Friday, July 2, 2021

የተዋረደው ሥጋ ልውጠት

 የተዋረደው ሥጋችን ልውጠት

" እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።" ፊልጵስዩስ 3፥ 21

1. የማይስተባበለው እውነት

መጻኢያን የሆኑ የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ተከታዮች በዚህ ጥቅስ ላይ ተመስርተው "ጌታ አንድ ቀን ወደ ፊት ተመልሶ ሲመጣ፣ የፈረሰውን ሟችና በስባሽ አካላችንን የእርሱን ወደሚመስል መንፈሳዊ አካል (አንዳንዴም ራሱን ተዳሳሹን አካል የሚሉ ይመስላሉ) ይለውጠዋል፣ ያኔም በመቃብር ውስጥ አፈር የሆነው ሥጋችን ይነሳና በክብር በሰማይ ለዘላለም ይኖራል" ብለው ሲያስተምሩ ይደመጣሉ። በእውነት ግን የምር እንደዚህ የምናምን ከሆነ በመጀመሪያ የሚፋጠጠንና ልናስተባብለው የማይቻለን ዋና እውነት፣ ጌታ ተመልሶ ከመጣ ዘመናት የተቆጠሩ መሆኑ ነው። 

የጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ ይጠበቅ የነበረውም ሆነ የተፈጸመው ወይም መፈጸም ያለበት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ መሆኑን በየትኛውም ሥነ መለኮት ማስተባበል አይቻልም!! በአዲስ ኪዳን ከደርዘን በላይ ሞልቶ በሚፈስ የምስክርነት ቃል አስረግጠን ልንናገረው የምንችለው እውነት፣ ጌታ ኢየሱስ ዳግመኛ ተመልሶ እንደሚመጣ ራሱ ጌታችንም ሆነ ሐዋርያቱ ሲያስተምሩና ሲጽፉልን፣ የመመለሻውን ጊዜ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውጭ እንዳናስብ አድርገው መናገራቸውን ነው፤ እነርሱ የተናገሩትን ብቻ እንጂ እኛ የመሰለንን እና ልንሰማው የምንፈልገውን አናምንም። 

በመሆኑም እግዚአብሔር ለነገር ሁሉ ጊዜን የመደበ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም "ጊዜን የሚናገር" አምላክ መሆኑን ጭምር ከሚጠራጠርና፣ እግዚአብሔር ለትንቢት ፍጻሜ የመደበውንና የገለጠውን ጊዜ እያስተባበለ፣ እግዚአብሔር ያልተናገረውን ጊዜ በመጠባበቅ ያለእውቀት "የእግዚአብሔር አራሚ" ለመሆን ከሚዳዳው ሥነ መለኮት ጋር የመስመር ልዩነት አድርገናል፣ አልተገናኘንም። እግዚአብሔር በግልጽ የተናገረውን ጊዜ ለእግዚአብሔር ተአማኒነት የተቆረቆርን መስሎንም ይሁን ወይም ለልማዳዊው ሥነመለኮታችን ትክክለኛነት ተጨንቀን፣ ጥብቅና በሚመስል አቋም ተይዘን፣ እንደተጻፈው ቃሉ ሳይሆን፣ "የለም እንዲህ ማለቱ ነው" ብንልና ቃሉን ልናርም ብንሞክር አሳች አስተማሪ መሆናችን ነው። ይህ በራሱ ንስሃን የሚጠይቅ ሥነመለኮታዊ ውድቀት ነው።

ስለዚህ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ምንም ነገር ይሁን ምንም፣ ሲፈልግ 'መንፈሳዊ' ከወደደም 'አካላዊ' ትንሣኤ ወይም ልዋጤ የትኛውም ቢሆን ያለጥርጥር ያኔውኑ የተፈጸመ ጉዳይ መሆን አለበት። "በዚህ ጥቅስ ላይ የተነገረው ነገር ሁሉ፣ ናፋቂያኑ እንደሚጠባበቁት ያለ የመጻኢነት 'ተስፋም' ይሁን ወይም ሌላ ማናቸውም ከትንሣኤ ተፈጥሮና ባህርይ ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ ሁሉ፣ የአማኞች የተዋረደ ሥጋ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል መለወጡም ጭምር ተፈጻሚ የሆነው እና መፈጸምም ያለበት፣ ጌታ ተመልሶ በመጣበት በ70 አ.ም ላይ ያኔ ነው ስል እነሆ በድጋሚ ድምጼን ከፍ አድርጌ አስታውቃለሁ። እንደ 'ንጣይ' እና 'ግንጣይ' ቢያስቆጥርም እንኳ ከተባረከው የቃሉ ምስክርነት ጋር ለመቆምና ለመሞት እመርጣለሁ። እነሆ የሙታን ትንሣኤም ሆነ ይህ የህያዋን የልዋጤ ተስፋ በተባረከው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው ተፈጽሟል፣ አልፏልም። በዚህ ጥቅስ አውድ ላይ እና በጠቅላላ በያዘው ቁም ነገር ላይ መነጋገር የምንችለው፣ ከሁሉ በፊት ይህ ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር የተጋመደ ትንሣኤም ይሁን ልዋጤ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክስተት እንደሆነ በገጾቹ ሁሉ ከሚያስተምረው የተፈጸመ ወንጌል ጋር የተግባባን እንደሆነ ብቻ ነው።

2. የአውደ ምንባቡ መልዕክት

የፊልጵስዩስ 3፥ 21 "የተዋረደው ሥጋችን" ልዋጤ በነገረ ፍጻሜና በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ አውድ ውስጥ የቀረበ የጽድቅ መገኘት እና የድነት ሙላት ተስፋ ፍጻሜ መሆኑን ጥቅሱን ከበው ያሉ ጉዳዮች ሁሉ ያመለክታሉ። ይህም የጽድቅ መገኘትና የድነት ሙላት፣ "በክርስቶስ በማመን ያለው"... "ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው" የተባለው "ጽድቅ" (ቁጥር 7-9) ነው። ጳውሎስ "በእርሱ እገኝ ዘንድ" ሲል በክርስቶስ ለመገኘት ያለው ምኞት ወደክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት የሚያመለክት መግለጫ ነው። ጴጥሮስም ተመሳሳይ ነገር ይናገራል፣ "ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥" (2ጴጥሮስ 3፥ 13-14)። ጳውሎስ "አሁን (ገና) እንዳላገኘሁ" ይላል፣ ያ ገና ያላገኘው ነገር ምንድን ነው? በግሪኩ lambano የተሰኘው ቃል ተሻጋሪ ግስ ነው፣ ነገሩ ግን አልተገለጸም። ጉዳዩ በቁጥር 11 ላይ ያነሳው ትንሣኤ ይሆንን? አዎ በዝርዝሩ ውስጥ ትንሣኤም ተካቶበታል፣ ነገሩ ግን ከዚያም የሚሰፋ ነው። ክርስቶስ በመምጣቱ ሥጋቸውን ከአንድ የታወቀ ደረጃ ሊገለጥ ወደማይችል ወደ እርሱ አካል የላቀ የክብር ደረጃ ፍጽምና ይለውጠዋል፤ እርሱም አማኞች እንዲኖራቸው ያሰበላቸው የአካል አይነት በስራዎች ጽድቅ ላይ የሚመካ አካል ሳይሆን እርሱ ባጠናቀቀው ፍጽምና ላይ የሚመካውን የጽድቅ አካል ነው። ልብ ብለን ካየነው ፊልጵስዩስ 3 ደግሞ እንዳለ የሚያወራው ስለጽድቅ መገኘት ነው። የዚህ ጽድቅ ተቃራኒ ደግሞ ጳውሎስ እንደ ጉድፍ የቆጠረውና አይሁድ በከንቱ የሚመኩበት በሕግ የሚገኝ ጽድቅ ነው። ክርስቶስን ማግኘት እርሱም በክርስቶስ በማመን ያለውን ጽድቅ፣ ማለትም በእምነት በኩል ከእግዚአብሔር ዘንድ በጸጋ የሚታደለውን ጽድቅ ማግኘት ነው (ቁጥር 9)።

