Thursday, March 24, 2022

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ ፍጻሜ

የነገረ ፍጻሜ አጠቃላይ እይታ

(በዚህች አጭር ዳሰሳ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ጊዜው፣ ቋንቋው፣ እና አካባቢያዊ መልከዓ ምድሩ መሆናቸውን አንስተን እንመለከታለን)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ቀን፣ ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲናገር በትክክል ስለ ምን እየተናገረ ነው? የሚናገረውስ ስለ ነባራዊው ተዳሳሹ ግዑዝ ዓለም (ኮስሞስ/ግሎብ) ፍጻሜ ነውን፣ ስለጊዜ መጨረሻስ ነውን፣ ወይስ ስለ ሌላ ነገር መጨረሻ? ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት መጨረሻ ከነዚህ የተለየውን የሌላ ነገር መጨረሻን እንደሚያመለክት የዚህ ጽሁፍ ዋና ሃሳብ እንደሆነ ከመነሻዬ ልጠቁም እወዳለሁ። በማነሳቸውም ጉዳዮች ላይ እማኜ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንዲሆን እተጋለሁ፤ የተጻፈውም የጥሁፍ ዘለግታ ለማይፈሩ ነው።

፩. የነገረ ፍጻሜን ጥናት አንስተን ትንቢትን ስንመረምር ልናጤናቸው የሚገቡ ሶስት ጠቃሚ ነጥቦች ጊዜውን፣ ቋንቋውን እና መልከዓ ምድራዊውን አቀራረብ ነው። በተለይ ደግሞ ጊዜውን መረዳት ሁሉም ነገር ማለት ነው። ይህንን ማወቅ ወደ ትክክለኛው መረዳት ውስጥ ያስገባናል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉ ትንቢታዊ እና አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋዎች፣ ለምሳሌ  በደመና መምጣት፣ የፀሐይና የጨረቃ መጨለም፣ እንዲሁም የከዋክብት መውደቅ የመሳሰሉት ምስሎች በቀጥታ የተወሰዱት ከብሉይ ኪዳን የቅዱሳት መጻሕፍት የንግግርና የአጻጻፍ ዘቤ ነው። በመሰረታዊነት ይህንን ማወቅ ልማድ ካጠለቀብን የእስራት ካቴና እና በከንቱ አምልኮ ከሚፈጸም ራስን የማጥፋት መንፈሳዊና ማህበራዊ ቀውስ ይታደገናል። እንዲህ ያለው እብደት በታሪክ ውስጥ እንደነበር ጥቂቶቹን በማሳያነት ለመጥቀስ ያህል እንደ ጂም ጆንስ፣ ዴቪድ ቆሬሽ፣ ቻርለስ ማንሰን፣ ራንዲ ዌቨር (ይኸውም በሃል ሊንድሴ አስተምህሮ አነሳሽነት)፣ ዴቪድ በርግ ("የእግዚአብሔር ልጆች ነን" የሚሉ)፣ ሮለን ስቱዋርት፣  "የቀስተ ደመና ሰው"/"የዮሐንስ 3፡16 ሰው" በማለት ራሳቸውን የሚጠሩ፣ እንደ ማርሻል አፕልዋይት/"የገነት በር" ሲሉ ራሳቸውን የሰየሙ/ እንደ ሃሌ ቦፕ እና የጃፓኑ የምድር ውስጥ ባቡር ፈንጂ ጠማጆች በመሳሰሉት ዘንድ በስፋት ታይቷል። በመጨረሻም መልከዓ ምድራዊውን አካባቢ፣ ቦታውን እና ስፍራውን ማወቅ ትንቢትን በመተርጎሙ ስራ ወደ ትክክለኛው ምህዋር ውስጥ ያስገባናል። ልብ አድርጉ፣ ደቀ መዛሙርት (ማለትም የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ደቀ መዛሙርት) ጥፋት መቅረቡን ሲያውቁ ሸሽተው እንዲወጡ የተመከሩት ከይሁዳ እንጂ ከጃልሜዳ አይደለም፤ ከኢየሩሳሌም እንጂ ከአዲስ አለም አይደለም።

