የፍጥረት መቃተት
መግቢያ፦
በርካታ ክርስቲያኖች ፍጥረት ብለው የሚገልጹትን ይህን ግዑዝ ፕላኔት ምድር አስመልክቶ አሁን ተፈጥሮ እየቃተተ እንደሆነና አንድ ቀን ወደፊት ደግሞ ፍጽምናውን እንደሚያገኝ ያምናሉ ይጠባበቃሉም። የፍጥረትንና የተፈጥሮንም ልዩነት ሳይገነዘቡ ቃሉን እንተርጉም ይላሉ። አንድ ቀንም ይህ የፍጥረት መታደስና ፍጽምና ሲመጣም ይላሉ፣ ያኔ በየትኛውም የአለም ጥግ በፍጡራን መካከል ጉዳትና መጎዳዳት አይኖርም፣ መታመምና መሰቃየት ይቀራል፣ ሟችና ገዳይ አይታሰቡም፣ ተናካሽና ተናዳፊ የሆኑ ነፍሳት የሚናከሱና የሚናደፉ አይሆኑም፣ ነብርና ፍየል አብረው ይተኛሉ፣ አንበሳውና በሬው ባንድነት ሳር ይግጣሉ፣ ሕጻን ልጅ ከእባብ ጋር ይጫወታል፤ ንቢቱም ጣፋጭ ማሯን ብቻ ትለግሳለች እንጂ መርዟን አትወጋም፤ (እዚህ ጋ በቅንፍ ትንሽ ሙድ ቢጤ ልያዝና) ያኔም “ንቦ ንቦ አትናደፊ፣ ንቦ አትናደፊ” የሚል ዘፈን አይታሰብም። ሲቀጥልም በረሮና አይጥ በቤታችን ሳያስቸግሩን አብረን በሰላም እንኖራለን፣ ምናልባትም አስቤዛ ስንሸምት እንደ ቤተሰብ አባል እነርሱንም ከግምት ያስገባ ሸመታ እንፈጽማለን፣ የጸሐይ ሙቀትና ትኩሳት፣ የብርድና የውርጭ ቃጠሎ ይቀራል፣ እሾሃማ ተክል እና መርዛማ እጽዋት ጉዳት ማስከተላቹውን ያቆማሉ፣ የሰሉ ድንጋዮችና ቋጥኞች ከእንግዲህ የሚቆርጡና የሚግጡ አይሆኑም፣ ብላ ብላ ብላ ወዘተ....።
ይህንን ትምህርት ለመደገፍ ታዲያ ብዙ ጊዜ የትርጉም ሰለባ የሚሆነው ጥቅስ ይህ በሮሜ 8፥ 19-23፡ ያለው ቃል ነው።
“የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።”
በዚህ ክፍል ላይ ከፍ ሲል በተጠቀሰው አይነት የሚቀርበውን ታዋቂ ትርጓሜ “ንዳው በዘጠና ትርጉም” ብየዋለሁ፣ ፈጽሞም አልስማማበትምም። ለምን እንደማልስማማበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያቴን ቀጥሎ አቀርባለሁ።
፩. ፍጥረት ባዲስ ፍጥረት፦ ሲጀመር “ፍጥረት” እና “አዲስ ፍጥረት” የሚሉት እነዚህ ሁለት ቃላት ወይም መግለጫዎች የሚያመለክቱት ሰዎችን ነው እንጂ ግዑዙን አለም ወይም በጥቅሉ ፕላኔቷን ምድር ወይም ተፈጥሮን አይደለም። ይህ ግዑዝ አለም ወይም ፕላኔቷ ምድር (በጥቅሉ ተፈጥሮ”) በዚህ የንባብ ክፍል ውስጥ በሚሰጥ የበርካታ ተርጓሚዎች ትንተና መሰረት ተፈጥሮ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ይደርሳል” ብለው ስለ ማሰባቸው ሳስበው ራሱ እገረማለሁ። ከፍ ሲል የጠቃቀስኳቸውና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ፣ ዛፉም ድንጋዩም፣ ለማዳው እንስሳ የዱር አውሬው ሁሉ ወደዚያ ክብር ይደርሳል የሚል ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ መቃዠት ካልሆነ በቀር ምን ሊሆን ይችላል? የሌለ (non existence) እና ክፍሉ በአውዱ ውስጥ ፈጽሞ የማያነሳውን ጉዳይ ሰንቅሮ ማስተማርም መታረም ያለበት ግብዴ ስህተት ነው።
ለምሳሌ፣ በበርካታ የሥነ መለኮት አዋቂዎች ዘንድ ፍጥረታዊ መገለጥን ወይም አጠቃላይ መገለጥን ያስተምራል ተብሎ ፊት ለፊት ሰለባ የሚሆነውን ምንባብ፣ ይኸውም ሮሜ 1፥ 19-23 ያለውን ክፍል ተጠግተን በገዛ አውዱ ውስጥ ብንመለከተው፣ ፈጽሞ ያንን እንደማያስተምር እንረዳለን። ሰውም እውነተኛውን አምላክ ወደማወቅ የሚመጣው ተፈጥሮን በማየት ሳይሆን ወልድ ራሱን ሊገልጥለት ሲወድ ብቻ ነው። ይልቁንም ክፍሉ የሚያወራው እግዚአብሔር ስለራሱ መገለጥ ሰጥቷቸው ስለነበሩ ሰዎች፣ በታሪካቸው የዘላለም ኃይሉንና አምላክነቱን ለማወቅ እድሉ ስለነበራቸው ሰዎች፣ በተገለጠላቸው መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት ሰዎች፣ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ፍርድ ስለደረሰባቸው ሰዎች ነው። ከእስራኤል በቀር ይህ እድል የነበውረው፣ ዕድሉንም ያበላሸ፣ በዚህም ምክንያት በታሪኩ ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔር የቀጣው ሌላ አንድም ህዝብ ከምድር አህዛብ መካከል አልነበረም።
"እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ።" ሮሜ 1፥19-21
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ፈጽሞ ስለተዳሳሹ ፍጥረተ አለም እየተናገረ አለመሆኑን፣ ይልቁንም እግዚአብሔርን ለማወቅ እድሉ ስለነበራቸው አመጸኛ ሰዎች የሚናገር መሆኑን ማየት የተሳነው እንደመሆን አሳዛኝ ጨለማ የለም። እንግዲህ በሮሜ 1 ላይ በገጠመው የመረዳት መንሸዋረር አቅጣጫውን ስቶና ፍጥነቱን ከልክ በላይ ጨምሮ እንደሚያሽከረክር ሕገ ወጥ አሽከርካሪ በሕገ ወጥ ስነፍታቴና ከመስመር በወጣ ሃቲት በሮሜ 8 ላይ ሲዘባርቅ ራሱንም የሚሰሙትንም ይዞ ገደል ይገባል። ይሄ ነው በየምስባኩ፣ በየመጽሐፉና በማህበራዊ ሚድያው የሚታይና የሚሰማ “ንዳው በዘጠና”።
፪. እስራኤል እንደ ፍጥረት፦ የሮሜ ምዕራፍ 8 የንባብ ክፍላችን ጠቅላላ አውደ ምንባቡ እንደሚያሳየው ከሆነ “ፍጥረት” የሚለው ቃል እስራኤል እንደሆነ እንድናስብ ግድ ይለናል። እስራኤል ፍጥረት ነው። ፍጥረት በግሪኩ ktisis ነው። በአዲስ ኪዳንም ለ20 ጊዜ ያህል በተለያየ አውድ ጥቅም ላይ ውሏል። ወደ አማርኛ ሲተረጎምም “ተፈጥሮ” ፣ “የተፈጠረ”፣ ወይም “ፍጡር” ተብሏል። አንዳንድ ጊዜ ቃሉ በጥቅሉ ተዳሳሹን ፍጥረተ አለም ለማመልከት ሲያግለግል፣ ከዚያ በመለስ ደግሞ የሰውን ዘር ለማመልከት ያገለግላል፤ ለምሳሌ፣ በማርቆስ 16፥ 15 “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ማለቱ ወንጌልን ለተዳሳሹ ግዑዝ አለም፣ ለዛፉና ለድንጋዩ ስበኩ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ወንጌል የሚሰበከው ሊሰሙት፣ የእምነትና የንስሃ ምላሽ በመስጠት ሊለወጡ እድሉ ላላቸው ለሰዎች ነው።
ጳውሎስ ግን ክርስቲያኖችን አዲሱ ፍጥረት በማለት ይጠራቸዋል፡- “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፣ እነሆ፥ ሁሉ አዲስ ሆኖአል” (2ቆሮ. 5፥ 17) ይላልና። አዲሱ ፍጥረት የሚያመለክተው ክርስቲያኖችን ነው እንጂ የተለወጠች ግዑዝ ፕላኔት ምድርን አይደለም። (ዓለም ግን በክርስቲያኖች ብትሞላ የተሻለ ተፈጥሯዊ ፕላኔት ልትሆን መቻልዋ አይጠረጠርም)። የአዲሱ ፍጥረት የመጀመሪያው በኩር ጌታ ኢየሱስ መሆኑንም ቃሉ ያስተምራል (1ቆሮ 15፥ 20፤ ቆላ 1፥ 15)፤ ቤተክርስቲያንም ከእርሱ የተነሳ ፍጥረቱ ሆናለች (ኤፌ 2፥ 10)።
ይህ ktisis የተሰኘው የግሪክ ቃል የሚያመለክተው በጥቅሉ ተዳሳሹን ፍጥረተ አለም ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በተለይ ሰዎችንም ለመግለጥ ጥቅም ላይ መዋሉን አትርሱ። እስራኤል የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደነበረ ኢሳይያስ ይነግረናል፣ “አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል…ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።” (ኢሳይያስ 43፥ 1 እና 15)። ስለዚህ እንዲህ ካሉ በርካታ ጥቅሶች በመነሳት “ፍጥረት” የተባለው አመልካችነቱ እስራኤልን እንደ ህዝብ ደግሞ ነው እንጂ ሌላ ግዑዝ ፍጥረተ አለምን አለመሆኑን ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል።
ይህ ፍጥረት የሚለው ቃል ደግሞ የሚያመለክተው የአሮጌው ኪዳን ሰዎችን፣ ማለትም በጳውሎስ ዘመን ገና በአሮጌው ኪዳን ሥር ተገዝተው ያሉትን የሚያመለክት የሆነውን ያህል፤ ከፍ ሲል ለማሳየት በተፈለገው መሰረት አዲሱ ፍጥረት የሚለው ሀረግ ደግሞ የሚያመለክተው የአዲሱ ቃል ኪዳን ሰዎችን (ክርስቲያኖችን) ነው። በንባብ ክፍላችን “ፍጥረት” የተባለው “ይጠብቃል”፣ “ይናፍቃል”፣ “ይቃትታል”፣ “በምጥ ይኖራል”፤ እንዲሁም “የመንፈስ በኩራት” ያለው አዲሱ ፍጥረትም ይጠብቃል ይቃትታልም።