 በቁጥር 10 ላይ የሚያነሳው "የሙታን ትንሣኤ" ሙታን ከሞት ስለሚወጡበት ኩነት ነው፤ በእርግጥም ሙታን የሚለው አምነው በተስፋ የሞቱትን የብሉይ ኪዳን እስራኤልን ሲሆን፣ ጳውሎስም ራሱ ደግሞ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ከሚሰበሰበው ከነገረ ፍጻሜአዊው መከር አስቀድሞ ካሉትና ይህንን የሙታን ትንሣኤ ከሚጠባበቁትና ከሚካፈሉት በኩራት መካከል ነው። "ልደርስ እመኛለሁ" ማለቱም ወቅቱ የራሳቸውን መዳን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የሚፈጽሙበት አይነተኛ የትግል ጊዜ በመሆኑ፣ በዚያ የትግል ወቅት ከእምነት አፈግፍገው የሚቀሩና በትንሣኤ ተካፋይ የማይሆኑ መኖራቸውንም ያሳያል። ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱና "መጨረሻቸው ጥፋት" የሆኑ "የመስቀሉ ጠላቶች" ነበሩና (ቁጥር 2-3፣ 18-19)። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በትምህርቱ፣ እርሱ ብቻ ነገረ ፍጻሜአዊው "ትንሣኤና ሕይወት" መሆኑን ግልጽ እድርጓል (ዮሐንስ 11፥ 25-26)፤ ስለሆነም የጳውሎስ ምኞት ገና እንዳላገኘው ሁሉ ክርስቶስን ማግኘት ነበር (ቁጥር 12)፤ ጳውሎስ የሚመኘው ራሱን ክርስቶስን ማግኘት እንጂ የገዛ ራሱን ሰብዓዊ ሥጋ የሚተካ ሌላ አካል ማግኘት አልነበረም። ክርስቶስን ማግኘት ደግሞ የመንፈሳዊ አካሉ ፍጽምና ነው። ጉዳዩ ከምናስበው በላይ የሰፋ መሆኑን በግርድፉ እንየው።

ጳውሎስ እያነሳ ያለው ጉዳይ ጽድቁ ገና የተጠናቀቀ አለመሆኑን ነው። ስለዚህም "አሁን (ገና) እንዳልያዝሁት" ወይንም ገና እንዳልጸደቅሁ ነኝ እያለን ነው። ጳውሎስ መልዕክቶቹን ይጽፍ በነበረበት ጊዜ መጽደቅ ያኔ ገና ተስፋ ነበር። ጳውሎስና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ገና የእግዚአብሔር ጽድቅ አልነበራቸውምን? ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖራል። በተጠናቀቀ እና ሙላቱን ባገኘበት መልኩ የእግዚአብሔር ጽድቅ ገና ወደፊት ለእነርሱ የሚገለጥ ነበር። 

ይህንን ልዋጤ፣ እርሱም የጽድቅ ተስፋ ፍጻሜን አስመልክቶ ማጽናት የምፈልገው አንድ ጉዳይ፣   "ይገለጣል" የተባለው "የእግዚአብሔርን ጽድቅ" (ሮሜ 1፥ 17) ጌታ ኢየሱስ በክብር እስኪመለስ ድረስ ገና ለፍሬ፣ ይኸውም ለመዳናችን ፍጽምና ያልደረሰ የነበረ መሆኑን ነው። (ይህንን በጉልህ የሚያሳዩ በርካታ ምንባባት አሉ፤ ለምሳሌ፦ ዕብራውያን 9፥ 28፤ ሮሜ 13፥ 11፤ 1ተሰሎንቄ 5፥ 9፤ 2ጢሞቴዎስ 2፥ 10፤ ዕብራውያን 1፥ 14፤ 1ጴጥሮስ 1፥ 5፣ 9፤ እና 2ጴጥሮስ 3፥ 15፤ ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ ይችላሉ)። ክርስቶስ፣ ጽድቅ፣ ትንሣኤና ፍጽምና ወይም ሙላት የተሰኙት ቃላት ሁሉም የሚያመለክቱት ያንንው ጳውሎስ ሊያየውና ሊደርስበት የሚመኘውን አንዱን ተስፋ ነው። ይህም ተስፋ ያኔ "ቀድሞውኑ ሆኗል ግን እስካሁን ድረስ ገና አላለቀም" (the already  and not yet) አይነት ባህርይ ባለው በሽግግሩ ውቅት ላይ የነበረ እውነታ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ "ክርስቶስን ማግኘት" ያኔ ተጀምሯል ግን በሙላት አልተጠናቀቀም፣ ፍጻሜውን ወደፊት ይጠብቃል ማለት ነው። ስለዚህም ጳውሎስ እንደ ጴጥሮስ ሁሉ (2ጴጥሮስ 3፥ 13-14)፣ አዲሱን ሰማያዊ አገር ወደፊት (በቅርብ አመታት ውስጥ፣ በጣም በአጭር ጊዜ) እየተጠባበቀ ወደላይ አሻቅቦ ያያል (3፥ 21)። 

በዚህ አውድ ውስጥ ማንም የቃሉ ተማሪ በግልጽ የሚያየው አንድ እውነት ይህ መጠባበቅ እነርሱ ማመን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ትውልድ የዘመን ርዝመት በላይ በጣም ረጅም ጊዜ የሚወስድ አለመሆኑን ነው፣ ምክንያቱም "በመጀመርያ ካመኑበት ጊዜ ይልቅ መዳናቸው ወደእነርሱ እየቀረበ ነበር"። ያን ጊዜም "ከእንቅልፍ የሚነሱበት" ሰዓት ደርሶ ነበር። ያኔም ለእነርሱ "ሌሊቱ አልፎ" የአሮጌውን ዘመን የጨለማ ኃይል ሙሉ በሙሉ አውጥተው የሚጥሉበት "ቀኑ ቀርቦ" ነበር (ሮሜ 13፥ 11-12)። ሊመጣ ባለው ዘመንም ጠላቶቻቸውን በመደምሰስ በሙላት የሚገለጠውን የሚመጣውን ዘመን ኃይል ቀምሰው ነበር (ፊልጵስዩስ 3፥ 18-21፤ ማቴዎስ 24፥ 2-3)። ስለዚህ እስከ ጌታችን ዳግመኛ ምጽአትና ከእርሱም ጋር የሚሆነው የሙታን ትንሳኤ እስኪፈጸም፣ ዘላለምም እስኪጀመር ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት ለጳውሎስና ለመልዕክቱ ተደራስያን እሩቅ እና እረጅም አልነበረም፤ "ዘመኑ አጭር ሆኖአል" (1ቆሮንቶስ 7፥ 29) ይሉ ነበርና። ያኔ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ዘመኑ፣ መጨረሻው፣ ፍጻሜው፣ ቀኖቹ ቅርብ ብቻ ሳይሆን ሰአቱም የመጨረሻ ነበር (1ዮሐንስ 2፥ 18)፣ ስለዚህም እያጣደፈ በሚያልቅ የዘመን ሙጣጭ ውስጥ ነበሩ።

