“ቶሎ” እና የክርስቶስ ታማኝነት
“እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ”
(ራእይ 3፥ 11)
ኢየሱስ በቶሎ የሚመጣው ለማን ነው? “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ” ሲል ለገራቸው ብቻ አይደለምን፣ ወይንስ በየዘመናቱ፣ ለትውልድ ሁሉ ነው? ሁልጊዜስ በቶሎ ይመጣልን?
“በቶሎ” ማለት ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ማለት ነው፣ ብላችሁ የምታስቡና የምታነቡ ከሆነ፣ እንግዲያውስ በቅድሚያ የሚያስፈልጋችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ሳይሆን፣ የሚያስፈልጋችሁ የቋንቋ ስርዓት ማወቅ ነው፤ የሚያስፈልጋችሁ የመዝገበ ቃላትና የሰዋሰው ትምህርት ነው።
ሁልጊዜ ሰዎች ኢየሱስ “በቶሎ ይመጣል” ሲሉ ስሰማ በውስጤ እገረማለሁ፣ ጥያቄም ያጭርብኛል። በእርግጥ እኔም ከተጻፈው ጋር እየተጣላሁ እንደዚያ ከሚሉ ወገን ነበርኩ። በውኑ አሁንም ድረስ ያለ ጥያቄ ይህንን የሚያስተጋቡ ጥቂቶች አይደሉም። ይህንን የምታነቡ ወገኖች፣ ኢየሱስ “በቶሎ ይመጣል” የሚለውን መግለጫ ስትሰሙ ትንሽም ቢሆን ጥያቄ አይፈጥርባችሁምን? እንደውም አንዳንድ ክርስቲያኖችማ ላለፉት 2,000 ዓመታት ኢየሱስን “በቅርቡ” እንደሚመለስ በየዘመኑ ትንበያቸውን ሲናገሩ ቆይተዋል። ለመሆኑ ይህ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን “ቶሎ” ለዛሬ ዘመን ይቆጠራልን?
የኢየሱስ “በቶሎ” ተመልሶ መምጣት በራእይ ምዕራፍ 1፣ ምዕራፍ 3 እና ምዕራፍ 22 ላይ እንደተጠቀሰው፣ ይህም ኢየሱስ ራሱ ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለዮሐንስ ባሳየው ራእይ “በቶሎ እመጣለሁ” ሲል የተናገረው ቃል እንደሆነ እናውቃለን። ብዙዎች ግን ይህንን ሲያነቡ የሚገባቸው ቀጥተኛው ትርጉም ሳይሆን፣ የሚረዱት ተቃራኒውን ነው። እስቲ አስቡት አንድ ቋንቋ ማንኛውም አይነት ትርጉም ሊኖረው ይችላልን? አንድ ነገር ራሱን ማለት ነው እንጂ፣ ተቃራኒውን ማለት አይደለም። ‘በቅርቡ’ ማለትን ‘ሩቅ’ ማለት ነው ልንል ይቻለናልን? ፍቅር ማለትስ ጥላቻ ሊሆን ይችላልን? ደስተኛ ማለት ሀዘንተኛ ማለት ነውን? ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን ላይ በቅርቡ ወይም በቶሎ እንደሚመጣ ተናግሯል፣ “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ” የሚለውን ይህንን ንግግሩን አንብቤ ሳበቃ፣ የለም ይህ ይዘገያል ማለት ነው ብዬ ብረዳው ከዚህ የበለጠ የሚታዘንለትና የሚያስቆጣ ድንቁርናስ ይኖራልን? ይህ ግን ድንቁርና ብቻ አይደለም፣ ኃሰትን የማመን ኃጢአትም ጭምር ነው እንጂ። “እናንተ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ” እንደተባለ፣ የፈለጋችሁትን ለማመን ትችላላችሁ፤ ሲያሻችሁም “እነሆ በቶሎ ብዬ እመጣለሁ” የሚለውን የታመነ ቃሉን ለውጣችሁ፣ “እነሆ ቆየት ብዬ እመጣለሁ” ብላችሁ ልታኑቡትም ትችላላችሁ። ይህ ግን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚፈጸም የትርጉም ወንጀል ነው። እኔ ግን በበኩሌ ይህንን ወንጀል መጸየፍ ከጀመርሁ ቆየሁ። ከልቤ የማምነውም ይኸው የቶሎ መምጣት ትንቢቱ ተፈጽሟል ብዬ ነው። በእርግጥ እናንተ እንደሚመስላችሁ፣ ቃሉንም ለውጣችሁ “እነሆ ቆየት ብዬ እመጣለሁ” ስትሉ እንደምታነቡት አይነት ጌታችን ተናግሮ ቢሆን ኖሮ እንኳ፣ እስካሁንም በዚህ ቃሉ መሰረት ያልመጣ ከሆነ ይህን ያህል ዘመን ሳይመጣ መቆየቱ ራሱ ታማኝ አያደርገውም።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ “ቶሎ” የሚለው ቃል ከጊዜ አንጻር በመዝገበ ቃላታዊ ትርጉሙ በቅርቡ ማለት እንደሆነ እንዴት እናውቃለን? መልስ፦ ምክንያቱም ይህንን የጊዜ ወሰን የሚያረጋግጡ ከ100 በላይ የሆኑ ምንባባት በአዲስ ኪዳን ያሉ በመሆናቸው ነው። የኢየሱስ መምጣት በግሪኩ “ፓውሮዥያ” ሲተረጎም “ውጤታማ የሆነ መለኮታዊ መገኘት” ማለት ነው፤ ይኸውም፣ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ ከነበሩት ተከታዮቹና ተቃዋሚዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ገና በሕይወት እያሉ የሚሆን እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነው፤ ምሳሌ፡ ማቴዎስ 10፥ 23፤ 16፥ 27-28፤ 24፥ 29-34፤ 26፥ 64 ተመልከቱ፣ እንግዲህ "ቶሎ" ማለት ምንም መቀባባት ሳያስፈልገው ትርጉሙና ተዛማጅነቱ የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ጠቋሚ በሆኑ ምንባባት በእነዚህ ምሳሌዎች በተገለጠው አይነት ነው። እደግመዋለሁ፣ እነዚህ ጥቅሶች የደቀ መዛሙርቱ ትውልድ ሳያልፍ ሊፈጸም ያለውን ምጽአቱን የሚጠቁሙ ጊዜ አመልካች ምንባባት መሆናቸውን ካስተዋልን፣ የራእዩ ቶሎ ሲተረጎምም ያው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው።
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ፣ የኢየሱስ ዳግመኛ ምጽአት “በቶሎ” የሚሆን እንደሆነ ሲነገር፣ ይህንን የጊዜ ወሰን ለማመልከት መጽሐፉ የተለያዩ ቃላትንና ሀረጎችን በግልጽ እንደሚጠቅም በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፤ ለምሳሌ፣ “ይኾን ዘንድ ያለው”፣ “በቶሎ ሊሆን የተገባው” እንዲሁም “ዘመኑ ቀርቦአል” በሚል ንግግር የበለጠ ተብራርቷል። እንግዲህ "ቶሎ" ማለት ትርጉሙ ይኸው ነው። “ቶሎ” የሚለውን ቃል ከጊዜ አንጻር በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ አድርጎ በመተርጎም ቅዱሳት መጻህፍትን የማጣመም ኃጢአት ከእኛ ይራቅ።