ይህ ግዑዝ ምድር ያበቃለታል ወይ? መዝሙር  78፥ 69፤ 104፥ 5፤ መክብብ 1፥ 4፤ እና ኤፌሶን 3፥ 21 ሁሉም እነዚህ ምንባባት ይህንን ጥያቄ ሲመልሱ ፈጽሞ፣ በጭራሽ እንደማያበቃለት ይመሰክራሉ። ጃክ ቫን ኢንኮርክት (ኢምፔ) እንኳን ይህን እውነታ ተረድቶታል። ይሁን እንጂ ይህን እውነታ የተረዳው ከዴቪድ ቺልተን ደብዳቤ በኋላ ነበር። ማቴዎስ 24፥ 3 የሚያመለክተው የዘመኑን ፍጻሜ እንጂ የ“ዓለምን/የግሎብን-“ኮስሞስ”ን ፍጻሜ አይደለም፤ 2ጴጥ 3 ደግሞ ትዕምርታዊ በሆነ ዘይቤ የሰማያትና የምድር “ነገሮች” እንደሚቀልጡ ያመለክታል። "ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል" ማለትም በእንግሊዝኛው “ኤለመንቶች” የሚለው ቃል በግሪኩ "ስቶቼዮን" ነው፤ ትርጉሙም ማንኛውም ፊተኛ የሆነ ነገር ሁሉ ወይም ዋና የሆነ ነገር ሁሉ ማለት ነው፤ እነርሱም ስርአቶች፣ መርሆች እና ፍልስፍናዎች ሁሉ ሲሆኑ፣ በገላትያ 4፥ 3፣ 9፣ በቆላስይስ  2፥ 8፣ 20፣ በዕብራውያን 5፥ 12 ላይ እንደተገለጸው "ዓለም" በተሰኘ አግባብ ጥቅም ላይ ውለዋል። የአዲሱ ሰማይ እና የአዲሱ ምድር መፈጠር የአሮጌው ኪዳን ዋነኛ ማዘዣ ጣቢያ የሆኑት ኢየሩሳሌም እና በዚያ ያለው ምድራዊው ቤተ መቅደስ ከተደመሰሱ በኋላ የአዲሱን ኪዳን መገለጥና መመስረት ያመለክታሉ።  (ገላትያ 4፥ 24-26፤ ዕብራውያን 9፥ 8)። በዚያ ቆሞ የነበረው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውድመት የነገረ ፍጻሜ ትምህርት ዋና ጭብጥ ነው።  (ማቴዎስ 24፥ 2,፤ ዳንኤል 9፥ 27፤ ራእይ 11፥ 2)። መጽሐፍ ቅዱስ በብቸኝነት የሚያውቀው የመጨረሻው ዘመን ማለት ቤተመቅደሱን ከቦ ያለው የአሮጌው ኪዳን ስርዓት የመጨረሻ ቀናት ማለት ነው  (ሐዋርያት 2፥ 16-21፤ ዕብራውያን 1፥ 2)፣ እንጂ ከዚህ የተለየው የመጨረሻ ቀን እሳቤ ሁሉ ልበ ወለድ ተረት ነው። የክርስቶስ አካል የሆነው የአዲሱ ኪዳን ቤተ መቅደስ በይፋ የተገለጠው የአሮጌው ኪዳን ቤተመቅደስ ከተደመሰሰ በኋላ ነው። (ዕብራውያን 9፥ 8)። ይህ አዲሱ ቤተ መቅደስ ማለትም “አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር” (ራዕይ 21፥ 1)፣ እርስዋም እንደ ሙሽሪት የተገለጸችው (ራዕይ 21፥ 2፤ ሮሜ 7፥ 4፤ 2 ቆሮንቶስ 11፥ 2) አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና (ራዕይ 21፥ 2) የገላትያ 4፥ 26- አዲሱ ኪዳን፣ ዕብራውያን 12፥ 22) ደግሞም  የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ/ማደሪያ የሆነው ነው (ራእይ 21፥ 3)። የክርስቶስ ሙሽራ፣ እርሷም አካሉ/መቅደሱ/ የሆነች ማደሪያው ናት (ቆላስይስ 1፥ 24)። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ ከላይ ከሰማይ የመጣውና በምድር ላይ ከሰዎች ጋር የተጣመረው የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። ይህም በሰማይ የሆነችው ፈቃዱ በምድር ላይ መደረጓ ነው (ማቴዎስ 6፥ 10)። አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ማለት በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ፣ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ሰማእታት ደም የተሰበከውና በዳግመኛ ምጽአቱ በ70 ዓ.ም ጠላቶቹን ሁሉ በመደምሰስ በይፋ የተገለጠው ክርስትናችን ነው እንጂ ሌላ አይደለም። ይህ ኃላፋውያን ያመጡት አዲስና እንግዳ አተያይ አይደለም፣ የፒዩሪታን እንቅስቃሴ ምሁር የነበረው ጆን ኦዌን እንኳ ፣ ስለ አሮጌውና ስለ አዲሱ ሰማይና ምድር በ2ጴጥሮስ 3፥ 7፣10፣12፣13 የተጻፉትን ጥቅሶችን አስመልክቶ ሲያስተምር ወደዚህ ድምዳሜ ደርሶ እንደነበር እናያለን። የቃላቱን ብሉይ ኪዳናዊ አጠቃቀም መመልከት ከቻልን ደግሞ ከቃል ኪዳኑ ሕዝብ ጋር ባላቸው ግንኙነት ውስጥ አድርጎ እንደሚያያቸው ማስተዋል አይሳነንም። ለምሳሌ፦ "ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፥ ጽዮንንም፦ አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ።" (ኢሳይያስ 51፥ 16)።  ሙሴም ይህን የቃል ኪዳን ሕዝብ በዚሁ አጠራር "ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፣ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።"  (ዘዳግም 32፥ 1)ሲል ተናግሯል። ኢሳይያስም በድጋሚ "እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ።"  (ኢሳይያስ 1፥ 2) ሲል በተመሳሳይ ተናግሯል። ይህም አዲሱ ኪዳን መጨረሻ የሌለው፣ ዘላለማዊ ነው፣ (ዕብራውያን 13፥ 20 )። እንግዲህ “የዘላለም ቃል ኪዳን” በሚለው ሐረግ ውስጥ የመጨረሻ ቀናት የሚል ጽንሰ አሳብ አስገብቶ ቃሉን አስገድዶ መተርጎም ፈጽሞ የማይቻል ነው።

በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ፍጻሜ ሆኖ ሊጠፋ የተዘጋጀው ያ የአሮጌው ኪዳን ሥርዓት እንጂ ለነባራዊው ተዳሳሹ ግዑዝ አለም ወይም ለዚህች ፕላኔት ምድር ጨርሶ ፍጻሜ የለም (ዕብራውያን 8፥ 13)። እደግመዋለሁ፣ ፍጻሜው የብሉይ ኪዳን ዘመን ፍጻሜ ነው። ነብዩ ዳንኤል በትንቢቱ፣ "ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤"  (ዳንኤል 12፥ 9) ሲል የብሉይ ኪዳንን “የፍጻሜ ዘመን” ያመለክታል። የሚያመላክተው ግን  “የጊዜን ፍጻሜ/ ማብቂያ” አይደለም። ስንከተለው የኖርነው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ በእጅጉ ኋላ ቀርና በብዙሃኑ ሳይመዘንና ሳይፈተን ያለጥያቄ የተለመደ ነው። ራዕይ 10፥ 6-7 የሚያመለክተው ከአሁን በኋላ “መዘግየት” አይሆንም፣ እንደውም ከዚህ በኋላ "ጊዜ የለም"፣ የሚልን አገላለጽ ነው። የቀድሞው የመጻኢያን አስተምህሮ አቀንቃኙ ጆርጅ ኤልዶን ላድ እንኳን በዚህ ጉዳይ “ጊዜ የለም” የሚለውን ጉዳይ አምኗል። ንግግሩ በረከሰችው ምድር ላይ የተወሰነውን የእግዚአብሔር ፍርድ ከአሁን በኋላ ለማዘግየት የሚያስችል እድል እንደሌለ የሚያሳወቅ ነው። የነገረ-ፍጻሜ ጥናት ከመጨረሻው ቀን፣ ከዘመኑ ፍጻሜ እና ከመጨረሻው ጊዜ ጋር የተያያዘ ነው ማለት በጥቅሉ ከአሮጌው የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ማብቃት ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው። ፈጽሞ ስለ ኒዩክለር ኃይል እና ስለ ኮምፒተር ቺፕስ የተነገረ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ተጠግተን ስናጠና በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ጊዜው ነው። እንግዲህ በየዘመኑ የተነገሩና ዛሬም እየተነገሩ ያሉ ህዝብ የሚያደናግሩ ሀሰተኛና የተጭበረበሩ ትንቢቶችን ለማጋለጥ ዋናው ቁልፍ ጊዜውን ማወቅ ነው። የሚያጭበረብሩን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የማያውቁና የማያምኑ መምህራኖቻችን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አያጭበረብረንም። መጽሐፍ ቅዱስ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ  ትንቢቶች ጋር በተያያዘ፣ በምንም መልኩ ግልጽ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ እንኳ በጣም ግልጽ እና ትክክለኛ ሆኖ እናየዋለን። ጊዜን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፣ በጊዜ ውስጥ ያስቀመጠውንና የወሰነውን ሰውንም ሲናገረውም ጊዜን በሚረዳበት በዚህ ትክክለኛ መንገድ ይገናኘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነገሮች ከጊዜአንጻር “ሩቅ” እንደሆኑ ሲናገር “የታተሙ” መሆናቸውን ያመለክታል፣ (ለምሳሌ ሕዝቅኤል 12፥ 27-28፤  ከዳንኤል 8፥ 26፤ 12፥ 4፣ 9 ጋር አመሳክሩ)፤ በብሉይ ኪዳን ጊዜም  'ሊፈጸሙ ያሉ የቅርብ ጉዳዮችን' ሲያመለክት ፣ በፍጥነት የሚፈጸሙ እና ቶሎ የሚሆኑ መሆናቸውን ያሳያል፣ (ለምሳሌ ሕዝቅኤል 12፥ 23፣ 25)፤ አዲስ ኪዳንም በዚሁ ይዘት ስለ ጊዜ እንደዚሁ ይናገራል፣ (ለምሳሌ ራእይ 1፥ 1፣ 3፤ 3፥ 11፤ 16፥ 15፤ 22፥ 6፣ 7፣ 10፣ 12፣ 20)። እግዚአብሔር የ70 ዓመታትንየባቢሎን ምርኮ ቆይታ እንደ ረጅም ጊዜ ሲቆጥረው በጊዜ ተወስኖ ላለው ሰው ጊዜው ረጅም ነው ማለቱ ነው እንጂ ለራሱ አይደለም (ኤርምያስ 29፥ 28)። 

ጊዜ ጠቋሚ ከሆኑ ከነዚህ ምንባባት ቀጥተኝ ትርጓሜ ተነጥሎ ትንቢትን ለመረዳት መሞከር አሁንም የትንቢቱን ፍጻሜው እያራዘሙ በቀጣይነት ገና ወደፊት ገፍቶ በማሰብ፣ ንግርተኛዋ ጄን ዲክሰን እንኳ እንቅጩን ትናገርበት ከነበረው የትንበያዋ ትክክለኛነት ውጪ እንደ ማየት ይሆናል። ዘዳግም  18፥ 21-22 እና 1 ተሰሎንቄ 5፥ 20-21 ያለውን ተመልከቱ፣ እነዚህ ሁለት ጥቅሶች “ትንቢትን” ለመፈተሽ የሚያስችሉ መመዘኛ መስፈርትን የያዙ ናቸው። የዛሬዎቹ የቅድመ ሺህ አመት መንግስት ነባያን ግን ይህንን የመመዘኛ መስፈርት አይወዱትም፣ ጠምደው ይዘውታል። “አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነው” ሲሉም ቃሉን ያለአውዱ እየሰነቀሩ ትንቢታቸውንና ንግርታቸውን ለማጽናት ይጥራሉ። ይህ ግን ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ እይታ አንጻር የተባለ ነው፤ እርሱ ግን ሰውን በጊዜ ውስጥ ስለወሰነው ከሰው ጋር የሚያደርገውን ተዛምዶ በጊዜ ቀመር ውስጥ ያደርገዋል። ትንቢት ግን ጊዜ አመልካች የሆኑ ንግግሮቹን ገልጦ ሲናገር በአቀራረቡ የተለየ ካልሆነ በቀር፣ ትንቢት ከጊዜው ተነጥሎ ለማንም ቢሆን በትርጓሜው ምንም ማለት አይደለም። የቅድመ ሺህ አመት አስተምህሮ አቀንቃኝ ነባያን የጊዜ ምዳቤ ልምምድ እሳቤው የተበላሸ ከመሆኑ የተነሳ፣ በ1948 የተቋቋመችውን እስራኤልን እንዲሁም በ1967 ወደ እስራኤል ይዞታነት የተመለሰችውን ኢየሩሳሌምን ታሳቢ በማድረግ፣ "ንጥቀት በ81 ይሆንና፣ ኢየሱስ በ88 አ.ም ተመልሶ ሲመጣ የሚያየው ያ “የመጨረሻው ትውልድ” ነው" ይላሉ።  እነዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስተማሪዎች ነን የሚሉ ወገኖች ስለ "ሺህ ዓመት” ዘይቤ የሚከተሉትን አስተምህሮና ከቃሉ የተፋለሰ ትርጓሜ በከፍተኛ ሁኔታ እያስተላለፉ ብዙዎችን ያስታሉ። በዘመናችን እንደ አሸን ከፈሉት ደላላ ነባያን ባልተናነሰ የእግዚአብሔርን ቃል በማያውቁና "የነገረ መጨረሻ መምህራን ነን" በሚሉ መጻኢ ዘመን ቆጣርያን ትምህርት የተወሰዱ ይበዛሉ። ሬድዮናቸውና ቴሌቭዥናቸው ላይ ቆመው ወደ መካከለኛው ምስራቅና ወደ ወቅታዊ የአለም ትኩስ የፖለቲካ ሁኔታ አፍጥጠው ትንቢትን ለመተርጎም የሚያደርጉት መላላጥ ጠያቂ ከሆነው የአለም ማህበረሰብ ብዙ ትችትና ፌዝ የተሞላ ትዝብት አስተናግዷል። እነዚህ የቅድመ ሺህ አመት አስተምህሮ አቀንቃኝ ነባያን  “አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነው” ሲሉ እንደሚናገሩትና ትርጉሙም እነርሱ በሚሉት መንገድ መወሰድ ካለበት እንግዲያውስ ተቃራኒው ጉዳይ እውነት ይሆናል ማለት ነው፣ ስለሆነም የሚጠባበቁት የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግስት ግዛት ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ይሆናል ማለት ነው።