የእግዚአብሔር ጽድቅ መጻኢ ገጽታ የነበረው መሆኑን ጳውሎስ በግልጽ አስተምሯል፤  እነዚያም የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በዘመናቸው ያገኙት ዘንድ ናፍቀውና ጓጉተው ይጠባበቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን ፣ "እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።" (ገላትያ 5፥ 5) ሲል ግልጽ አድርጓል። ተመልከቱ፣ ጽድቅ ያኔውኑ የተፈጸመ ወይም የተጠናቀቀ ኩነት ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ጳውሎስ በእምነት መጽደቅን የተስፋ ጉዳይ በማድረጉ በንግግሩ ትልቅ ስህተት እየፈጸመ ነበር ማለት ነው። ጽድቅ ያለቀለትና የተጠናቀቀ ጉዳይ ከሆነ ታዲያ ጳውሎስ ለምን ተስፋ ያደርገዋል? ከፍ ሲል እንዳመለከትኩት ጳውሎስ ይኖር የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ "የመጨረሻው ቀኖች" ሲል በሚጠራው ዘመን ላይ ነበር፣ እነዚያም ቀኖች የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀኖች ነበሩ። እነዚያ የመጨረሻዎቹ ቀኖች በክርስቶስ መወለድ ተጀምረው በ70 ዓ.ም ላይ የአይሁድ ቤተመቅደስ ሲደመሰስ ተፈጽመዋል። አሁን ግን እኛ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ "የሚመጣው ዘመን" እያለ በሚጠራው በአዲሱ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው። ከበአለ ሃምሳ ጀምሮ የእስራኤል መቅሰፍተ እልቂት እስከሆነበት ድረስ ያለው የአርባ አመታት ጊዜ ከአሮጌው ኪዳን ወደአዲሱ ኪዳን ሽግግር የሚደረግበት የሽግግሩ ወቅት ነው። በዚህ የሽግግር ወቅት አዲሱ ኪዳን ገና ተመርቆ ተጀምሯል እንጂ ተጠናቆ አልተፈጸመም ነበር። ያ ጊዜ "already but not yet" የተሰኘው ጊዜ ነው።

በዚህ የሽግግር ወቅት የጳውሎስ ምኞት እና አላማ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ነው፣ ይኸውም ክርስቶስን ማግኘት፣ የክርስቶስን ጽድቅ ማግኘት ነው፣ (ፊልጵስዩስ 3፥13-14)። "እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ"፣ ምናልባት እንዲህ ያለ ንግግር በዚህ ምንባብ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደገመ ይመስላል። ግልጽ የሚያደርገው አንድ እውነት "የእግዚአብሔር መጥራት ዋጋ" ሲል የሚጠራውን የጽድቅን ብድራት ገና ያላገኘ ወይም ያልያዘ እና ገና ፍጹም ያልሆነ መሆኑን ነው። ዘመኑ ካልተፈጸመና አዲሱ ኪዳን በሙላት ካልተገለጠ በቀር ይህ ፍጹምነት እርሱም የእግዚአብሔር የመጥራት ዋጋ የተሰኘው የጽድቅ ብድራት ሊገኝ አይችልም። ስለዚህ፣ ትግሉን ስሙ፦ 

" በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።" (ፊልጵስዩስ 3፥ 14)፤ በአዲሱ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ "ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው" ይላል። ያንን ሕይወት ገና ወደላይ ተጠርቶ ሲሄድ እንደሚቀበል እንጂ ተጠርቶ ወደላይ ከመሄዱ በፊት እንዳለው ወይም እንደያዘው ገና አያስብም። "እፈጥናለሁ" ማለት በግሪኩ dioko ነው፣ ይኸውም አንዳችን ነገር ለማግኘት እና ለመያዝ መሮጥ ነው። ያለማቋረጥ ወደ ግቤ እገሰግሳለሁ እያለ ነው። ለምን አጥብቆ ወደግቡ ይሮጣል? ቢባል የቤተክርስቲያን ፍጽምና ለሆነው ብድራት ነው፣ ይኸውም በዳግመኛ ምጽአቱ የክርስቶስን ጽድቅ መቀበል ነው። ከፍ ሲል የጠቀስናቸውንና በጻድቃን ትንሳኤ ተካፋይ የማይሆኑ ያልናቸውን፣ ጳውሎስም "የመስቀሉ ጠላቶች" ሲል የሚጠራቸውን ይሁዲዎችንና ወደ ጥፋት የሚያደርሳቸውን ለአሮጌው ኪዳን ያላቸውን ቅንአት ካነሳ በኋላ (ቁጥር 17-19)፤ ቀጥሎ በቁጥር 20 ላይ በቅርቡ ራሱን ጨምሮ "እኛ" ሲል ለሚጠራቸው ሁሉ ስለሚመጣው ብድራት ወደሚናገረው ርእሰ ጉዳይ ያልፋል። 

በቁጥር 20 " እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤" ሲል በመስቀሉ ጠላቶችና የሰማያዊ አገር ዜግነት ባላቸው መካከል ያለውን ተቃርኖ ያመለክታል። "እኛ" የሚለው ጳውሎስንና የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ጨምሮም ሌሎች አማኞችን ሁሉ ነው። ዳግመኛ የተወለድን ሁላችንም ዜግነታችን ሰማያዊ፣ አገራችንም በሰማይ ነው። ዜግነት ማለትም "አገራችን" የሚለው ቃል (በግሪኩ politeuma)፣ በአዲስ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋለው እዚህ ላይ ብቻ ነው፣ ነገር ግን politeumai የተሰኘው ግስ በፊልጵስዩስ 1፥ 27 ላይ ጥቅም ላይ ሲውል አመልካችነቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው ማህበራዊ ተሳትፎውንና የዜግነት ድርሻውን የሚወጣ የክርስቲያናዊ አኗኗር ዘይቤን ነው። "አገራችን በሰማይ ነው"፦ ይህም አይገሰስም፣ አይለወጥምም፤ "ነው" ይላልና፣ የጸናና የተመሰረተ በማንም የማይገፈፍ አስተማማኝ የዜግነት መብት ነው። ሰማያዊውን መንፈሳዊ፣ መሬታዊውን ደግሞ ፍጥረታዊ ሰው ሲል ባነጻጸረበት በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 47-48 ባለው ገለጻ ለሰው ልጆች የተመደበውን ሁለት አይነት ዜግነት በግልጽ ማየት ይቻላል

ሰማይ ምንድን ነው? ብንጠየቅስ ምን ትርጉምና ማብራርያ ሰጥተን ልንገልጠው እንችላለን? ተመልከቱ፦ "ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።" ዕብራውያን 9፥ 24 ይላል፤ እዚህ እንደምናየው ሰማይ የእግዚአብሔር ማደርያ ነው። "በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ" ብለን ስንጸልይ እግዚአብሔር ማደርያው በሰማያት እንደሆነ እያወቅን ነው። ሰማይ እውነተኛይቱ ቅድስት ናት።

2ቆሮንቶስ 12፥ 1-4 "ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።"

እዚህም ላይ በድጋሚ ሰማይን የእግዚአብሔር ማደርያ፣ የመኖሪያው ስፍራ ሆኖ እናያለን። ሰማይ በዚህ ተዳሳሽ አለም የተወሰነ አንድ ቦታ ላይ ያለ የሆነ ስፍራ አይደለም። ሰማይ በእውነትም በሰማያዊው አለም የሚገኝ፣ አድራሻ ያለው ኑባሬ ነው። ጳውሎስ በሥጋ ይሁን ወይም ያለሥጋ መሆኑን የማያውቀው፣ እንዴት እንደሆነ ግን እግዚአብሔር ብቻ ወደሚያውቀው "ገነት" ሲል ወደሚጠራው ሦስተኛው ሰማይ ተነጥቆ በዚያ የነበረውን በሰው ቃል ሊገለጥ የማይችል ልምምዱን መሰክራል። እንግዲህ እንደ ክርስቲያን አገራችንና ዜግነታችን በሰማይ ነው። ከስፍራ አንጻር አሁን ያለነው በሰማይ ነው፣ ሥጋዊውን ሞት በምንሞትበት ጊዜ ነፍሳችን ይህንን ነባራዊ አለም ስትተው ሄዳ የምትገኝበት 'ይሄ'፣ 'እዚህ' ወይም 'እዚያ' የሚባል አድራሻና፣ ያ ኑባሬ ሰማያዊው አለም ነው። በሥጋ ስንሞት፣ የእግዚአብሔር መኖርያ በሆነው በመንፈሳዊው አለም በሰማይ እናድራለን። ጳውሎስ "ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" (ፊልጵስዩስ 1፥ 23) ይላል፤ እንደ አማኝ መናፈቅ ካለብን ይህንን ያለ ነገር ብቻ እንናፍቃለን እንጂ ተፈጽሞ ያለፈ ነገር መናፈቅ የሌለ ነገር መናፈቅና መድከም ነው።

