርሱም አሁን የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ትርጉምና መልእክት በርቶላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ፍጻሜአቸው ገና ድሮ ያለፈ መሆኑን እስካሁን ገና ያላወቀና ያልባነነ የቃሉ ወዳጅና ተማሪ ከሆናችሁ፣ የምትነቁበትና የምትባንኑበት ጊዜው አሁን ነው ልላችሁ እወዳለሁ።

  • ያልተጻፈ የሚያነቡ ክርስቲያኖች

ቅዱሳት መጻሕፍት ብዙዎች ከያዙት እምነት በተቃራኒው ይህ ግዑዙ ፍጥረተ አለም መቼም እንደሚጠፋ የሚያስተምሩበት አንድም ሥፍራ የለም። ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ አድርጉ።

ዘፍጥረት 8፥ 21 “እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም”

የሚገርመው ሰዎች የተጻፈውን ቸል ብለው ያልተጻፈ እያነበቡ፣ እግዚአብሔር ምድርን አንድ ጊዜ በውሃ አጥፍቷት ነበር በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ በእሳት ያጠፋታል ለማለት ይደፍራሉ። እግዚአብሔር የገባው ቃል ግን “ምድርን ዳግመኛ … አልረግምም፥…ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም” የሚል ነው እንጂ ሁሉን የማጥፋት ዘዴውን ከውሃ ሙላት ወደ እሳት ቃጠሎ አልለወጠውም። በውሃስ ፈንታ በእሳት አቃጥሎ ማጥፋት ምቾት ይሰጠዋልን? ወይስ ዳግመኛ ምድርን ላለማጥፋት ነው ቃል የገባው?

መዝሙር 148፥ 4-6 “ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፤ የሰማያት በላይም ውኃ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም”

እግዚአብሔር ሰማይና ምድር አያልፉም ብሎ ለዘለአለም እንዲመሰርቱ የሰጠው ትእዛዝ ምን እንደነበር ተመልከቱ። ኦሪት ዘፍጥረት 8፣ 21 ላይ እግዚአብሔር ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ እንደማያጠፋ ተናግሯል። እግዚአብሔር ሊታመን ይችላልን? ቃሉንሥ ይጠብቃልን? በቅርቡ እንደሚመጣሥ ተናግሮ አልነበረምን? ያንንስ አላደረገውምን?

አሁን እንግዲህ እርግጠኛ ነኝ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደተናገረው ያኔውኑ በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ተመልሶ ከሆነ፣ እንግዲያውስ አሁን የምንኖረውና እየኖርን ያለነው በአዲሱ ሰማይ እና ምድር ውስጥ ነው ማለት ነው።

ራእይ : 21፥1-2 “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ”

ተዳሳሽ ሰማይና ምድር ለሚጠባበቁ ተላላ ክርስቲያኖች ይህንን መቀበል ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። እንዴት ነው በአዲስ ሰማይ እና ምድር ውስጥ ነን ማለት ይምንችለው? ሲሉም ይጠይቃሉ። 

  • አዲሱ ኪዳን፣ አዲሱ ሰማይና ምድር

አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር ግን በክርስቶስ ተመርቆ የተሰጠን አዲሱ ኪዳን መሆኑን ሲረዱ ያኔ ይህን ለመቀበል ቀላል ይሆንላቸዋል።

ገላትያ 4፥ 22-26 “አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት”

እናታችን የሆነችው ይህች "ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም" በእውነት ማን ናት? እዚህ ላይ ያለው ንጽጽር በሁለቱ ኪዳኖች መካከል ያለ መሆኑን ልብ በሉ። ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ብሉይ ኪዳንን ትወክላለች፣ ስለዚህ ይህቺ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ደግሞ አዲሱን ኪዳንን ትወክላለች ማለት ነው።

ራእይ 21፥ 9 “ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ”

“ሙሽራይቱ” የተባለችው “የበጉ ሚስት” ለመሆኑ ማን ናት? ቤተክርስቲያን አይደለችምን! መልአኵ ለዮሐንስ “የበጉን ሚስት” እያሳየው ነው። ይህን እያሰባችሁ የሚቀጥለውን ጥቅስ አስተውሉ።

ራእይ 21፥ 10 “በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤

“ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ” ይልና “ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን አሳየኝ” ይላል የበጉ ሚስት አዲሲቷ ኢየሩሳሌም፣ እርስዋም ቤተ ክርስቲያን ናት። አሮጌዋ ኢየሩሳሌም ሥጋዊቷ እስራኤል ነበረች አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ደግሞ የክርስቶስ ሙሽራ ናት። ላይኛይቱ እየሩሳሌም "የበጉ ሚስት" ነች፣ እርስዋም ቤተክርስቲያን ነች፣ እርስዋም አዲሱ ኪዳን ናት፣ የግዚአብሔር ከተማም ናት። የዕብራውያን መልዕክት የጽዮንን ተራራና ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን በንጽጽር ባቀረበ ጊዜ ይህንን ይጠቁሟል።

ዕብራውያን 12፥ 22-24 “ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።”