ተመልከቱ፣ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጠር አንድ ትውልድ (40 ዓመታት ያህል ማለት ነው፣ ዕብ. 3፡9፣10) አለፈ፣ ሃሌ ቦፕ ሃል ዘመኑን ጠብቆ ኮሜት ተመልሳ በአለም እንደምትታይ ባረጋገጠልን መሰረት እንኳ ቢመዘኑ የቅድመ ሺህ አመት አማኞች እንዳላቸው ንግርት ኢየሱስ በ1988 “አልተመለሰም”። ተመልከቱ፣ እስራኤል ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረችበት ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ስንቆጥር አንድ የአርባ ዓመታት ጊዜ አልፎ ወደ ሁለተኛው አርባ አመት እየገሰገስን ነው፣ አሁንም ግን ወፍ የለም። ሃል ሊንዲሲ የተሰኘው የዚሁ ትንበያ ባለቤት ይህ ትንበያው ሳይሳካ ከቀረ አንባቢዎቹ 'ሥራ ፈት'፣ 'ቦዘኔ' (a  bum) ብለው እንዲጠሩት ፍቃድ ሰጥቷል። እንግዲህ 40 አመታትን ጠብቆ ንግርቱ ያልተሳካ መሆኑን እያዩ፣ እነዚህን የሃል ሊንድሴን ቃላት ማንም ሰው ቢሆን ለምንድን ነው መስማት የማይፈልገው? ጌታ ኢየሱስ በፍርድ ደመና ተመልሶ ሲመጣ የሚያየው ትውልድ ግን የትኛው ትውልድ ነው? (የፍርድ ደመና ኢሳይያስ 19፥ 1፤ ሕዝቅኤል 32፥ 7-9፤ 30፥ 3፤ ማቴዎስ 26፥ 64) "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴዎስ 24፥ 34) "ይህ ትውልድ" የተሰኘው ሀረግ በተለያየ መልኩ ኢየሱስ 16 ጊዜ ያህል ሲጠቅሰው፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ጴጥሮስ ጠቅሶታል። ይህም ሁልጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ሲናገር በዚያ ከእርሱ ጋር ቆመው ይሰሙ የነበሩ ሰዎችን ትውልድ የሚያመለክት ነው እንጂ፣ በውስጡ  'ምናልባት' 'ከሆነ' ወይም 'ካልሆነ' አይነት አልያም 'ይህ ትውልድ ባይሆን እንኳ ሌላው ትውልድ' የሚል የሚያመነታ፣ የሚያጠራጥር እና የሚያወዛግብ ነገር የለውም። ትውልድ (በግሪኩ 'ጌኔአ') የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ 38 ጊዜ ያህል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን አንድም ጊዜ ቢሆን እንኳ ዘርን ለማመልከት ጥቅም ላይ አልዋለም፤ ይህ ጥቅስ ማለትም "ይህ ትውልድ"  ማለት "በታሪክ ዘመናቸው ሁሉ የነበሩና ያሉ የአይሁድን ሕዝብ ማለት ነው" ወይም "መላው የሰው ዘር ማለት ነው" በሚለው መላምት ላይ የተመሰረተውን የትርጉም ስህተት አጥጋቢ በሆነ መንገድ መቃወም ይቻላል ወይ? አዎን በእርግጠኝነት! "ይህ ትውልድ" የተሰኘው ሀረግ ለማቴዎስም ሆነ ለተቀሩት ወንጌላውያን  እነርሱና እና ማህበረሰባቸው የነበሩበት ትውልድ ማለት ነው እንጂ ሌላ ምንም አመስጥሮ የለውም። ሆን ተብሎ የተለየ ትርጉም እንዲይዝ ካልተደረገ በቀር ሁልጊዜም ቢሆን  ኢየሱስ የሚናገረው ተወልዶ ስላደገበትና በሥጋው ወራት በምድራዊ አገልግሎቱ ስላገለገለው ስለ ራሱ ትውልድ ነው። እንደ ዕብራውያን 3፥ 9 እና 10 ባለ ምንባብ  "ያ ትውልድ" (ማለትም ያ ያለፈው ትውልድ) ተብሎ ሲነገር እንሰማለን። ኢየሱስ 'ይህ ትውልድ' በማለት ፈንታ 'ያ ትውልድ' ብሎ ለመናገር ምንም አያግደውም፤ ዳሩ ግን እየደጋገመ 'ይህ ትውልድ' ማለቱን እንረዳለን፣ በዚህ ንግግሩ ኢየሱስ እያመለከተ ያለው እርሱ ባገለገለበት ዘመን ስላለው ትውልድ ካልሆነ፣ በተቃራኒው ግን ያ ትውልድ ብሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ገና ወደፊት ስለሚኖር ሌላ ትውልድ ለማሰብ እንገደድ ይሆናል። ስለዚህ ኢየሱስ በደብረዘይት ተራራ ባቀረበው ፍካሬው እርሱ ሲናገር በዚያ ቆመው ያደምጡ የነበሩትን ሰዎች ለማመልከት በማያሻማ ሁኔታ “ይህ ትውልድ” የሚለውን ግልጽ ሐረግ ተጠቅሟል። በደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬው ላይ "ይህ ትውልድ" (ማቴዎስ 24፤ ማርቆስ 13፤ ሉቃስ 21) የሚለው ሀረግ ከአውዱ ተነጥሎ ቀዋሚነት በሌለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ 'በግልጽ የሚያሳየው መጻኢ የሆነውን የወደፊቱን ትውልድ ማለቱ ነው' ብሎ ቃሉን እንደ መጠምዘዝ ምን አስነዋሪ ተግባር ይኖራል። እነርሱ ግን ያለ እውቀት ሲተረጉሙ ቃሉ ገና የወደፊቱን ማለትም መጻኢውን እንዲናገር ለማስገደድ ሲሉ፣ "ይህ" የተሰኘውን የአሁኑን አመልካች ቃል "ያ" ወደተሰኘ የወደፊቱን አመልካች ቃል መለወጥ ነበረባቸው። “አዎ፣ “ይህ ትውልድ” የተሰኘውን ሀረግ በተቀረው የአዲስ ኪዳን ክፍል ውስጥ በቀረበበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በጊዜው ስለነበረው ትውልድ መሆኑን በመካድ፣ ያንን ጠቆም አድርጎ ለማለፍ እንኳን በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ የትርጓሜ ወጥነት የሌላቸው ይሆናሉ። ከዚህም የተነሳ በትምህርታቸውና በአቋማቸው '“ያ ትውልድ” ወይም ዘር ማለት ነው' ሲሉ ኢየሱስ በደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬው በእውነት የተናገረውን ቃል ትርጉሙን ለውጦ ለማንበብና ለመረዳት ሲደፍሩ አያፍሩም። ነገር ግን ቃሉ በተነገረበት ጊዜ የነበረውን ቀጥተኛ ትርጉም ማለት ካልሆነ እንግዲያውስ በመላው አዲስ ኪዳን ሙሉ በሙሉ ፍቺ ወይም ትርጉም የሌለው ይሆናል ማለት ነው። እነርሱ ግን እንዲህ ካልተረጎሙት በቀር የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ ያቆሙበት መሰረት የሚናድባቸው በመሆኑ፣ ይህ ሀረግ እንደዚህ አይነት ትርጉም ሊኖረው ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማገላበጥ ፍላጎቱ ላላችሁ አንባብያን "ትውልድ" የሚለው ቃልና እና "ይህ ትውልድ" የሚሉው  ሀረግ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል የሚያሳይ አጠር ያለ ዝርዝር እነሆ፦