ሰማይ የአማኙ ተስፋው ነው። ስሞት ወደጌታ፣ ወደ ሰማይ እሄዳለሁ፣ አስተማማኝና የምጠባበቀው የተረጋገጠ ተስፋ ነው። " ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።" (2ቆሮንቶስ 5፥ 1) እዚህ ላይ ጳውሎስ "ድንኳን" ሲል የሚጠራው "ምድራዊ መኖሪያ" ተዳሳሹ አካላችንን ነው። ጴጥሮስም በተመሳሳይ መንገድ ሥጋውን ምን ብሎ እንደሚጠራው ተመልከቱ፦ "ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።" (2ጴጥሮስ 1፥ 13-14)፤ አማኞች ሁሉ በሥጋ የሚሞቱበት አንድ የሆነ ቀን አላቸው፣ ታዲያ ያ በሚሆንበት ጊዜ፣ ፈጽሞ የማንኖርና የማንገኝ አንሆንም፣ ወደ እሳት ባህር የምንሄድም አንሆንም፣ በቀጥታ የምንሄደው ወደ ሰማይ ነው። ጳውሎስን ስሙት፦ "እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።" (2ቆሮንቶስ 5፥ 6-8) ይላል። 

እንደ ክርስቲያን ተስፋችን፣ ማለትም ስለ መጻኢው ያለን ፍጹም እርግጠኝነት፣ ይህንን ሥጋዊ አካል የሆነ ማደሪያችንን በሞት ምክንያት ስንተወው፣ ወዲያውኑ በሰማይ ከጌታ ጋር መሆናችን ነው። ለጥንት ቤተክርስቲያን ተሰጥተው የነበሩ ሁሉም ተስፋዎች ተፈጽመዋል፤ ዳግመኛ ምጽአቱ፣ የሙታን ትንሳኤ፣ የጽድቅ ሙላት፣ የመዳን ተስፋ፣ የዘላለም ሕይወት፣ ይህ ሁሉ ለእነርሱ የሚጠባበቁት ተስፋቸው ነበር፤ በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን መጨረሻ በፓሮውዥያው ተፈጽመዋል። ክርስቶስ ተመልሷል፣ ትንሳኤም ከአሁን በፊት ሆንዋል፣ ፍርድም አልፏል፤ ይህ ሁሉ ከዚህ በኋላ በእኛ ዘመንም ይሁን ወደፊት የማይሆንና የማይደገም የተፈጸመ ትንቢት ነው። የተፈጸመ ነገር ደግሞ ተስፋችን ሊሆን አይችልም። የተሰጠና ያላችሁን ነገር ተስፋ ልታደርጉት አትችሉም። ምን ተስፋ እንደሚያደርግና እንደማያደርግ ጳውሎስን ስሙት፦ "በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።" (ሮሜ 8፥ 24-25) ክርስትናን ልንኖረውና የድሉን ደስታ ልናጣጥመው የሚገባን ይህንን የተፈጸመ ተስፋ እውነታ ተቀብለን ነው። ትምህርታችንን እና እምነታችንን መረዳት የተሳናቸውና ለመረዳትም ፍላጎት የሌላቸው አንዳንድ ወገኖች ግን በተፈጸመው ወንጌል አስተምህሯችን ውስጥ ለክርስቲያን ምንም ተስፋ የለውም እንደምንል አድርገው ተመልክተውናል፤ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው። በተፈጸመው ወንጌል የሚታወጀው መጽናናት የሞላበት የተፈጸመው ተስፋ እርስዋም የተገኘች እውነት እንጂ፣ ልብን የምታሳዝን የምትዘገይ ተስፋ አይደለችም። አስተምህሯችሁ ተስፋ ገዳይ ነው ሲሉ ለሚነቅፉን ሁሉ ወደመጽሐፍ ቅዱሳቸው ተመልሰው እግዚአብሔር በቃሉ ለሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ጊዜን የመደበና ያ ጊዜ መቼ እንደሚሆን በግልጽ  የተናገረ እንደሆነ በትህትና እንዲማሩ እንመክራለን። ተስፋ ተፈጽሟል ባዮች የምስራች ተናጋሪዎች ነን እንጂ ተስፋ ነጣቂዎች አይደለንም። የጥንት ቤተክርስቲያን ተስፋ ስታደርገው የነበረው ነገር ሁሉ ተፈጽሞ ተገልጧል፣ እኛም እነርሱ ተስፋ ያደረጉትንና የተፈጸመላቸውን አምነን ወርሰናል፣ አምነን የገባነው ወደተፈጸመው እውነታ ነው። ስለዚህ እኛ በየተራ ሞተን ወደሰማይ መሄዳችንን የምንጠብቅ ከመሆኑ በቀር እግዚአብሔር ተናግሮ ያልፈጸመው ምንም ተስፋ የለም። ክርስቶስ በፈጸመው ተስፋ ሞተን የምንሄድበትን መኖርያ፣ ሰማይን አዘጋጅቶልናል፤ ተስፋችን ይኸው ነው።

ጳውሎስ ይቀጥልና "ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤" ይላል። "እንጠባበቃለን" የተሰኘው ቃል በግሪኩ apekdechomai ነው፤ ትርጉሙም ጓግቶ መጠበቅ፣ የሚመጣውን የክብር እንግዳ በናፍቆትና በፍቅር እንኳን ደህና መጣህልን ብሎ ለመቀበል ተዘጋጅቶ መጠበቅን ያሳያል። ይህ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ሰባት ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በተጠቀሰበት ስፍራ ሁሉ አገባቡ ዳግመኛ ምጽአቱን በሚያሳይ መልኩ ነው። apekdechomai የተሰኘው ይህ ቃል በሮሜ 8 ላይ ሦስት ጊዜ ጥቅም ላይ ውላል፦

ሮሜ 8፥ 19 "የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና(apekdechomai)።" ጌታ በሚመለስበት ጊዜ የሚገለጡት "የእግዚአብሔር ልጆች" እነማን ናቸው? ያኔ ኢየሩሳሌምን በማጥፋት ክርስቲያኖች የእርሱ ልጆች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።

ሮሜ 8፥ 23 "እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን (apekdechomai) ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።"

ቤዛነት ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር የተጋመደ ነው። " በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።" ሉቃስ 21፥ 27-28፤ በዚህ ጥቅስ አውድ "ይህ" ተብሎ ይሆናል የተባለው ነገር የኢየሩሳሌም ውድመት ነው። ቤዛነት የሚጠናቀቀው ኢየሩሳሌምን በፍርድ ሊያጠፋትና ለአሮጌው ኪዳን ፍጻሜውን ሊሰጠው ጌታ ሲመለስ ነው።

ሮሜ 8፥ 25 "የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን(apekdechomai)።"  

ሁሉም እነዚህ በሮሜ 8 ያለው የቃሉ አውዳዊ አገባብ ዳግመኛ ምጽአቱ ነው። (ተጨማሪ ማጣቀሻ 1ቆሮንቶስ 1፥ 7፤ ገላትያ 5፥ 5፤ እና ዕብራውያን 9፥ 28 ተመልከት)፤ ስለዚህ ጓግተውና ናፍቀው የሚጠባበቁት ጌታ ሲመጣ በፓሮውዥያው ጽድቅን ያመጣላቸዋል ማለት ነው (ዕብራውያን 9፥ 28)።

ስለዚህ የቁጥር 21 የልዋጤ ተስፋም በዚሁ የዳግመኛ ምጽአቱና የጽድቅ መሰጠት አውድ ውስጥ መታየት ያለበት መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ግልጽ የሆነው ይህ የቃሉ ትምህርት እና ቃሉን ልተካ ባዩ እድሜ ጠገብ ልማዳዊ ዶግማ በተለይ በዚህ ጉዳይ ነጭና ጥቁር ስለሆኑ፣ መጻኢያንም ቃሉን ብቻ ዋቢ አድርገን የምንመሰክርለትን ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን ተስፋ ፍጻሜ መቀበል ስለማይችሉ፣ ወይም ስለማይፈልጉ፣ የትንሳኤን ተፈጥሮ ወይም ባህርይ በተመለከተ ያለውን የኖረ ልማዳዊ ትምህርታቸውን ይዘው ቀርተዋል። ይህንን ጊዜ ያለፈበትን (expired ያደረገ) የመጻኢነት ትምህርት በቅዱሳት መጻህፍት ፈትነንና ፈትሸን ልናጸናውም ሆነ ልንሽረው ካልደፈርን በቀር ንጹሁንና ቅኑን ትምህርት ሳናውቅ ከሌሎች በወረስነው ልማድ እንደሳትን፣ ሳንታረም ቀናችን ያበቃል፤ በርዕሰ ጉዳዩም ላይ በበቂ ሳያስቡበት አዋቂ ነን የሚሉትንም መመለስና ማቅናትም በእውነት ከባድ ነው። አሁን ቁጥር 21ን በሌላ ርእስ ማየታችንን እንቀጥል።