የራእይ መጽሐፍ መግቢያ በራእዩ ውስጥ የተገለጡት ጉዳዮች ሊሆኑ ያለበትን ጊዜ ሲያመለክት “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባው” (ራእይ 1፥ 1) ማለቱ፣ ቶሎነቱ ለዮሐንስና ለበኩረ ተደራስያኑ መሆኑን እንጂ፣ ተቃራኒውን ማለትም፣ እነርሱ ካለፉ ከዘመናት በኋላ ስለሚሆን ነገር አለመሆኑ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ ቶሎ ካለ ያው ከጊዜ አንጻር የበኩረ ተደራሲያኑን ቅርብ ዘመን፣ የእነርሱን ቶሎ የሚያመለክት ነው (ቁ 19 እና 22፥ 6)። በአንጻሩ ደግሞ የሩቅ ዘመን ክንውንን ሲያመለክት ልክ በዳንኤል 2፥ 28-30 እንደተጻፈው “በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን” በማለት፣ ክንውኑ ይኸውም ከጊዜ አንጻር ይሆናል የተባለው ጉዳይ የፍጻሜውን ቀጠሮ ከበኩረ ተደራስያኑ አይነተኛ ዘመን አርቆ የሚያስቀምጠው መሆኑን መርሳት የለብንም።
ጌታ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ራት ተቀምጠው ሳሉ እግራቸውን ካጠበላቸው በኋላ ከእነርሱ አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ነገራቸው። ከጥቂት ንግግሮች በኋላም ለአስቆሮቱ ይሁዳ ቁራሽ አጥቅሶ ሰጠውና “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው” (ዮሐንስ 13፥ 27) ይላል። ከዚያ በኋላ ይሁዳ ጌታውን ለመሸጥ አመቺ ጊዜ እየፈለገ ብዙ ሺህ አመታት ቆይቷል ወይ? በጭራሽ፣ ያ “ቶሎ” የሚቆጠረው ይሁዳ ቁራሽ ከተቀበለበት ሰላሳ ዲናር እስከተቀበለበት ድረስ ባለው ጊዜ ነው። በጣም አጭር ጊዜ።
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ጢሞቴዎስን ፈጥኖ ሊልክላቸው እንደሚፈልግ ሲነግራቸው (ፊልጵስዩስ 2፥ 19) ምን ማለቱ ነበር? “እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤” (ቁጥር 23) ሲል ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ጢሞቴዎስን “በኋለኛው ዘመን” እልክላችኋለሁ ማለቱ ነበርን? በጭራሽ እንደዚያ ማለቱ አይደለም። ትጉህ የሆነ የቃሉ ተማሪ “ቶሎ” የተሰኘውን ይህንን አንድ ቃል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከጊዜ አንጻር እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ መረዳት ከፈለገ ቀላሉ ነገር ጥቅስ ማውጫ (Concordance) ይዞ የቃሉን አገባብ እንዲመለከት እመክራለሁ።
በነገረ ፍጻሜ አስተምህሯቸው መጻኢያን የሆኑ ተርጓሚዎች ብዙውን ጊዜ አቋማቸውን ሲከላከሉ፦ “ኢየሱስ እስካሁን ድረስ ገና እንዳልተመለሰ ስለምናውቅ ይህ “ቶሎ” የሚለው ቃል ከዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ አንጻር ወይ “በኋለኛው ዘመን የሚሆን” ማለቱ ነው፣ አልያም መደበኛ ትርጉም የለውም” ሲሉ የዞረበት አይነት መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ይህ መከራከሪያ ግን “ጥያቄውን መልሶ መጠየቅ” የሚባል ኢ-አመክንዮአዊ ስህተት የሚፈጸምበት ነው፤ ጥያቄውን መጠየቅ ማለት የክርክሩን ጭብጥ የሚደመድመውን እውነት የሚያድበሰብሱበት ወይም የሚያጣጥሉበ ከምክንያታዊነት የወደቀ ስህተት ነው። ጥያቄውን የሚያነሱ ክርክሮች በውዝግቡ ውስጥ ያሉትን ትክክለኛ ጭብጦች ሆን ብለው ለማድበስበስ የሚሰሩ ሲሆን እንዲህ ያሉ ግራ ገብ የሆኑ ክርክሮችም እንደ ዙሪያ ጥምጥም አመክንዮ ሊታዩ ይችላሉ። ይህ ማለት አንድ ሰው ጉዳዩን በቀጥተኛ አመክንዮ እውነት መሆኑን ከማረጋገጥ ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም ለመሄድ እየሞከረ እውነታውን ያድበሰብሰዋል ማለት ነው። በቃሉ ንጹህ ትምህርት ላይ በአመጽ የሚደረግ እንዲህ ያለ ድርቅናና ግትርነት ደግሞ ይገድልሃል እንጂ አያለመልምህም።