ማቴዎስ 1፥ 1፣ 17፤ 11፥ 16፤ 12፥ 41፣ 42፣ 45፤ 16፥ 4፤ 23፥ 33፣ 36፤ 24፥ 34፤ ማርቆስ 8፥ 12፣ 38፤ 9፥ 19፤ ሉቃስ 7፥ 31፣ 9፥ 41፤ 11፥ 30፣ 31፣ 32 ፣ 50፣ 51፤ 17፥ 25፤  ሐዋርያት 2፥ 40። ኢየሱስ በእያንዳንዱ የንባብ ክፍል ውስጥ ማንን እየተናገረ እንዳለ በግልፅ ለማየት እንዲቻለን ጥቂቶቹን ላቅርብላችሁ።

"ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።"

" ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ?"

" የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤"

"ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።"

"ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል"

" ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም"

፪. የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በወጉ ለመረዳት ሌላው ወሳኙ ነጥብ በብሉይ  ኪዳን በስፋት አገልግሎት ላይ የተዋለውን ትንቢታዊ/አቡቀለምሲሳዊ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀምን መረዳት ነው። ይህ አይነቱ የቋንቋ ዘይቤ በመላው አዲስ ኪዳንም ጥቅም ላይ ውሏል። የአዲስ ኪዳንን ደብዳቤዎች ያነቡ የነበሩ እነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አይሁድ፣ ይህንን የብሉይ ኪዳን ቋንቋ እና ምስል ከሳች የሆነ የንግግር ዘይቤ ያለችግር ይረዱት ነበር። በደመና መምጣት፣ የፀሐይ፣ የጨረቃ መጨለም እና የከዋክብት መውደቅ የመሳሰሉ ማጣቀሻዎች ከሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አንባብያን ይልቅ ለነዚያ ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁድ ፈጽሞ የተለየ ትርጉም ነበራችው። አስተውሉ በፍርድ ደመና ውስጥ የመምጣት ትንቢታዊ ቋንቋ እና ምስል ከሳች የሆነው የንግግር ዘይቤ በመላው ብሉይ ኪዳን በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።