3. ክቡር ሥጋው ማለት

ኢየሱስ ከሞት በተነሳ ጊዜ ሥጋው በአይነቱ የተለየ ነበርን? የነበረውስ የከበረ ሥጋ ነበርን? በርካቶች እንደዛ እንደሆነ ያስባሉ፣ የናገራሉ ። ነገር ግን ከመቃብር የወጣው የኢየሱስ ሥጋ ያው ራሱ ወደ መቃብር ከወረደው ሥጋ ጋር አንድና አንድ አይነት ነው፣ ምንም የተለየ ነገር የለውም የሚለውን ማመን እመርጣለሁ። መጽሐፍ ቅዱሱን የሚያውቅ ሰው ታዲያ፣ "እንግዲያውስ ደህና ማርቆስ ከትንሳኤው በኋላ የኢየሱስ ሥጋ የተለየ ነው ይለናል አይደለም ወይ?" ሲል ይጠይቃል፦

ማር 16፥ 11-12 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤

እንዲህ ካሉ ጥቅሶች የተነሳ በርካቶች የኢየሱስ የትንሳኤው አካል የተለየ እንደሆነ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ማርቆስ በወንጌሉ ሌላ ክፍል ቀደም ሲል የሚለውን ስሙ፦

ማር 9፥ 2  ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ

"ተለወጠ" የሚለው ቃል metamorphosis የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የሚተረጉም ሲሆን፤  የግሪኩ ቃል morphe ትርጉሙ 'ከ' ሲሆን meta ደግሞ መለወጥ ከተሰኘው ሁለት የቃላት ጥምረት የተገኘ ነው። ቃሉም እንደ ትርጉሙ የሚያሳየው ያው መለወጥን ነው። በቀላሉ ሊሰመርበት የሚገባው የቃሉ ትርጉም 'ከአንድ ነገር መለወጥን' ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ከትንሳኤ በፊት መሆኑን አትርሱ።

ታዲያኮ ከትንሳኤው በኋላ ኢየሱስ በተዘጉ ደጆችና መስኮቶች አልፎ ሄዶ ነበር ብላችሁም ታስቡ ደግሞ ይሆናል። መልካም፣ ታዲያ ይህ የተለየ ስጋ ነበር ወይ? በጭራሽ አይደለም፣ ቀጥሎ ያለውን ተመልከቱ፦

ሉቃ 4፥ 28-30 በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥ ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤  እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።

ህዝቡ ኢየሱስን ከላይ ወደ ታች ገፍትረው ሊጥሉት ወደ ገደል አፋፍ የዘውት ወጡ፣ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። ያንን እንዴት አደረገው? ከሞት ከመነሳቱም በፊት እንኳ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ያደርግ ነበር።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሉቃስ ምን ብሎ እንደጻፈ ልብ አድርጉ፦

ሉቃ 24፥ 38-39 እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።

በመስቀል ላይ የተቸነከረው ቁስል በርግጥም በግልጽ በሰውነቱ ላይ የሚታይ እንደነበር ከዚህ እናስተውላለን። ደግሞም እርሱ ስጋና አጥንት እንጂ መንፈስ  እንዳልሆነም ተናግሮአል።

ሉቃ 24፥ 40-43። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፦ በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ።

እዚህ ላይ ኢየሱስን ሲመገብ እናየዋለን። የከበረ ሰጋ ይራባልን? ተርቦሳ ይበላልን? እንዲህ ያሉ አገላለጾች የሚያሳዪኝ ያው እውነተኛውን ተፈጥሮአዊ ስጋ ነው እንጂ ሌላ አይነት እንዳስብ አያደርጉኝም። 

ዮሐ 20፥ 27-28 ከዚያም በኋላ ቶማስን፦ ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። ቶማስም፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።

እዚህም ላይ እንደገና ያንንው በሚስማር የተበሳውን የኢየሱስን የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካር እንዲሁም የጎኑን መወጋት እናያለን። ልክ ቀደም ሲል ከትንሳኤው በፊት መስቀሉ ላይ እንደሆነውና እንደነበረው አይነት ማለት ነው። "በትንሳኤ የምንቀበለው የከበረው ሥጋችን ፍጹም ይሆናል" ሲባልና ተደጋግሞ ሲነገረን ሰምተናል፤ የኢየሱስ ሥጋ ግን እንደዚያ እንዳልነበረ ብዙዎች አላስተዋሉም። በሥጋው ሞቶ በመንፈስ ሕያው የሆነው ኢየሱስ ከሞት በተነሳው አካሉ የመስቀሉ ችንካርና ጎኑን የወጋው ጦር ቁስል አብሮት እንደነበር፣ ይህንንም ለደቀመዛሙርቱ እንዳሳያቸው ወንጌላት በግልጽ ያመለክታሉ። ኢየሱስ ከትንሳኤውም በኋላ የነበረው አካል ያው ራሱ እግዚአብሔር ያዘጋጀለትና ከድንግል ማርያም የነሳው ሥጋው ነው እንጂ ከትንሳኤው በኋላ የተቀበለው ሌላ የተለወጠ የከበረ ሰጋ አልነበረም። እኛም በትንሳኤ የምንቀበለው ሰውነታችን በእርግጥም እንደ ኢየሱስ አይነት እንደሚሆን በልማድ ሲነገረን ኖሮአል። ነገር ግን፣ የኢየሱስ የትንሳኤ አካል በጎኑ ላይ የተወጋውና በእጆቹ መዳፍ ላይ ያለው የችንካሩ ቁስል ይገኝበት ከነበረ፣ ታዲያ ይህ ማለት፣ እኛም በትንሳኤ የምንቀበለው ሰውነት ያለፍንበትንና የተለማመድነውን የማንኛውም አይነት ህመምና ስቃይ ጠባሳ ሁሉ ይገኝበታል ማለት ነውን? ለምሳሌ የኢየሱስ የችንካሩ ምልክት እና የቁስሉ ጠባሳ ከትንሳኤው በኋላ በአካሉ ላይ ይታይና ይዳሰስ ከነበረ፣ እግሩ ተቆርጦ በአካል ጉዳት የኖረና ቆይቶ የሞተ ሰው 'በትንሳኤ ቀን' ምን አይነት አካል ሊኖረው ነው? እንዲህ ካለ አጉል እምነት ወደቃሉ ብርሃን እንድንመለስ ጸጋው ይርዳን።

 የኢየሱስ የሥጋው ትንሳኤ አልአዛር ከነበረው የተለየ አልነበረም ማለት እንችላለን። ትንሳኤው የኢየሱስን ሥጋ ወደ ምንም አለወጠውም፣ ከትንሳኤውም በኋላ የነበረው ያው ከመጀመርያ አብ ያዘጋጀለትና በመስቀል ላይ የቆሰለው ሥጋው ነው፤ ይልቁንም ቃል የሆነው ኢየሱስ በተዘጋጀለትና በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋው ከመሰረቱ ከትንሳኤው በፊትም ሆነ በኋላ ያው ኃጢአት ያላወቀው ክቡር ነበር።