የጽዮን ተራራ ካለ በኋላ “እና” በሚለው ቃል ምትክ “ይኸውም” ወይም “ይህችም” የሕያው እግዚአብሔር ከተማ መባል ነበረበት። ደብረ ጽዮን ወይም የጽዮን ተራራ የእግዚአብሔር ከተማ እርስዋም ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ናት። ስለዚህ፣ የጽዮን ተራራ፣ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ፣ የሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያንን ነው። እነርሱም ኋላ ላይ በቁጥር 28 ላይ እንቀበለዋለን የተባለው የማይናወጥ መንግሥት የሚያመለክተው በክርስቶስ አካል የተዋጁትን ሁሉ ነው። በሌላ አነጋገር እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማኞች በሰማያትም የተጻፉ የበኵራት ማኅበር ማለት ናቸው።

  • ቃሉን በወጋችን ላይ እናንግስ

በወጋችንና በቅዱሳት መካከል ምርጫ እንድናደርግ የቀረበልንን ጥሪ ቸል አንበል። ሰዎች ተጣብቋቸው ባለው ወግ እና በቅዱሳት መጻሕፍት መካከል አንዱን መምረጥ አለባቸው - ምርጫውም ቀላል እና ግልጽ መሆን አለበት። የዳግመኛ ምጽአቱ እውነትን አይቀሬነት የቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት ነው፤ ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን እውነታ መካድ ማለት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡ መሆናቸውን መካድ ነው። በዚህ ትስማማላችሁን? እንግዲህ፣ ዳግም ምጽአቱ ፍጻሜ እንዲያገኝ በመለኮት የተቀጠረለት ጊዜ ልክ እንደ ዳግም ምጽአቱ የቅዱሳት መጻህፍት እውነታ የማያሻማ እና ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። ልክ እንደዚሁ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳግም ምጽአት ፍጻሜ የሚሰጠውን የጊዜ መግለጫ መካድ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጠውን ቃል መካድ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህስ ያስማማናልን? ይፈጸማል የተባለው ዳግም ምጽአትና ለፍጻሜው የተመደበለት የጊዜ ወሰን ሁሉቱም በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡ፣ ሊካዱም የማይችሉ ናቸው።

ምናልባት ይህንን የምታነቡ ወገኖች ይህ አመለካከት ሰምታችሁትም አስባችሁትም የምታውቁት አዲስና እንግዳ ከሆነባችሁ፣ በጌታ ፍቅርና በትህትና የምለምናችሁ እንዳትደነብሩ ነው፤ ይልቁንም እያልኩ ያለሁት ምን ያህል የቃሉ ድጋፍ እንዳለው በግልፅ እና በታማኝነት እንድትመለከቱት እጠይቃለሁ። አንድ ነገር እውነት ነው፣ እርሱም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባለው በእያንዳንዱ መጽሐፍ ማለት በሚቻልበት ደረጃ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረው እርሱ “በቅርቡ” እና “ቶሎ” ተመልሶ እንደሚመጣ ያሉው ትምህርት ነው። ይህንንም በየትኛውም ሥነ መለኮት ማስተባበል አይቻልም። በማንኛውም የሥነ ትርጓሜ እና የሥነ ፍታቴ መርህ ይህንን “በቅርቡ” እና “ቶሎ” የተሰኘ ጊዜ አመልካች መግለጫ ወደ 2,000 ዓመታት ለሚጠጋ እና ከዚያ ለሚያልፍ ዘመን ማራዘም በጣም ከባድ ነው። የየትኛውም ቋንቋ መዝገበ ቃላትም እነዚህን “በቅርቡ” እና “ቶሎ” የተሰኙ ጊዜ አመልካች ቃላት ሲተረጉሙ እንዲህ ያለውን የተራዘሙና የተለጠጠ የጊዜ ወሰን አያደርጉለትም። ከመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ እስከዚህ እኛ እስካለንበት ሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ “በቅርቡ” እና “ቶሎ” የተሰኙት ቃላት ትርጉማቸውንም ሆነ የዜ ወሰናቸውን አልለወጡም። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለእኔ ዋጋ ያለውና ዋናው ጉዳይ ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡ መሆናቸው ነው። ቅዱሳት መጻህፍት አይዋሹም። ጌታችን በቅዱሳት መጻህፍት ያስተማረውን ውድ እውነት እድሜ ጠገብ የሆነው የሰዎች ትውፊት እና የኖረ ልማድ እንዲነጥቃችሁ አትፍቀዱ። እነዚህ የተባሉ ነገሮች በእርግጥም እንደዛ እንደተባሉት መሆናቸውን ለማየት ቅዱሳት መጻህፍትን በየቀኑ እየመረመራችሁ በልብ ስፋት የቤርያ ሰዎችን ሁኑ።

በዚህ ጽሁፍም ሆነ በሌሎቹ ትምህርቶቼ ላይ ጥያቄዎች ቢኖሯችሁ ጻፉልኝ፤ ጸጋው ባገዘኝ ልክ መልሼ እጽፍላችኋለሁ። ብሎገሬን መጎብኘትም አትርሱ። ይጠቅመናል የምትሉትን ማናቸውንም ጽሁፍ በማናቸውም መንገድ ያለገደብ መጋራትና ማጋራት እንድትችሉም ፈቃዴ ነው።

ሰላምና ጸጋ ይብዛላችሁ!!

(ግዛቸው ከበደ)

gizachewkr@gmail.com
















From Blogger iPhone client