ለምሳሌ ኢሳይያስ 19፥ 1 "ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል" ሲል በግብፅ ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ይናገራል። "በፊቱ" ማለትም በመገኘቱ ፊት ነው፣ ይህም ቃል በግሪኩ ፓሮዥያ የተባለው ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ መምጣት በሚል ጥቅም ላይ ውሏል፤ ትርጉሙም የመምጣቱ መገኘት እንደማለት ነው።

ሕዝቅኤል  30፥ 3፣ 4 "የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።" (አደራችሁን ይህንን ጥቅስ ይዛችሁ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ሌላ ቅዥት ውስጥ እንዳትገቡ፤ ኢትዮጵያ የሚለው የአሁንዋን ኢትዮጵያ ሳይሆን የኩሽን ምድር ነው)

ሕዝቅኤል  32፥ 7-9 " ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።" በዚህ ፍርድ ውስጥ የምናየው ዋና ስዕል የብርሃናት መጨለም ነው፣ ሆኖም ግን በተዳሳሹ የተፈጥሮ ደመና ላይ ምንም የተፈጠረ ነገር አልነበረም። የሚመጣውን ፍርድ ለመግለጽ ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት ስለ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት ይናገራል። እያንዳንዳቸው እነዚህ ግዑዝ የሆኑ ፍጥረታዊ ብርሃናት ሌሊትንና ቀንን እንዲገዙ ይሰለጥኑ ዘንድ እንደተሰጣቸው ሁሉ፣ እዚህ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ቋንቋና ሥዕላዊ መግለጫዎቹ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ከአገሮች ገዥ ባለሥልጣናት ጋር አዛምዶ ያቀርባል። እነርሱም በሚቀበሉት ፍርድ ብርሃናቸው ማለትም ገዥነታቸውና ሥልጣናቸው መጥፋትና መጨለም ነበረበት።

ኢሳይያስ 13፥ 9፣ 10 የሚናገረው በሜዶናውያን እጅ የሚፈጸመውንና  በባቢሎን ላይ የሚደርሰውን ፍርድ ገለጻ ነው። እንዲህ ይላል፦ " እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል። የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።" በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ላይ ግን አካላዊ በሆነ መልኩ ምንም የደረሰ ነገር አልነበረም።

ዘፍጥረት 37፥ 9ና 10 በዮሴፍ ህልም ውስጥ ይህንኑ ቋንቋ እና ምሳሌ ይጠቀማል። "ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ፦ እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ። ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?" ተመልከቱ ቁጥር 10 ፀሐይን የዮሴፍ አባት፣ ጨረቃን እናቱ፣ እና ከዋክብቱ ደግሞ ወንድሞቹ እንደሆኑ ይተረጉመዋል። ሁሉም በትንሹ ዮሴፍ ላይ የተሾሙ ነበሩ፣ ዳሩ ነገሩ ሊገለበጥ እንደሆነና ዮሴፍም በአገዛዙ በሁሉም ላይ ሥልጣን ኖሮት ከፍ ከፍ እንደሚል ያሳያል።

እነዚህ ሁሉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በግብፅ ላይ፣ በባቢሎን ላይ እና በእስራኤል ምድር ላይ የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከል እና ለማቃናት ሊመጣ ስላለው ፍርድ ይናገራሉ። አዲስ ኪዳንም በተመሳሳይ የቋንቋ ዘይቤ ጌታችን የተሰቀለባትን ታላቂቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን/ ወይም በጥቅሉ እስራኤልን መንፈሳዊ ግብፅ እና ባቢሎን ተብላ የተገለፀችው እንደሆነ ይናገራል። ይህን ለማረጋገጥ ራዕይ 11፥ 8ን ከራዕይ 14፥ 8፤ 16፥ 19፤ 17፥ 1፣ 5፣ 18፤ 18፥ 2፣ 10፣ 18፣ 19፣ 21፤ 19፥ 2 ጋር አገናኝታችሁ ተመልከቱ።

፫. የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ለመረዳት የመጨረሻው አስፈላጊ ነጥብ ቦታውን የማወቅ ዋና ጉዳይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ውስጥ አስቀድመው በትንቢት የተነገሩ ጉዳዮች የሚፈጸሙት የት ነው? የራእይ መጽሐፍ እብዛኛውን ጊዜ የሚናገረው ስለ “ምድር” ሲሶ፣ ወይም በቀላሉ “ምድርን” ስለሚመታ ፍርድ፣ ወዘተ ነው። በእነዚህ በተነገሩ ፍርዶች ውስጥ ኮስሞስ/ግሎብ የሚለው የግሪክ ቃል በጭራሽ ጥቅም ላይ ውሎ አናየውም። አንዳንድ ትርጉሞች ይህንን አስተካክለው "ምድሪቱ/ ምድር" የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል። ፍርዱ “በምድሪቱ” ላይ በተለይም ማዕከሉን ኢየሩሳሌም ላይ እና ቤተ መቅደሱንም መገለጫው  ባደረገው  በእስራኤል “ምድር” ላይ በጥቅሉም ከአሮጌው ኪዳን በታች ተዘርግቶ በነበረ አሮጌ ሥርዓት ላይ እየመጣ የነበረ ቁጣ ነው። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ፍካሬው ውስጥ ወንጌል በ“ዓለም” ሁሉ እንደሚሰበክ እና ከዚያም መጨረሻው (ማለትም የአሮጌው ኪዳን ዘመን ፍጻሜ) እንደሚመጣ ሲናገር እንደ “ኦይኮመኔ” ያሉ ቃላትን አጽንዖት ሰጥቶ መጠቀሙን እናስተውላለን (ማቴዎስ 24፥ 14)። ኦይኮመኔ” የሚለው ቃል “መሬት፣ የምድር ምድራዊ ክፍል፣ በተለይ የሮማን ኢምፓየር፣ ምድር፣ ዓለም” ተብሎ ይገለጻል። ለምሳሌ በሉቃስ 2፥ 1 ላይ የሕዝብ ቆጠራ በመላው ዓለም እንዲደረግ በታወጀበት ጊዜ፣ ቆጠራው የተከናወነው በግሎቡ ላይ ሳይሆን ይልቁንም በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ መፈጸሙን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። እንግዲህ ኦይኮመኔ ወይም ኦኩሜኔ በጊዜው ለሚታወቀው፣ መኖርያ ለሆነው፣ ወይም ለሚኖርበት ዓለም የተሰጠ ጥንታዊ የግሪክ ቃል ነው እንጂ ግሎብን አያመለክትም። በጥንታዊት ግሪክ፣ በሄለኒክ ጂኦግራፊስቶች የሚታወቁትን በሦስት አህጉራት የተከፋፈሉትን የዓለም ክፍሎች ያመለክታል።