ስለዚህ ጳውሎስ፦ "ክቡር ሥጋውን እንዲመስል" በሚልበት ጊዜ፣ ይህ "እንዲመስል" የተሰኘው ቃል በግሪኩ 'summorphos' ነው፤ [እንግሊዘኛ ትርጉሙ፦ Jointly formed, i.e. (figuratively) similar:--conformed to, fashioned like unto. ይሰኛል]፤ ቃሉ morphe ከተሰኘ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም "የአንድ ነገር አስፈላጊና መሰረታዊ ጠባይ፣ አማራጭ የማይገኝለት አስፈላጊና መሰረታዊ ቅርጽ፣ አንድ አይነት፣ የተስማማ፣ "እንደ እርሱ ሆኖ የተሰራ"፣ ነው። በእርግጥ እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚጠቀምበት ቃል morphe የተሰኘውን ሳይሆን 'summorphos' የሚለውን ነው፤ በሁለቱ የቃል አጠቃቀም ላይ ጉልህ ልዩነት አለ። 'summorphos' ትርጉሙ፣ "ተጋጥሞ መሰራት" ነው። አብሮ መሆንን ወይም የአብሮነትን አንድነት ያሳያል። ይኸውም የስፍራ ደረጃ (positional) አንድነት ነው። አማኞች ከክርስቶስ ሥጋ ጋር የሚኖራቸውን አብሮነት የሚያሳይ ነው እንጂ መመሳሰል ወይም አንድ አይነትነት አይደለም።

የተዋረደው ስጋችን "ክቡር ሥጋውን እንዲመስል" መለወጡ (ማለትም metaschematizo መደረጉ) አካሉን የመምሰል (የ summorphos) ውጤት እንደሆነ ልብ አድርጉ። የተዋረደው ስጋችን አካሉን መስሎ (summorphon በመሆን) የተገለጠው፣ መስሎ እንዲለወጥ  metaschematizo በመደረጉ ምክንያት ነው።

ቁጥር 21 እንደዚህ ሊነበብ ይችላል፦ እርሱም (ክርስቶስ) ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ (ይህንን የተዋረደው ሥጋችንን) ክቡር ሥጋውን እንዲመስል (summorphon) የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል (metaschematizo) ።

"Morphed" የሆነውና ክቡር የተደረገው የክርስቶስ አካል ነው። እኛም ከወደድን ስጋችን ይህንን ክብር የሚቀዳጀው በመተባበር ወይም በመምሰል (summorphed በመሆን) በዚህ ህይወት ብቻ ነው። ከክርስቶስ ጋር አንድ የምንሆንበንት እምነትንና ቅዱስ ጥምቀትን የምንለማመደው በዚህ ህይወት ብቻ ነው። ተዳሳሹ አካል አሁን ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መገለጫ የሆነውም ለዚህ ነው፣ በዚያ መንገድ አይታይ ይሆናል እንጂ፣ አሁን በእምነትና በቅዱስ ጥምቀት ላገኘነው የማይሞት መንፈስ ተዳሳሹ አካል ቤቱ ነው። ይህ ማለት ግን የማይሞት ሥጋ አለን ማለት አይደለም። ሥጋ በሮሜ 6፥ 4 ውስጥ እንደተገለጠው ከመቀበሩ ሌላ ፈጽሞ morphed አይሆንም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተዳሳሽ የሆነ የከበረ ስጋ የሚታያቸው መጻእያን በአውደ ምንባቡ ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለው የግሪክ ቃል ላይ ሲቀባቡ ይስተዋላሉ።

4. ልዋጤው

".....እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል" 

ጌታ ተመልሶ በመምጣቱ ምክንያት ይህ ጉዳይ ቀድሞ የሆነና ያለፈ ድርጊት ከሆነ፣ ታዲያ እነዚያ ጌታ ሲመጣ ሊቀበሉት የተዘጋጁቱ በሕይወት የነበሩት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የተዋረደው ሥጋቸው ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተለወጠው እንዴት ነው? "መቼ?" የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ "እንዴት?" የሚለውን ለመመለስ ብዙም አይቸገርም። የዚህ ልውጠት ጠቅላላ ነገሩ "ጊዜው" ላይ የተመሰረተ ነውና፣ ጊዜውም ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣል። ስለዚህ ጥናታችንን በመቀጠል የልዋጤውን ተፈጥሮ ወይም ባህርይ እንዴት እንረዳለን? ወደሚለው እንለፍ። 

ይህንን የልውጠት ሁናቴ በአግባቡ ለመረዳት በመጀመርያ፦ "ይለውጣል" ወይም "ልዋጤ" የተሰኘውን ቃል እንይ፤ ቃሉ ጥቅም ላይ በዋለበት የንባብ ክፍል ውስጥ የበኩረ ቃሉን አገባብ መረዳት ያስፈልጋል። የግሪኩ ቃል "metaschematizo" ነው፣ [እንግሊዘኛ ትርጉሙ፦ "to Transform", "to alter", "to change the apperance", "transfigure" or "disguise"; figuratively, to apply /by accommodation/:--transfer, transform / self በሚል እንደሚተረጎም geoffrey w. bromiley ባዘጋጀው The Teological Dictionary of The new testament በተሰኘው መጽሐፍ ማየት ይቻላል (በአማርኛችን መቀየር፣ መለወጥ፣ መልክን ወይም ገጽታን መለወጥ፣ በልዩነት ሌላ መሆን ወይም የተደበቀውን ሌላ መግለጥ፤ በምሳሌአዊ አገላለጽ ያለውን ሁኔታ፣ መተግበርን፣ ለራስ ማድረግን፣ ማስተላለፍን ራስን መለወጥን ያሳያል)]። 

ለውጡ "ወደ አዲስ አይነትነት መለወጥ" መሆኑንም ከጥንታዊ የግሪክና የአይሁድ ጽሁፎች እንረዳለን። ሰማዕታት በሞታቸው ጊዜ ተለውጠው ወደ ሰማይ የሚሄዱበትን ክብር እንደሚያሳይ ለምሳሌ በተጨማሪ የብሉይ ኪዳን መጻህፍት የሰባ ሊቃናት ትርጉም ላይ ይታያል። ፋይሎ ግሱን ሲጠቀምበት 'ወደ አዲስ ቅርጽ ወይም መልክ መለወጥ' አድርጎ ያቀርበዋል፤ ጆሳፈስም ልብስን እንደመለወጥ ወይም እንደ ማስመሰል፣ እንዲሁም በገጽታ ተለውጦ እንደ መታየት ባለ መልኩ ይጠቀምበታል። በጥንት ቤተክርስቲያን ባሉ የጽሁፍ ስራዎች የቃሉንና የግሱን አጠቃቀም አስመልክቶ እንደምሳሌ ልንወስደው የምንችለው ምንም የሰነድ ማስረጃ ባይኖርም የሄርማ ራእዮች በተሰኘው ሰነድ ቅጽ 5.1 ላይ  'schema' የተሰኘው የግሪክ ቃል ጥቅም ላይ ውሏል ትርጉሙም ልብስ ወይም መልበስ እንደማለት ነው ነው።

በአዲስ ኪዳን ግን ቃሉ በተለያየ አውዳዊ አገባብ አምስት ጊዜ ያህል ጥቅም ላይ ውሎ እናየዋለን። በአምስቱም ውስጥ ያለው የቃሉ መሰረታዊ ፍቺ፦ ልዋጤ፣ ዝውውር፣ ራስን መለወጥ፣ በምሳሌያዊነት ወደ መኖርያነት መቀየር ሲሆን፤ በአምስቱም ውስጥ ያለው ትርጓሜ የሚያመለክተው 'አምሳላዊ ልውጠት' ነው፣ ይኸውም ከውስጥ የማይመጣ የውጫዊ መግለጫን ግምት እንደ ምሳሌ አድርጎ መስጠትን ወይም መውሰድን ነው [The outward expression that does not come from within]። ይኸውም መምሰል እንጂ ሆኖ መገኘት አይደለም።