ጳውሎስ ፍጥረት ይናፍቃል ሲል የፍጥረት ናፍቆት ምንድን ነው? ናፍቆት በግሪኩ apokaradokia ነው። ይህም ለመሆን ተስፋ ያለውን አንዳች ጉዳይ በኅይለኛ ስሜትና በብርቱ ናፍቆት ጓጉቶ መጠባበቅ ነው። ይህም ራስን ወደ ላይ አሻቅቦ በማንሳት አይንን ትኩር አድርጎ በመመልከት ተንጠራርቶ ማየት፣ መፈለግ ነው። በተዘረጋ እጅ እና ባንጋጠጠ ራስ ቀና ብሎ ሊመጣ ያለን ታላቅ ማዕረግተኛ ባለስልጣን አፉን ከፍቶ እንደሚጠብቅ አንድ ሰው፣ ልክ እንደዚሁ ፍጥረትም የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ናፍቆ እየተጠባበቀ ነበር ማለት ነው። ይህ አይነቱ የናፍቆት ጥበቃና ትጋት የሚጠበቀውን ጉዳይ ቅርበት ያመለክታል። መጠበቅ በግሪኩ apekdechomai ሲሆን ቃሉ ሮሜ 8፥ ቁጥር 19፣ 23 እና 25 ላይ ያለውን ጨምሮ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለሰባት ጊዜ ያህል በተጠቀሰበት ቦታ ሁሉ በቅርቡ፣ ቶሎ ሊሆን ያለውን የጌታ ዳግም ምጽአትን ከመጠባበቅ ጋር የተጣመረ ነው፣
፫. ለከንቱነት መገዛት፦ “ከንቱነት” በግሪኩ mataiates ነው። ሲተረጎምም የታሰበለትን ግብ ሳይመታ መቅረት፣ መክሸፍ ነው፤ የታሰበለትን ውጤት ማሳካት አልቻለም፣ አላማውን ሳተ፣ እንዲሆን የተፈለገውን ሳይሆን ቀረ ማለት ነው። ይህ ታዲያ ፍጽሞ ስለ ፕላኔት ምድር መክሸፍ የሚናገር አይደለም። የከሸፈው ሰው ነው እንጂ ግዑዙ አለም አይደለም። ቃሉ በሌላ ስፍራ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ፦ “እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።” (ኤፌሶን 4፥ 17) ከንቱነት እዚህም ላይ ያው mataiates ነው። ይህም የአዕምሮ ከንቱነት ነው። ይህም ስለ ሰዎች ስነ ምግባር የተነገረ ነው እንጂ ስለ ድንጋይና ዛፎች የተነገረ አይደለም። “ተገዝቷል” ማለትም በግሪኩ hupotasso ነው። ቃሉም የሚሊቴሪ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ከሌላው በታች ሆኖ፣ ተረግጦና ተሸንፎ ተንበርክኮ ማደር ነው። ይህም ለከንቱነት የመገዛት ሁኔታ ሥነ ምግባራዊ ዝቅጠትን ያሳያል። እስራኤል ከአባቶቻቸው የወረሱት ከንቱ ኑሮ እንደነበራቸው ጴጥሬስ ይናገራል (1ጴጥሮስ 1፥ 18)፣ ያም ከንቱ ኑሮ ከኦሪት ህግ በታች ተገዝተው ይኖሩ የነበሩበትን ኑሮ ያሳያል። እርሱም ህጉ የጫነባቸው ባርነትንና የሞት ቀንበር ነው። እስራኤልን ከተፈጠረችበት ዓላማ አግዶ የያዘና የከለከለ ቀንበር ነበር። ሕጉ ለከንቱነት አስገዝቷቸው ነበር።
እንግዲህ ይህ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” (ሮሜ. 8፥ 21) የሚለው በሮሜ መጽሐፍ አውደ ምንባብ ውስጥ ከሚነሳው ዋና ትምህርት ይኸውም ከሕጉ አርነት መውጣት ጋር ይስማማል። በሌላ አነጋገር “ፍጥረት” የተባሉት እነርሱም በአሮጌው ቃል ኪዳን ሥር ተገዝተው ያሉት፣ ወደ መበስበስና መንፈሳዊ ሞት ከሚመራው (2 ቆሮ. 3:7) “ከጥፋት ባርነት” ማለትም ከሕጉ ባርነት ነፃ ስለ መውጣታቸው የተነገረ ነው። የሚናገረውም ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን የክብር ነፃነት፣ እርሱም በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነ ነፃነትን ማግኘታቸው የማይቀር ስለመሆኑ ነው። ይህንንም ሙሉ ነጻነት ሙላትና ፍጻሜ የሚሰጠው በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው ዳግመኛ ምጽአቱ ነው።
፬. የሚቃትተው፦ ታዲያ ጳውሎስ ራሱና “ፍጥረት” በሚል ስያሜ የተጠቀሱት፣ እነርሱም የአሮጌው ኪዳን እስራኤል፣ በዚህ ጊዜ ማለትም ያኔ በ58 ዓ.ም.አካባቢ የሚቃትቱበት ምክንያት ምንድን ነበር? ልብ አድርጉ ይህ ግዑዙ አለም አይቃትትም፣ አያቃስትምም። መቃተት ሰውኛ ነው እንጂ የግዑዝ ፍጥረት መገለጫ አይደለም፤ ስሜት ያለው የሚሰማው እና የሚያስብ ሰው ነውና፣ ስለዚህ ሰዎች ይቃታሉ፣ እንጂ ግዑዝ አለም ይህ ተፈጥሮ የለውም። እንግዲህ በዚህ ክፍል “ይቃትታል” የተባለው ፍጥረት—በቅርቡ የሚሆን ቤዛነቱን እየጠበቀ ያለ ነበር ማለት ነው። ጻድቃን የሆኑ ሁሉም የእስራኤል ቅሬታዎች ይቃትቱ ነበር እንጂ ግዑዝ ፍጥረተ አለም የሚቃትተውም የሚያስቃትተውም ነገር የለውም።