ኢየሱስ በጀልዱ ወይም በጂንካ ያሉትን ሳይሆን በይሁዳ ያሉት በዙሪያው ወዳሉ ተራራዎች እንዲሸሹ ሲያመለክት ይህ ታላቁ መከራ የት ቦታ ላይ የሚደርስ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል (ማቴ 24፥ 16)። ብዙዎቻችን ይህ የማቴዎስ 24 ትንቢት በመላው ዓለም ስለሚደርስ ጥፋት፣ ስለ ኑክሌር ጦርነት እና በጥቅሉ የዚህ ግዑዝ ግሎብ መጥፋት እንደሆነ ስንማር ኖረናል። ጉዳዩ ግን እንዲህ ከሆነ ከይሁዳ ሸሽቶ ወደ ተራራ መሸሸግ ምን ጥቅም ይኖረዋል? በዘመናችን ከተፈለሰፉ የኤፍ-16 እና ከሃይድሮጂን ቦምቦች የሚደረግ እንዲህ ዓይነቱ ሽሽት  ትርጉም አልባ ይሆናል፣ በየትም ያለ ማንኛዉም ተራራ ከኒውክለር አረር አይሸሽግም። የሚቀጥለው ቁጥር ማቴዎስ 24፥ 17 ላይ፣ ኢየሱስ በቤታቸው ሰገነት ላይ ላሉ ሰዎች በቅድሚያ እቃቸውን ለመውሰድ እንኳ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ፣ ነገር ግን ጊዜ ሳያጠፉ ወዲያውኑ እንዲሸሹ አሳስቧቸዋል። በዚያን ዘመን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከቤታቸው በላይ እንደ ሰገነት ሆነው ተሰቅለው የተሠሩ ቤቶች ነበሯቸው (ሐዋርያት 10፥ 9)። እንግዲህ ተመልከቱ ማቴ.24 ስለ እነርሱ ቀናቶች እንጂ እየተናገረ ያለው ስለእኛ ቀኖች አይደለም! የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ለመረዳት ስፍራው በእጅጉ ማዕከላዊ ነገር ነው። በአለም ላይ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የአድራሻና የቦታ ለውጥ የተከሰተው ያኔ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ ነው። የእግዚአብሔር ሀልዎት  እና የአምልኮው ማዕከል የሆነው  ዋና የማዘዣ ጣቢያው የሆነውን  አድራሻውን ወደ ሌላ የቀየረ ክስተት ነው። በኢየሩሳሌም መስገድ ቀርቷል፣ አሁን የእግዚአብሔር አምልኮ በመንፈስ እና በእውነት ሆኗል (ዮሐንስ 4፥ 21-24)። ከእንግዲህ ወዲህ የአምልኮና የእግዚአብሔር አገልግሎት ዋና የማዘዣ ጣቢያ የሚገኘው በምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም መሆኑ ቀርቷል፣ አሁን የመንፈሳዊ አምልኮና የአገልግሎት ሁሉ ማእከል ዋና ጣቢያ ያለው በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም በሰማያዊትዋ ከተማ ነው (ገላትያ 4፥ 24-26፤ ዕብራ 12፥ 22)። ምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም የአሮጌው ኪዳን ዋና የማዘዣ ጣቢያ እና የሞት አገልግሎት ማዕከል ሆና የውድመቷን ቀን ጥፋቷን እየጠበቀች ነበር። "ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል" (ሉቃስ 11፥ 50፤ ማቴዎስ 23፥ 35-38) እንደተባለ የፍርዶች ሁሉ ፍርድ የሆነውን የከፋ ፍርድና በቀል ትጠብቃለች። የማቴዎስ 24 ትንቢትም  ይህንኑ አውድ ጠብቆ የከተማዋን ጉዳይና መጻኢውን እጣ ፈንታ ተከትሎ ይናገራል፣ የትንቢቱም ማዕከላዊ ጭብጥ የቤተመቅደሱ ጥፋትና ውድመት ነው። ቤተ መቅደሱ የትንቢቱ ዋና  ጭብጥ መሆኑን አለማየት በጠቅላላው ነገረ ፍጻሜን የምንረዳበትን መስመር ያስታል (ማቴዎስ 23፥ 38፤ 24፥ 2፣ 3፣ 15)። በዚህ የፍርድ ሂደት የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ አዲሱ እና ዘላለማዊው ስፍራ ለውጥ ያደርግ ነበር። እግዚአብሔር፣ አምልኮው እና አገልግሎቱ ከአሁን በኋላ በሕያዋን ድንጋዮች በተሠራ (1ጴጥሮስ 2፥ 5)  መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ/የክርስቶስ አካል ውስጥ እንጂ፣ በማናቸውም በእጅ በተሠራ ቤተመቅደስ ውስጥ አይኖርም (ሐዋርያት 7፥ 48፤ 17፥ 24፤ 2 ቆሮንቶስ 5፥ 1)። የሚያልመኩትም ቅዱሳን ሕዝቡ የእግዚአብሔር እስራኤል ሁሉ ናቸው፣  ዜግነታቸውም ሰማያዊ፣ አድራሻቸውም በሰማያዊ ስፍራ፣ አገራቸውም ሰማያዊቷ እየሩሳሌም የሆኑት ሁሉ ናቸው (ፊልጵስዩስ 3፥ 20፤ ገላትያ 4፥ 26፤ ዕብራውያን 12፥ 22፤ ማቴዎስ 5፥ 14)።  "በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር ተቀምጠው እየገዙ ያሉ  አሁን ዜጎች ናቸው (ኤፌሶን 2፥ 6፤ 1፥ 3)።