ለምሳሌ በዚህ በንባብ ክፍላችን ውስጥ አማኞች ወደ ፍጻሜው የሚያደርሳቸው መንፈስ ያላቸው መሆኑን፣ ዳሩ ግን ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ያላቸውን ይህንን "የተዋረደ" እርሱም የሚሞት አካል ክቡር ወደሆነው የማይሞት አካል የሚለውጠው መሆኑን ያመለክታል። በሌሎቹ የአዲስ ኪዳን ምንባባትም በተለያየ አውዳዊ አገባብ ቃሉ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ። ይህ የፊልጵስዩስ መልእክት ከተጻፈበት ጊዜ ጥቂት አመታት ቀደም ብሎ የተጻፈው 2ኛ ቆሮንቶስ ስለዚሁ የጽድቅና የልዋጤ ተስፋ በምዕራፍ 3፥ 18 ላይ ሲያበስር፣ "እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን" ሲል አለኝታቸውን ይመሰክራል። 

በዚህ "metaschematizo" በተሰኘ የግሪክ ቃል ላይ የተሻለ መረዳትን ያስጨብጡን እንደሆነ እነዚህን ጥቅሶች ጨምረን እንመልከት።

1ቆሮ 4፥6  ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ (metaschematizo) ተናገርሁ።

ጳውሎስ እዚህ ላይ በመንፈስ ህጻናት ለሆኑ የቆሮንቶስ ሰዎች በደረጃቸው ልክ ወርዶ ስለ ራሱና ስለ አጵሎስ "እንደ ምሳሌ" ሆኖ (ከውስጥ የማይመጣ ውጫዊ መግልጫን ከግምት በማስገባት)፣ ማለትም እነርሱን ሆኖ ሳይሆን "እነርሱን መስሎ" የሚለምናቸውና የሚመክራቸው ይመስላል። በመካከላቸው ሰፍኖ ስለነበረው የህጻናት ክርክር አስቀድሞ በምእራፍ 3 ላይ ገስጾአቸው ነበር፤ አሁን ደግሞ ጳውሎስ ራሱና አጵሎስ ጭምር ከቆሮንቶስ ሰዎች ይልቅ በሳሎች መሆናቸውን እያወቀ፣ የሚሻልና የሚበልጥ ሆኖ ለመታየት ግን አልፈለገም፣ ከዚያ ይልቅ ግን ትኩረታቸውን በጌታ ላይ እንዲያደርጉ እንጂ፣ በራሳቸው ላይ  እንዲያደርጉ አይፈልግም። "ምሳሌነቱ" ከውስጥ የማይመጣ ውጫዊ አገላለፅን ከግምት በማስገባት በቆሮንቶስ ሰዎች ፊት የበላይና የሚሻል ሆኖ ከመታየት የሚያቅብ ይመስላል። በቆሮንቶስ ሰዎች ፊት የሚበልጥና የተሻለ ሐዋርያ ሆኖ ከመታየት የሚያቅብ መገለጫ ነው።

ጳውሎስ ይህንን metaschematizo የተሰኘ ቃል በሁለተኛው መልእክቱ ላይም ሲጠቀምበት እናያለን፣ የቃሉን አጠቃቀም በተመለከተ ይኼኛው በተለይ ጉልህ የሆነ ምሳሌ ነው፦

2ቆሮ 11፥13-15 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ (metaschematizo)፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና (metaschematizo)። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ (metaschematizo) ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።

ተመልከቱት ግሱ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ይታያል። ሐሰተኞቹ ሐዋርያት እነርሱም የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ወደ ሐዋርያነት ራሳቸውን ለውጠዋል፣ እውነተኞቹን የክርስቶስ ሐዋርያት ግን አልነበሩም፣  ሰይጣንም የብርሃን መልአክ አልነበረም፣ መምሰል ግን ችሏል፣ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች አልነበሩም፣ ራሳቸውን ግን ማስመሰል ችለዋል፣ ይህም ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን በሚያሳይ መግለጫ  ተመሳስለው ተገኙ እንደማለት ነው፣ እንጂ ያንን የመሰሉትን ነገር ሆነው ተገኙ ማለት አይደለም። በዚሁ አይነት መንገድ እነዚያም ቅዱሳን የተዋረደው ስጋቸው ተለውጦአል። ስለዚህም በ70 አ.ም ላይ ከሆነው የቤዛነት ቀን ፍጻሜ ጀምሮ ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ አለመሞትን እግኝተዋል።

1ቆሮ 15፥ 51-53  እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።

እዚህ ላይ የተነገረለት ልዋጤ የማይሞተውን ( አለመሞትን) መልበስ ነው። ተዳሳሹ ስጋ ለፍጥረቱ እንግዳና ባእድ ወደ ሆነ ሁናቴ ይወሰዳል። የሚለወጠው ፍጥረቱ አይደለም፣ መንፈስ የሚሰጠውን የማይሞተውን ሁናቴ በጊዜያዊነት መውሰዱ ብቻ ነው። ፍጥረታዊ የሆነው ተዳሳሹ የተዋረደው ስጋ "የማይሞት" ይሆናል ማለት አይደለም፣  ይልቁንም በቀላሉ የማይሞት ለሆነው ለክርስቲያን መንፈስ ማደርያ ቤት የመሆንን ደረጃ ይቀበላል እንጂ። metaschematizo የተሰኘው ቃል ትርጉምና ጠቀሜታውም ይኸው ነው፤ በእውነተኛው አካላዊ ተፈጥሮ ላይ ምንም አይነት መሰረታዊ ተጽእኖና ልዩነት የማያመጣ ነገር ግን በአይነቱ ልዩ የሆነውን ጥራት (ለጊዜው) መልበስ ነው። ያ ደረጃና የክርስቲያን ማዕረግ ከሞት በኋላ መንፈስ በሚለይበት ጊዜ አብሮን ይኖራል እንጂ፣ መቼም ቢሆን ሥጋ ወደ ሰማይ እንደማይሄድ ሁሉ አንድ ቀን ሥጋን ከመቃብሩ ውስጥ አውጥቶ ሊያመጣው ከሥጋ ጋር አብሮ የሚቀርም አይደለም። 

አንድ ማስተልዋ ያለብን እውነት፣ በዚህ በፊልጵስዩስ 3፥ 21 የተነገረለት ልዋጤ ከፍ ሲል በተራ ቁጥር የአውደ ምንባቡን ዳሰሳ ባየንበት ጥናታችን አጽንዖት ሰጥቼ እንደጠቀስኩት በሽግግር ወቅት ላይ የተነገረ ተስፋ መሆኑን ነው፤ ልዋጤውም በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት የሽግግሩ ዘመን ሲያበቃ ያኔ በሕይወት ለነበሩት ላልሞቱት ቅዱሳን የሚሰራ ነው። ጌታ በመምጣቱ አስቀድመው ሙታን ለነበሩት ቅዱሳን ትንሳኤን ሲሰጣቸው፣ ገና ላልሞቱትና በናፍቆት ሲጠባበቁት ለነበሩ ሕያዋን ቅዱሳን ደግሞ ልዋጤን ይሰጣቸዋል፤ እንጂ ልዋጤ እና ትንሳኤ በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸሙ  ከመሆናቸው በቀር እርስ በርሳቸው ለአንድ አላማ የሚሰሩ ክስተቶች ናቸው። የትንሳኤም ሆነ የልዋጤ አላማ ቅዱሳንን በሰማያዊ አካል ከጌታ ጋር ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት መውሰድ ነው።

አማኞች ባመኑበት ቅጽበት በቅዱስ ጥምቀት አሰራር ወደ ፍጻሜው የሚያደርሳቸውን መንፈስ ማግኘታቸው አዲስ ኪዳንን ሞልቶ የሚፈስ እርግጠኛ አለኝታ ነው፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ያኔ እርሱ ያንን የወቅቱን የተዋረደ ሥጋቸውን ወደ ክቡር አካል ይለውጠዋል፣ ምክንያቱም ያው አዲስ ኪዳን የአማኞችን የቤዛነታቸውን ሙላት ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር አቆራኝቶት ይገልጠዋልና ነው።