ፍጥረት ከመሆን (የአሮጌው ኪዳን እስራኤል ከመሆን) አዲስ ፍጥረት ወደመሆን (የአዲሱ ኪዳን እስራኤል / ክርስቲያኖች ወደመሆን) ማለትም የእግዚአብሔር ልጆች ወደ መሆን የከበረ ነፃነት ለመድረስ (ሮሜ 8፥ 21) ቤዛነትን ለማግኘት/ ትንሳኤን ለማግኘት /ለመለወጥ ጓጉተዋል። ይህንን ግን አስተውሉ፣ ቤዛነት ገና ሙሉ በሙሉ እውን ለመሆን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተክርስቲያን ትውልድ ወቅት አርባ አመታትን የሚጠብቅ /ገናም ፍጻሜውን በሙላት ያላገኘ አንዱ ክስተት ነበር። ያኔም ጳውሎስና ወንድሞቹ በከፊል ቤዛነታቸውን በተስፋ ተቀብለው ሳለ (ኤፌ. 1፥ 7) ገና ሙሉ በሙሉ አልተቀዳጁትም ነበር (ኤፌ. 1፥ 14፣ ሮሜ. 8፥ 23)።
ቤዛነት በመሠረቱ “የኃጢአት ይቅርታ” ወይም “መዳን” ማለት ነው (ኤፌ. 1፥ 7)፤ ለዚህም ነው ጳውሎስና ወንድሞቹ ያኔ በ58 ዓ.ም ላይ እያሉ አሁንም ገና ይህንን ቤዛነት በጉጉት ይጠባበቁ የነበረው። ያ የአሮጌው ኪዳን “የሞት አገልግሎት” (2ቆሮ. 3፥ 7) ኃጢአትን ማስወገድ የማይችል ነበር (ዕብ 10፥ 4) ገናም ቤተመቅደሱ ሳይፈርስ ቆሞ ሳለ ሕጉ በስራ ላይ ነበር። ስለዚህም፣ በዚያ የመጠባበቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በቅርቡ ሊመጣ ያለውን የአዲሱን ቃል ኪዳን የኃጢአት ይቅርታ ዘመን፣ ማለትም ቤዛነታቸውን /መዳናቸውን /ትንሣኤያቸውን /የዘላለምን ሕይወት ይናፍቁ ነበር። በሌላ አነጋገር “የሰውነታቸውን ቤዛነት” ይናፍቁ ነበር (ሮም 8፥ 23)። ይህ ሰውነታችን” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የእስራኤልን ብዝሃ አካል እንደ ድርጅት (Corporately) ነው። “የእኛ” ሰውነት ሲልም ብዝሃ ቁጥርን ያሳያል፤ “ሰውነት” ግን ነጠላ ነው። ምጡና ናፍቆቱም የአሮጌው ኪዳን ታማኝ ቅሬታዎች (የእስራኤል አካል እንደ ኅብረት) ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን አካል ወደ ክርስቶስ፣ እርሱም ብዙ ብልቶች ያሉትን አንድ አካል ለመሆን (ሮሜ 12፥ 4–5፤ 1 ቆሮ 12፥ 12–31) የሚያልፉበትን ሂደት ያሳያል። ይህም በሙላት ፍጻሜውን የሚያገኘው ጌታ ኢየሱስ “ለሁለተኛ ጊዜ ለመዳን በሚገለጥበት ጊዜ” ነው። (ዕብ 9፥ 28)
ጳውሎስ ያ የበሰበሰ የአሮጌው ኪዳን ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ እና አዲሱ የዘላለም ሕይወት የቃል ኪዳን ዘመን በቅርቡ እንደሚጀምር እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ በ30 ዓ.ም አካባቢ የአሮጌው የቃል ኪዳን ዘመን በዚያው አንድ ትውልድ ውስጥ የሚያከትም እንደሆነ ተናግሮ ነበርና ነው (ማቴ. 24፥ 3፣ 34)። ስለዚህ፣ ጳውሎስ የሮሜ መልዕክቱን በ58 ዓ.ም እየጻፈ በነበረበት ወቅት፣ ያ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል የጠቀሰው ዘመን ወደ ፍጻሜው መጨረሻ እየተቃረበ መሆኑን ተረድቷል። በመሆኑም ጳውሎስ የአሮጌው ኪዳን ፍጻሜ በቅርቡ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። ጳውሎስና ወንድሞቹም ያንን ፍጻሜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር (ሮሜ 8፥ 23)።
፭. ጌዜ አመልካች ንግግሮች፦ በመላው የሮሜ መልዕክት ውስጥ ጊዜ አመላካች የሆኑ ንግግሮች፤ ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ ይህን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ በርካታ መግለጫዎችን ያቀርባል። ለምሳሌ፣ ከፍ ሲል እንደተገለጸው፣ “ፍጥረት” የተባሉት ጳውሎስ ራሱና አይሁድ ወንድሞቹ ቤዛነታቸውን ለማግኘት በናፍቆት ይጠባበቁ እንደነበር ተናግሯል (ሮሜ 8፥ 23)። በናፍቆት የመጠባበቃቸው ምክንያትም በቅርቡ እንደሚፈጸም በማወቃቸው ነው። ጳውሎስ እዚህ ላይ የእርግዝና ዘይቤን ተጠቅሞ ስለ ምጥ ይናገራል (ሮሜ 8፥ 23)፥ ይህም በቅርቡ የሚወለድ ልጅ መኖሩን ያመለክታል። በዚህ ሁኔታ፣ ይህ የልደቱ ምጥ በቅርቡ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን፣ የመቤዠት ዘመን/ የመዳን ዘመን ሊወለድ መሆኑን ያመለክታል።