ያ የጥንቱና ምድራዊው የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ ያ የመጀመሪያው ቃል ኪዳን እና የዚያ ቃል ኪዳን ማዕከል የሆነው ቤተ መቅደሱ እንዲሁም ከተማይቱ ኢየሩሳሌም ሊወድሙ እና ሊፈርሱ፣ ሊወገዱም ጥፋታቸው ቀርቦ ነበር (ዕብራውያን 8፥ 2፣ 7፣ 13)። እነዚህ ሁሉ የዚያ ሊጠፋ ተመድቦና ተዘጋጅቶ የነበረው የአሮጌው ኪዳን መገለጫ ነበሩ። እዚህ በዕብራውያን 8፥ 13 ጥቅም ላይ የዋለው "Eguus” የተሰኘው የግሪክ ቃል ትርጉሙ  ቅርብ፣ በደጅ (ራእይ 1፥ 3፤ 22፥ 10)፣ የተዘጋጀ፣ በቅርቡ ሊሆን ያለ ማለት ነው። በጊዜው ያልፉበት ከነበረው ብርቱ መከራ የተነሳ እውነተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ/የአካሉ/መቅደስ ማን እንደሆነ፣ እውነተኞቹም የእግዚአብሔር ልጆች እነማን እንደ ሆኑ፣ ስንዴው እና እንክርዳዱስ እነማን እንደነበሩ፣ በጎችና ፍየሎችስ እነማን እንደነበሩ፣ የአሮጌው ኪዳን አይሁድ ወይም የአዲስ ኪዳን አይሁድ የትኞቹ እንደነበሩ ገና ጎልተው በግልጽ ሊታዩ አልቻሉም ነበር። ይህን የሚለየው ሊገለጥ ያለው የእሳት ፍርድ ነበር። " ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።" (ዕብራውያን 9፥ 8) ተብሎ ተጽፏልና። የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ቤተመቅደስ፣ አሁንም እንደገና የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት ዋና ጭብጥ መሆኑን ተመልከቱ። አሮጌው የአዲሱ ተቃራኒ ነው። አሮጌ የሆነው የድሮው ቤተመቅደስ እርሱም የአይሁድ ቤተ መቅደስ "ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ" (ማቴዎስ 12፥ 6) ተብሎ በተጠራውና በተሰየመው አካሉ በሆነው የእግዚአብሔር ማደሪያ  “ተኮንኗል”። ይህ ከመቅደስ የሚበልጥ አዲሱ የእግዚአብሔር መኖሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዚያን ዘመን ይሉ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ብዙዎች በእኛ ዘመን በትምህርታቸው፣ “አይ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መሆን ብቻውን በቂ አይደለም፣ አሁንም በኢየሩሳሌም ተዳሳሽ የሆነ ቤተ መቅደስ ያስፈልገናል።" የሚሉ ይመስላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ደፍሬ እላለሁ፣  ያ አሮጌው ቤተመቅደስ፣ ከተማይቱና እና መላው የእስራኤል ሀገር አንድ ጊዜ ከወደሙ በኋላ፣ እውነተኛ አይሁዶች እነማን እንደሆኑ ግልጽ ተደርጓል  (1 ጴጥሮስ 2፥ 9፤ ማቴዎስ 21፥ 43፤ ሮሜ 2፥ 28፣ 29፤ 9፥ 8)። እነዚያ አሮጌዎቹ ዓይነቶች፣ ቁሶች እና ጥላዎች ሁሉም ታሪክ ሆነው ወድመዋል፣ ወደፊትም አይታሰቡም። አሮጌው ሲወገድ አዲሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ በዚያን ጊዜ ሙሉ በሙሉ እውን ሆኖ ተገልጧል። መቅደስ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቤተክርስቲያኑ/የአካሉ/ በሙላት መገለጥ እውን የሆነው በመስቀሉ ላይ የተሰጠውን ህጋዊ ውል ተከትሎ ነበር (ራእይ 21፥ 2፣ 3)። ኢየሱስ በአባቱ ቤት ለሁላችን የሚበቃ ብዙ መኖርያ አለው (ዮሐንስ 14፥ 3)። ይህ አዲሱ አድራሻችን ቋሚና ዘላለማዊ ሆኖ ሳለ ብዙዎች ግን አሁንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተመልሰው አሮጌውን የመኖሪያ ቦታ በዚያ መመስረት ይፈልጋሉ። አሁንም ግብፅ ወደተባለችው ባቢሎን ዘኢየሩሳሌም ለመመለስ ይናፍቃሉ (ራእይ 11፥ 8) እርሱ ግን ባርነትና ወደ ባርነት መመለስ ነው (ገላትያ 4፥ 25)። በዚህም ልክ እንደ አሮጌው ቤተ መቅደስ፣ እንደ ከተማይቱ እና እንደ ሕዝቡ ሁሉ ፍጻሜያቸው ተመሳሳይ ነው። እንጨታቸው፣ ሳራቸው እና አገዳቸው ይበላል (1ቆሮንቶስ 3፥ 12)። ያለ እውቀት ባቆሙት ነገረ ፍጻሜአዊ ሥነመለኮታቸው የሚያፍሩ ይሆናሉና።

gkr