መጽሐፍ ቅዱሴን ለመማር ጥረት ባደረግሁበት ዘመኔ እንደ መጻኢነት ያለ ግራ የገባው፣ አመክንዮአዊነትን የጣለና፣ ጊዜን የሚያሳክር አስተምህሮ ገጥሞኝ አያውቅም። ጆሮህን አሳየኝ ሲባል ሁለት እጆቹን በማጅራቱ በኩል አጠላልፎ ጆሮው ላይ ለመድረስ እንደሚሞክር ልብ አውልቅ “ጅል” ይቅርታ ልጅ ለማለት ነው፣ መጻኢነትም እንዲሁ ነው። ተመልከቱ፣ “ቶሎ” ትርጉሙ ተለውጧል በሚል፣ በዮሐንስ ራእይ “ቶሎ ብዬ እመጣለሁ” ያለው የኢየሱስ ቃል እስካሁን አልተፈጸመም ብለን የምናምን ከሆነ፣ እንግዲያውስ አስቆሮቱ ይሁዳ ቶሎ እንዲያደርገው የተነገረው የኢየሱስ ታልፎ መሰጠትም ሆነ፣ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ ፊልጵስዩስ ቶሎ ለመላክ የሰጠው ተስፋ ገና አልተፈጸመም ማለት ይሆናል።
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “ቶሎ” ወይም “ፈጥኖ” ተብለው የተተረጎሙ ሁለት ተመሳሳይ የግሪክ ቃላት አሉ።—ታኮስ (ራእይ 1፥ 1፤ 22፥ 6) እና ታኪ (ራእይ 22:፥ 7 ፣12፣ 20)። እነዚህ በመጽሐፉ መግቢያና መዝጊያ ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላት አንድ አይነት ስርወ ቃል ያላቸው ሲሆን ትርጉማቸውም ያው አንድ ሆኖ፣ ግልጽ የሆኑ ጊዜ አመልካች የሆኑ ቃላት ናቸው። ሊፈጸም የተገባውና የተነገረው ጉዳይ ከጊዜ አንጻር “ሳይዘገይ፣ በፍጥነት፣ በችኮላ፣ በቅርቡ ይፈጸማል።” ማለት ነው።
እነዚህ ቃላቶች እንደ ራዕይ መጽሐፍ ሁሉ በተቀረው የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ውስጥም ተመሳሳይ የሆነ ትርጉምና ጠቀሜታ አላቸው! ለምሳሌ ታኮስ የተሰኘውን የግሪክ ቃል በሉቃስ 18፥ 8 ላይ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ። በሐዋርያት ሥራ 12፥ 7፤ 22፥ 18፤ 25፥ 4። ያለውንም እንደ ምሳሌ ተመልከቱ፡-
“እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፦ ፈጥነህ (ታኮስ) ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።”(ሐዋርያት ሥራ 12፥ 7)
በማቴዎስ 5፥ 25፤ 28፥ 7፣ 8፤ በማርቆስ 16፥ 6 እና በዮሐንስ 11፥ 29 ውስጥ ደግሞ ታኪ የተሰኘውን ቃል እናገኛለን፤ ከእነርሱም ውስጥ አንዱ፡-
“ፈጥናችሁም (ታኪ) ሂዱና፦ ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ” (ማቴዎስ 28፥ 7)፣ የሚለው ነው።