ጳውሎስ ቁጥር 11 ላይ ከፍ ሲል፡- “ለእኛም ሊገለጥ ካለው ክብር ጋር ቢነጻጸር ይህ የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ” ( ሮሜ 8፥ 11) ማለቱን እዩ። "ሊገለጥ" ማለት በቅርቡ ማለት ነው! ከጥቂት ምዕራፎች በኋላም፣ ጳውሎስ፣ “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ጊዜ አሁን ነው...ሌሊቱም አልፎአል ቀኑም ቀርቦአል” (ሮሜ 13፥ 11-12) እያለ ይናገራል። "ቀርቧል" ማለት "ሊሆን ነው" ማለት ነው! በሮሜ ውስጥ ያሉት እነዚህ ሁሉ የጊዜ መግለጫዎች ጳውሎስ በቅርቡ መቤዠትን/አዲሱን ፍጥረት እንደሚጠብቅ ያሳያሉ።
፮. የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አጠቃላይ ትንሳኤ፦ ጳውሎስ ስለ መንቃት ወይም መነሳት “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ጊዜ አሁን ነው… ሌሊቱ አልፏል ቀኑም ቀርቦአል” (ሮሜ 13፡11–12)፣ ሲል የተናገረውን ቃል አስተውሉ። በርካታ የቃሉ ተርጓሚዎች እንዳመለከቱት ከሆነ ጳውሎስ እዚህ ላይ ስለ አጠቃላይ ትንሣኤ የትንቢተ ዳንኤልን ቃል እያስተጋባ ነው፣ እርሱም :- “በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹም ወደ ዘላለም ሕይወት እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና” (ዳንኤል 12፥ 2) ይላል። ጳውሎስ ይህንን የብሉይ ኪዳንን ክፍል አንስቶ “ከእንቅልፍ የምትነሡበት” በማለት ስለ ትንሣኤ የጠቀሰበት ምክንያት በመጨረሻም አሁን ሊፈጸም የቀረበበት ወቅት በመሆኑ ነው! በሌላ አነጋገር፣ “ፍጥረት”፣ እርሱም የእስራኤል ጻድቃን ቅሬታዎች ሊነሱ ወይም ቤዛነታቸውን ሊቀበሉ ጊዜው ደርሶ ነበር ማለት ነው።
ኤፍ ኤፍ ብሩስ በዚህ ጥቅስ ላይ ማብራርያ ሲሰጡ የሚሉትን ተመልከቱ:- “ከእንቅልፍ ለመነሳት ጊዜው አሁን ነው። ይህ መንፈሳዊ የመንቃት ተግባር በመላው ሐዋርያዊ ትምህርት ውስጥ ያለማቋረጥ የሚያዝዘው ጉዳይ ነበር፤ ለምሳሌ 1 ተሰሎንቄ 5፥ 4 ላይ ያለውን ተመልከቱ። “ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን አሁን ቅርብ ነው” ሲልም እዚህ ላይ " መዳን" የተባለው ጉዳይ ሙላቱና ፍጻሜው የሚታዩውና የሚጠበቀው ለእነርሱ ሊመጣ ባለው የወደፊቱ ጊዜ ውስጥ ነው። ሮሜ 8፥ 23 ላይ በተነገረው መሠረት አማኞች የሚጠብቁት የሰውነታቸው ቤዛ ልጅነትን ነው። እንደ 1ጴጥ 1፥ 5 ከሆነ የዚህም “መዳን ፍጻሜ ክርስቶስ ሲገለጥ በክብር የሚገለጥ ለእነርሱ የተጠበቀና የተዘጋጀ የመጨረሻው ዘመን’ መዳን ነው፤ ዕብራውያን 9፥ 28 ላይ ያለውም ከዚሁ ጋር ይስማማል።[F.F. Bruce: Tyndale New Testament Commentaries; Romans. Inter-Varsity Press, 1963. P 242]
እንግዲህ ጳውሎስ በዚህ እየተናገረ ያለው ይኸንንው ርዕሰ ጉዳይ ነው:- “ፍጥረት” [ማለትም የአሮጌው ኪዳን እስራኤል] “ከጥፋት ባርነት” [ማለትም ወደ መበስበስ/ ወደ ሞት ከሚያደርሰው ከሕጕ ባርነት፣] ነፃ ወጥቶ ለእግዚአብሄር ልጆች ወደሚሆን የክብር ነፃነት [ይኸውም ወደ ኃጢአት ስርየት፣ እርሱም በክርስቶስ ወደ ሆነ ነፃነት፣ እርሱም የዘላለም ሕይወት ደስታ]” የሚደርስበት ነው። ከፍ ሲል ሮሜ. 8፥ 21፣ ላይ ለማመልከት የተሞከረውም ይኸንንው ነው።
ይህ ደግሞ ጳውሎስ ቀደም ሲል በዚሁ የሮሜ መልዕክቱ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 1-11 ላይ ከተናገረው ነገር ጋር ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይን የሚጋራ ነው፤ ይኸውም ጳውሎስ ቀድሞ በሥጋ (በሕጕ) ይመላለሱ የነበሩትን፥ አሁን ግን በመንፈስ የሚመላለሱትን የእግዚአብሔርን ልጆች መንፈሳዊ ለውጥ ሲናገር ያነሳው ጉዳይ ነው። ( ሮሜ. 8፥ 1 ተመልከቱ)። መላው የሮሜ ምእራፍ 8 የሚያወራው ስለ መንፈሳዊ ለውጥ ነው እንጂ ስለ ግዑዙ ዐለም ወይም ስለ ፕላኔት ምድር ለውጥ የሚናገር አይደለም። የተሻለ ሥጋዊ ፕላኔት ሊኖረን የሚችለው በርግጥም በመንፈስ የተለወጡ ሰዎች በምድር ላይ ሲበዙ ነው፤ ወንጌልን ማዳረስ ያለብንም ለዚህ ነው።
፯. የወሊዱ ምጥ፦ ጳውሎስ ስለዚህ ምጥ ሲናገር፡ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በመቃተትና በምጥ ይኖራል” (ሮሜ. 8፥ 22) ሲል የተናገረውን ተጠግተን እንመልከት። ጌታ ኢየሱስም በደብረ ዘይቱ ተራራ ፍካሬው ስለዚሁ የወሊድ ምጥ አይነት የመከራ ወቅት አስቀድሞ (በ33 ዓ.ም.) ደቀ መዛሙርቱ ስለ መቅደሱ መጥፋትና ስለ አሮጌው የቃል ኪዳን ዘመን ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ (ማቴ. 24፥ 3) ይህንንም በግልጽ ተናግሯል፤ እንዲህ ሲል፦ “ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው” (ማቴዎስ 24፥ 5-8)።
ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ የሚናገሩት ስለ አንዱ ዓይነት “ምጥ” ነው! “በምጥ መኖሩ”፣ ምጥ በግሪኩ sunodino ነው። ትርጉሙም በህመም መሰቃየት ነው። የአዲሱ ኪዳን ዘመን ውልደት ልክ እንደ ልጅ መውለድ የስቃይና የህመም ሂደት ነበረበት። አዲሱ የቃል ኪዳን ሥርዓት ከአሮጌው ሥርዓት በእጅጉ የሚለይ ሲሆን፣ በውስጡም ትልቅ ለውጦች እንዳሉትና ከለውጡ ጋር ተያይዞም ብዙ ሕመምና ተቃውሞ እንደሚኖር ማሰብ ያስፈልጋል። ይህ ምጥ የአዲሱን ዓለም ልደትና የልደቱን ምጥ ለማሳየትና ለመግለጥ የጊዜውንም አስጨናቂነት ለማመልከት ያገለግላል። በወሊድ ወቅት የልጁ ከማህጸን መውጣት እየቀረበ በሄደ ቁጥር የወሊዱ ምጥ እየጨመረ መሄዱ እርግጥ ነው። ምጥም የከፋ ህመምና ስቃይን ለማሳየት ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው።
በአይሁድ እምነት መሰረት መሲሃዊው የእስራኤል መንግስት ከመገለጡ አስቀድሞ እስራኤል በከባድ የመከራ ጊዜ ውስጥ እንደምታልፍ ይጠበቃል። ዊልያም ባርክሌይ “ጊዜ በአይሁዶች መረዳት ይህ የአሁኑ ዘመን እና የሚመጣው (ሊመጣ ያለው) ዘመን በሚል በሁለት ታላላቅ ምድብ ይከፈላል። ይህ የአሁኑ ዘመን የተሰኘው የጊዜ ምድብ ሙሉ በሙሉ መጥፎ እና ከሰው ልጆች የተሃድሶ ተስፋ ርቆ ያለ ነው፤ ጥገናዊ ለውጥ ሊደረግለት የሚችለውም በእግዚአብሔር ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ሊመጣ ያለውን አዲሱን ዘመን ሲያመጣው ያኔ ወርቃማው ዘመን ይገለጣል። ነገር ግን ይህ የአሁኑ ዘመን በተባለውና ሊመጣ ያለው ዘመን በተባለው በነዚህ ሁለት ዘመናት መካከል ልክ አዲስ ዘመን ሊወለድ ምጥ እንደሚፋፋም ሁሉ የሚያስጨንቅና የሚያስፈራ፣ ረብሻና ብጥብጥ ያለበት ነው። ያኔም የግዚአብሔር ቀን እየተባለ የሚጠራው ከባድ ክፍለ ጊዜ ይመጣል” ሲሉ ይጽፋሉ። [William Barclay; The Daily Study Bible Series: The Letter to the Romans. The Westminster press. pp 108-109]
እንግዲህ ይህ ምጥ በሚል የቀረበው ምሳሌአዊ ገለጻ የሚያገለግለው የመሲሃዊውን ዘመን ልደት አስጨናቂ ጊዜ ለማሳየት ነው፤ ይህ ወቅት ግን ፍጥረት የሚታደስበት አይነተኛ ጊዜ ነው። እስቲ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ተመልከቱ፦
ኢሳይያስ 26፥ 16-18 “አቤቱ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሰጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ። የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮኽ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል። እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላደረግነም፤ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ።”