የእነዚህ ቃላት አጠቃቀም ሁልጊዜም ቢሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ወጥነት ያለው ነው። በተከሰቱበትና ጥቅም ላይ በዋሉበት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሊፈጸሙ የተመደቡ ጉዳዮች ተሟልተው እስኪፈጸሙ ድረስ ረዘም ያለ ክፍለ ጊዜን የሚወስዱ አይደሉም ማለት ነው።
አንዳንድ ስለመጨረሻው ዘመን እናስተምራለን የሚሉ ሰባኪያን “በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነው” የሚለውን የጴጥሮስን ቃል በመጥቀስ፣ “ታኮስ” ከተሰኘው የግሪክ ቃል አጠቃቀምና ከአጠቃላይ ሁኔታው ሊሸውዱ እንደሚችሉ ያስባሉ። ያ ከሆነ፣ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ 3,000 ዓመታት ነበር የቆየው ማለት ነው? በጭራሽ እንደዚያ አይደለም። በራዕይ መጽሐፍ ላይ ምሁራዊ ምርምር ያደረጉ ኬኔት ጄንትሪ ስለዚህ ጉዳይ የሚከተለውን ብለዋል፡-
“በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጴጥሮስ በግልጽ እየተናገረ ያለው እግዚአብሔር አምላክ ጊዜን የሚመለከተው ወይም የሚቆጥረው ሰው ጊዜን ከሚያይበት አተያይ በተለየ መሆኑን ነው። ዮሐንስ ግን ንግግሩ ያ አልነበረምያ። ጊዜያዊ የሆኑ ወይም በጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የተመደቡ ጉዳዮችን አንስተን በእግዚአብሔር የጊዜ አቆጣጠር ውስጥ እያስገባን ልንተረጉማቸው አንችልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ጴጥሮስ ስለ እግዚአብሔር እየተናገረ ነው፣ ዮሐንስ ግን መመሪያዎችን ለሰዎች እየሰጠ ነው። ጴጥሮስ ስለ እግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ስለ ጊዜ ያለውን አተያይ በተመለከተ አጠቃላይ ሥነ-መለኮታዊ መግለጫን እየሰጠ ነው፤ ዮሐንስ ግን በአንድ ታሪካዊ ወቅት በነበሩ ሰዎች ሕይወት እየደረሰ ስላለና እየገጠማቸው ያለ መከራን አስመልክቶ ለሰዎች መመሪያን ይሰጣል። ስለ እግዚአብሔር የተነገሩ ሥነ-መለኮታዊ እውነቶችን አንስተን ለሰዎች በሰዎች ደረጃ ከሚሰጡ ታሪካዊ መመሪያዎች ጋር ማሳከርና ግራ ማጋባት የለብንም። በሦስተኛ ደረጃ፣ ጴጥሮስ አንዳንድ ትንቢቶች ገና ስላልተፈጸሙ ከመነሻው ውድቅ ናቸው የሚሉ የዘባቾችን ንግግር አንስቶ፤ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።”(2ጴጥሮስ 3፥ 3-4) ሲል ሃሳባቸውን በመቃወም በግልፅ እየተናገረ ነው። ጴጥሮስ በንግግሩ የእግዚአብሔር ፍርድ አስመልክቶ ለምን የዘገየ እንደመሰለ አንስቶ ይመሰክራል ፤ ዮሐንስ ግን በራእዩ እነዚያን በከፋ መከራ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች (ራሱንም ይጨምራል ራዕ 1፥ 9) ምን መጠበቅ እንዳለባቸው እያመለከታቸው ነው። “ትንቢቶቹም በቅርቡ ሊፈጸሙ ነው” ሲልም እየደጋገመ በተለያዩ መንገዶች ይናገራቸዋል።