ሚክያስ 4፥ 9-10 “አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን? የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፤ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።”
በነዚህ ሁለት ምንባባት የምናየው ምጥ ላይ ያለችው እስራኤል መሆንዋን ነው። ጳውሎስም ባነሳነው የሮሜ መልዕክቱ የሚጠቀምባቸው ቃላት ሁሉም ከእስራኤል ጋር የተገናኙ ናቸው። እንግዲህ እስራኤል የመሲሃዊውን መንግስት ውልደት የምትጠባበቅ ምጥ የደረሰባት ፍጥረት ናት፤ አዲሱ አለም ሊወለድ በአሮጌው አለም እስራኤል ላይ የደረሰውን አስጨናቂ ጊዜ ለማመልከት አገልግሏል እንጂ ግዑዝ አለም ያምጣል ብሎ ማሰብ በእውነት ቃሉን አለመረዳት ነው።
፰. የ”አሁን” በኩራት፦ “ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ…” አስተውሉ ይህ “አሁን” የመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን አሁን ነው እንጂ የእኔና የእናንተ አሁን አይደለም። “ራሳችን ደግሞ” (እኛም ራሳችን) የተባሉትም ጳውሎስና የሮሜ ክርስቲያኖች ማለትም በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ክርስቶስን ተቀብለው የእስራኤልን መዳን የሚጠባበቁ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳንን ነው፤ እነርሱም “የመንፈስ በኩራት” የነበራቸው ናቸው። መንፈስ የሆነው ብኩርና ወይም በኩራት የሆነው መንፈስ እንደማለት ነው። ያን መንፈስ በመጀመሪያ የተቀበሉት ደግሞ አይሁድ ክርስቲያኖች ነበሩ። ምጡም መቃተቱም የእነርሱና የትውልዳቸው ነበር።
ሮሜ 8 በግልጽ እንደሚያስተምረው መንፈስ የተሰጠው እንደመያዣ ሆኖ ነው፤ መያዣም በግሪኩ arrhabon ነው። ይኸውም ለግዥ የሚከፈል ቅድመ ክፍያ፣ ቀሪውን ፈጽሞ ለማስረከብ አስቀድሞ የሚሰጥ ቀብድ፣ ማስተማመኛ ወይም መተማመኛ ነው። የእስራኤል ልጆች የሚሰበስቡትን የመከሩን በኩራት /የመጀመርያ ፍሬ/ መስዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ በህጉ ታዘው ነበር (ዘጸ 23፥ 19፤ ነህ 10፥ 35)። ይህ ስጦታ ዩሚያረጋግጠው መከሩ ሁሉ ከእርሱ እንደሆነና በእውነትም ሁሉም የእርሱ እንደሆነ ነው። በኩራቱን በእግዚአብሔር ፊት ሲያቀርቡ ቀሪውን መከር እንደሚሰቡስቡ በማመን ያቀርባሉ። ልክ እንዲሁ እግዚአብሔር የመንፈስን ስጦታ ሲሰጣቸው ያ በኩራት ነበር፣ የመዳንን ሂደት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽመውም ይህ ማስተማመኛና መያዣቸው ነበር።
ያ የመዳን ሂደት ፍጻሜ ደግሞ “የልጅነታቸው መገለጥ” ነው። ይህም ከእስራኤል ጋር የተገናኘ መሆኑን ጳውሎስ በዚሁ አውድ ሮሜ ምዕራፍ 9 ላይ ይናገራል “እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና” (ሮሜ 9፥ 4)። ተመልከቱ ልጅነት ከመሰረቱ የእስራኤል ተስፋ ነበር፣ ቤተክርስትያን እርስዋም አዲሲቱና እውነተኛይቱ እስራኤል ያንን ልጅነት ተቀብላለች።
“የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት” ሲል ልጅነት ወይም ልጅ የመሆን ሙሉ መገለጥ ከሰውነት ቤዛነት ጋር መመሳሰሉን ያሳያል። በሮሜ መጽሐፍ ከምዕራፍ 3 ቁጥር 24 በኋላ ይህ ቤዛነት የሚለው ቃል እንደገና ጥቅም ላይ የዋለው በምዕራፍ 8 ቁጥር 23 ላይ መሆኑን ተመልከቱ። ይህ ቤዛነት የተሰኘ ጽንሰ አሳብ የሚያስታውሰን ደግሞ በዚሁ ምንባብ ውስጥ ሲንሸራሸር የነበረውን የዘጸዓትን ርዕሰ ጉዳይ ነው። ይህም የሰውነት ቤዛነት የትንሣኤ ሕይወት ነው። እኔ በግሌ ያገላበጥኳቸው ኮሜንታተሮችም ይህንንው ያመሳክራሉ።
፱. ስነፍጻሜአዊ መጠባበቅ፦ በቁጥር 23 ላይ የተነገረውን ስነፍጻሜአዊ መጠባበቅ የሚያብራራው ቀጥሎ በቁጥር 24 እና 25 ላይ የተሰጠው አጽንኦት ነው። እርሱ ላይ ጥቂት ነገር ልበልና ወደ ማጠቃለያዬ አልፋለሁ። ቃሉም እንዲህ ይላል፦ “በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።” ምን ማለት ነው? “ፍጥረት” እና “በኩራት” የሆኑ ምዕመናን በናፍቆት የሚጠብቁት ተስፋ እርሱም ድነታቸው፣ ያኔ ጳውሎስ ይህንን የሮሜ መልዕክት ገና እየጻፈ በነበረበት ጊዜም እንኳ ለጳውሎስና ለሮሜ ክርስቲያኖች ገና ወደፊት ያለ፣ በሙላትና በፍጹምነት ያላገኙት ነገር ነበር ማለት ነው። “ድነናል” ግን “በተስፋ” ነው ይላል። እዚህ ላይ ጳውሎስ መዳንን በኃላፊ ጊዜ ግስ ያስቀምጠውና ተስፋን ያመጣል። እነርሱ የዳኑት ተስፋን አምነው ነው፤ ስለዚህም እነርሱ የነበራቸው የመዳን ተስፋ ነበር። ይህም ተስፋ የሚፈጸመው በዘመናቸውና በትውልዳቸው ውስጥ ነበር።
“ተስፋ”፤ መዳንና ተስፋ በጳውሎስ መልዕክቶች ውስጥ የተቆራኙ ናቸው። ቃሉም በግሪኩ elpis ነውና በሮሜ መልዕክት ውስጥ ለ14 ጊዜ ያሃ ተጠቅሷል፤ የሚያመለክተውም በታመነ ቃል ላይ ቆሞ ስለመጻኢው መተማመንን እና እርግጠኝነትን ነው። በዘመናችን ተስፋን አዲስ ኪዳን ከሚጠቀምበት አገባብ በተለየ መልኩ በርካቶች ሲጠቀሙበት ስለምናይ እውነተኛውን ተስፋ ለዘመኑ ሰው ማስረዳት ያስቸግራል። ስለዚህም አዲስ ኪዳን የሚያስቱምረው ተስፋ ለዘመነኛው አማኝ ነኝ ባይ ጸጉረ ልውጥ (ኤልያን) ሆኖበታል። ተስፋ በአዲስ ኪዳን ጠቀሜታው ስለወደፊቱ ዘላለማዊ ዕድል ፍጹም የሆነ እርግጠኝነትን፣ ጓግቶ የመጠበቅ ዝንባሌን፣ እግዚአብሔር የሰጠው ቃሉ ጽኑ ተስፋ ሆኖ ሊፈጸም እንደሚችል መተማመንን ያመለክታል።
ጳውሎስ አዘውትሮ ስለ መዳን ሲናገር በመጻኢ ጊዜ ግስ ወደፊት እየጠበቀ ማቅረቡን ግን ልብ በሉ፣ ለምሳሌ ሮሜ 5፥ 9-10 “ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤” ይላል። በንባብ ክፍላችን ውስጥ ድነትን በመጻኢ ጊዜ ወርድና ስፋቱ እንደሚያቀርበው ሁሉ በሌሎቹም መልእክቶች ይህንንም ያንጸባርቃል (ለምሳሌ 1ተሰሎንቄ 5፥ 8 ላይ ተመልከቱ)።
ማጠቃለያ፦
ጌታ ኢየሱስ በ30 ዓ.ም. አካባቢ ይህንን ጉዳይ ሲናገር - ከአሮጌው የቃል ኪዳን ዘመን ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን የሚደረገው ይህ ለውጥ- በአንድ ትውልድ ውስጥ እንደሚሆን መናገሩንና ያም ሂደት በመከራ ምጥ የታጀበ እንደሚሆን ማስታወቁን አስታውሱ (ማቴ. 24፥ 3፣ 8፣ 34)። ጳውሎስም ገና በ58 ዓ.ም ላይ ሆኖ ይህንን መልዕክት ለሮሜ ሰዎች እየጻፋ በነበረበት ወቅት የምጡ ጊዜ አብቅቶ ይህ አዲስ ልደት በቅርቡ እንደሚከሰት አውቆ ነበር። ስለዚህም ከፍ ሲል የጠቃቀስናቸውን እነዚያን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ የሮሜ መጽሐፍ ንግግሮቹን ተከትለን በሮሜ 8 ላይ የቀረበውን ፍጥረት ከጥፋት ባርነት ነጻ ስለሚሆንበት ሁኔታና ጊዜ ስንመረምር፣ ሁኔታው የእስራኤል መታደስ፣ ጊዜውም ጌታ ተመልሶ በሚመጣበት በ70 አ.ም እንደሆነ እናስተውላለን። ጳውሎስም የተስፋው ፍጻሜ ጊዜው እንደደረሰ ይህንን ያወቀው ከኢየሱስ ትምህርት መሆኑ ግልጽ ነው።
እንግዲህ ልብ በሉ፣ ተማሩም። ተረት ካቀበላችሁ አጉራ ዘለል፣ አውድ ዘለል ትርጉምም ተለዩ። ሮሜ 8 ስለ አዲስ ተፈጥሮ ወይም ግዑዝ አለም የሚናገር ክፍል እንደሆነ በመሰለን መጠንና እንደዚያ ተርጉምን ለማስተማር በደፈርን መጠን ግራ የገባቸውና፣ የእግዚአብሔርን ማህበር ግራ የሚያጋቡ ሰባኪዎች እንሆናለን። የመጨረሻው ዘመን አስተማሪዎች ነን የምትሉ፣ ስለ ጌታ ዳግም ምጽአት ተንታኞች ነን የምትሉ፣ ሲላችሁ ስለ ስለአርማጌዶን፣ ስለምጻት ቀን ስለ ኤክሊፕስና ኮስሞስ ረብሻ እያወራችሁ ስለ አለም ጥፋትና ስለ ምድር ውድመት ሽብር እየተነተናችሁ፣ ሲላችሁ ደግሞ ስለምትታደስ ፕላኔት ምድር የሌለ ነገር እየዘባረቃችሁ መያዣና መጨበጫ በሌለው፣ ቅጥ አንባሩ በጠፋ ስነ ፍጻሜ የምታምታቱ እነ ንዳው በዘጠና እስቲ ጥቂት እንኳ ነገረ ፍጻሜን አንብቡ። አዲሱ ፍጥረት የሚለው የሚያመለክተው የአዲሱን ቃል ኪዳን ክርስቲያኖች ነው እንጂ አዲስ ግዑዝ ዓለም ወይም ፕላኔት ምድር ፈጽሞ አይደለም—በክርስቶስ የሆነው አዲሱ ፍጥረት ደግሞ የተወለደው የምጡ ጊዜ አብቅቶ ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነው!
ግዛቸው።