ይህ ጉዳይ ትኩሳቱ እጅጉን የጋለ ነው፣ ቸል ብለን ብናልፈው እንኳ እስከ ጥግ ሄዶ እምነታችንና ለኢየሱስ ያለንን ቅንነታችንን ይበላል፦ የሚያስነሳውም ጥያቄ ኢየሱስ እውነተኛ ነቢይ ነበር ወይስ አይደለም? የሚል በቀላሉ ልናልፈው የማንችለውን ተግዳሮት ነው። ከኢየሱስ ጋር ስጓዝ በእውነት እርሱን እንደ እውነተኛ ነቢይ ነው የማየው፣ ወይንስ ኢየሱስ ቶሎ እመጣለሁ ሲል በንግግሩ ተሳስቶ ነበር? የሚበዙት ክርስቲያኖች “በቶሎ ተመልሼ እመጣለሁ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አሳስተው ተረድተውታል ማለት ነውን። እኔ እንደሚገባኝና ላስተባብለው እንደማይቻለኝ እውነት ከሆነ ጌታ ኢየሱስን እንደ እውነተኛ ነቢይና እንደ ብሩክ የእግዚአብሔር ልጅ ሊያከብረው የሚችል ብቸኛው የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የፕሪቴሪዝም አቋም ነው። ሌላው ሁሉ ትርኪ ምርኪ፣ ግራ ገብ የመጻኢነት ትምህርት ከሃዲዎችና ተቃዋሚዎች በክርስትና ላይ ለሚያነሱት ስድብና ትችት ዱላ አቀባይ ከመሆን አያልፍም።
ታዲያ ኢየሱስ በእርግጥ ተመልሶ የመጣው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንዶች በሕይወት እያሉ ነውን? ፍርጥም ብለን፣ አዎን!! ነው መልሳችን። ፕሪቴሪዝም በሚያስተምረው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት የሚስተጋባው የተፈጸመ ወንጌል ኢየሱስ አይሁዶችን ስለ ኃጢአታቸው ለመቅጣት፣ አዳኝ አድርገው ስላልተቀበሉትም ሊፈርድባቸው በ70 ዓ.ም ተመልሶ እንደመጣ (ማቴዎስ 23፥ 29-39) ነው።
ይህ አመጣጥ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን እንዴት በፍርድ ይመጣ እንደነበር ባለው አይነት የቀረበ ነው። እግዚአብሔር ያኔ ፍርዱን ሲያከናውን እርሱን ማንም በገሃድ አያየውም ነበር፤ ዳሩ ግን የፍርዱን ውጤትና ተጽዕኖ በጠላቶቹ ላይ ብዙ ጊዜ አሳይቶ ነበር። በዮሐንስ 5፥ 19-22 እንደተገለጠው፣ ኢየሱስ አብ እንዳለው አይነት የመፍረድ ስልጣን ተሰጥቶታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያኔ በነበሩት አህዛብና እስራኤል ላይ ለመፍረድ እግዚአብሔር ተቃዋሚ የሆኑ ሌሎች ጠላቶችን እያስነሳ ይጠቀም ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ጌታ ኢየሱስ በመለኮታዊ ሥልጣኑ የሮምን ጦር አሰልፎ ለጦርነት በማስከተት በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌምንና ቤተመቅደሱን አጠፋ።
እንግዲህ ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት ያለማቋረጥ ሁልጊዜ “ቶሎ ይመጣል” እያልን የከረምነው፣ ለወጋችንና ለልማዳችን ገዶን ቀጥተኛውን የቃሉን ትምህርት ለማስተባበል እየደፈርን ነው። ሰዎች ይህንን ማየት ለምን እንደተሳናቸው ባሰብኩት ቁጥር እገረማለሁ። ልማድና ወግ የጫነብንን ግግር ጨለማ የምንገላገልበት አይነተኛ መንገድ ግን ቃሉን እንደተጻፈ እንዲሁ በመቀበል ብቻ ነው። “ቶሎ” ማለት ትርጉሙና ተዛምዶው ሌላ ምንም ቅብ የሌለው፣ የክርስቶስንም ታማኝነት የሚያረጋግጥ ያው ቶሎ ነውና።
እንዲህ ያሉ አስተማሪ የነገረ ፍጻሜ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንበብ ቢያስፈልጋችሁ፣
http://gizachewkr.blogspot.com/?m=1
በሚል አድራሻ ወደ ብሎገሬ ጎራ በሉ።