5. እነርሱ እና እኛ

ፊልጵስዩስ 3፥ 21 ከሁሉ በፊት የሚያመለክተው፣ ክርስቲያኖች ገና በሕይወት እያሉ በውስጣቸው እንዲኖር ከተሰጣቸው የማይሞት ምንፈስ ቀጥተኛ ተጽዕኖና ውጤት የተነሳ የማይሞተውን ስለ መልበሳቸው ነው እንጂ፣ ገና ወደ ፊት ይሆናል ተብሎ በብዙዎች ስለሚጠበቅ ከሞት የመነሳትና ከመቃብር ወጥቶ ስለሚመጣ ስለተዳሳሹ አካል መለወጥ ጉዳይ አይደለም። በቀራንዮ መስቀል ላይ በክርስቶስ ሞት ተመርቆ የተሰጠውን፣ በቅዱስ ጥምቀትም አማካኝነት በቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲሰራና በእምነት እንዲታደል እግዚአብሔር በጸጋው ያደረገውንና፣ ደግሞም በ70 አ.ም ላይ ፍርዱን በአሮጌው ሥርአት ላይ አድርጎ ቤዛነታችንን በይፋ ያቀዳጀንን፣ የእግዚአብሔርን አሰራር አለመረዳት አሁንም ገና ወደ ፊት በዘመናት ርቀት ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ድጋፍ የሌለውንና ፈጽሞ የማይኖረውን (NON EXISTENCE) "የሥጋ ትንሳኤ" ያስጠብቃል። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ በገጾቹ አንድም ቦታ ላይ 'የሥጋ ትንሳኤ'፣ ወይም 'አካላዊ ትንሳኤ'፣ ወይም 'ቁሳዊ ትንሳኤ' የሚል ቃልም ሆነ ሃረግ የለውም፤ በቅዱስ ቃሉ እውቅና የተሰጠው "የሙታን ትንሳኤ" ወይም "ከሙታን መነሳት" ብቻ ነው፤ በአንድ በኩልየአስተምህሮ ልዩነታችንም የሚነሳውም ከዚህ የቃል እና የስያሜ አጠቃቀም ዙርያ ነው።

በእነዚያ የሽግግሩ ወቅት በህይወት በነበሩ ቅዱሳን፣ ከእነርሱም አስቀድሞ ሞተው በነበሩት አማኞች እና ከ70 አ.ም በኋላ ባመንን በእኛ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋል። እነርሱ፣ ማለትም በሕይወት የነበሩ ቅዱሳን የማይሞተውን አካል ተቀብለው በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለመኖር ሊወሰዱ የሞታቸውን ጊዜ ሳይሆን የዳግመኛ ምጽአቱን ፓሮውዥያ መጠበቅ ነበረባቸው። በሽግግሩ ወቅትና በአሮጌው ኪዳን በታች ሆነው ከፓሮውዥያው በፊት ያንቀላፉቱ ሙታን ቅዱሳን ደግሞ ክርስቶስ በትንሳኤው ከሃደስ ያወጣቸውን የቅዱሳን ነፍሳት ባከማቸበት በሰማይ ባለው መቅደስ አደባባይ በመሰዊያው ዙርያ የምጽአቱን ቀን ትንሳኤያቸውን እስኪቀበሉ ድረስ ይጠብቁ ነበር። እኛ ከ70 አ.ም በኋላ ያመንን የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ደግሞ በቅዱስ ጥምቀት አሰራር ባገኘነው አለመሞት ምክንያት ያንን የማይሞተውን አካል በሞታችን ቀን ወዲያውኑ ተቀብለን፣ ከፖሮውዥያው በኋላ ወደ መቅደሱ ውስጥ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ድል ነስተው ከገቡት አእላፋት ጋር በዘላለማዊ ደስታና ክብር እንቀላቀላለን።

ከ70 አ.ም በኋላ ያሉ ክርስቲያኖች ሕያዋን ናቸውና በሥጋቸው በሚሞቱበት ጊዜ ከመስቀሉ በፊት የሞቱ ቅዱሳን እንደነበራቸው አይነት ትንሳኤ አይኖራቸውም። ትንሳኤ የሚያስፈልገው ለሙታን ብቻ ነው እንጂ ለሕያዋን አይደለም። ትንሳኤን የሚለማመዱትም "ገነት ከሆነው ሃደስ" የወጡ ሙታን ቅዱሳን ብቻ ናቸው። ስለዚህም የእነርሱ ትንሳኤ ከሲኦል ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት የሆነ ትንሳኤ እንጂ፣ ልክ 'እንደ ዞንቢ ልቦለድ ፊልም' ከምድር  ጉድጓድ ከመቃብር ወጥቶ የመምጣት አይነት ክስተት አይደለም። እነዚያም የሽግግሩ ወቅት ቅዱሳን በሚሞቱበት ጊዜ ክርስቶስ በትንሳኤው ድል ነስቶ በእርገቱ በማረከውና፣ ወስዶ በሰማይ ወዳለው የመቅደሱ አደባባይ ባመጣው "ገነት በሆነው ሃደስ" የትንሳኤያቸውን ቀን እንዲጠብቁ ተደርገው ተከማችተዋል ብዬ አምናለሁ። ድል ነሺው ንጉሰ ነገስት ጌታ ኢየሱስ ሞትንና መቃብርን በትንሳኤው ድል ነስቶ፣ ግርማን በተጎናጸፈው ዕርገቱ አእላፋት ምርኮኞችን አስከትሎ በክብር ወደ ላይ ወጥቶአል።  በመዝሙር 68፥ 18 "ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ"  በሚለው  መሰረት፣ ከትንሳኤው በኋላ በድል አድራጊነት ግርማው ወደሰማይ ሲወጣ ያኔ ገነትን እና በዚያ በአብርሃም እቅፍ የነበሩትን ሁሉ ማርኮ እና አስከትሎ ወደ ሦስተኛው ሰማይ (2ቆሮንቶስ 12፥ 1-4) ይዟት አርጓል። ጳውሎስም ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ በነበረው ሰማያዊ ጉዞ ገነትን በሰማይ እንጂ አስቀድማ በነበረችበት ስፍራ አላያትም። ስለዚህ ከሰማዕታትና ምርጦች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹ በሰማያዊው ቤተመቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ካለው የደጁ አደባባይ በመሰውያው ስር የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባበቁ እንዲከማቹ የተደረጉ ሁሉ አስቀድመው እንደ ምርኮ በእርግጥ  ወደዚያ የተወሰዱ ናቸው፤ ዮሐንስ በራእዩ፦

 

"አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።"(ራዕይ 6 9-11) ሲል ይነግረናል። 

[ዕርገቱንና ትሩፋቱን የዳሰስሁበትን ጽሁፍ እንደተጨማሪ መረጃ መመልከት ለምትሹ እነሆ ሊንኩ፦ 

http://gizachewkr.blogspot.com/2019/05/blog-post.html]


 እነዚህ ነፍሳት በ70 አ.ም በሆነው ምጽአት ትንሣኤን አግኝተው ከክርስቶስ ጋር የተመለሱና በአዲሱ የማይሞት አካል ከክርስቶስ ጋር የነገሱ ቅዱሳን ናቸው። እኛም አካላዊውን ሞት ስንሞት አምነን ባገኘነው አዲሱ ሕይወት ለዘላለም ከጌታ ጋር ልንሆን በቀጥታ ወደ ሰማይ በክብር እንሄዳለን እንጂ፣ ከቆይታ በኋላ ከመቃብር ወጥተን በአካል ልንመጣ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሲሞቱ ይሄዱበት ወደነበረው መከማቻ ሲኦል አንሄድም። ለእኛ ወደ ሰማይ እንሄድ ዘንድ አሁን ትንሣኤ አያስፈልገንም። ምክንያቱም ከ70ው አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ተስፋ ፍጻሜ በኋላ ሀደስ ከሆነው ሲኦል የሚነሱና የሚወጡ ሙታን አይኖሩም፤ ስለዚህም ከ70 አ.ም በኋላ ላሉ ቅዱሳን ትንሣኤ አስፈላጊያቸው አይደለም፣ ሙታን አይደሉም አይሆኑምና። ነገር ግን ትንሳኤ ከ70 አ.ም በፊት ሞተው በሲኦል ሀደስ ለነበሩ ቅዱሳን አስፈላጊያቸው ነበር። እነርሱ ወደሰማይ መሄድ ከመቻላቸው በፊት ከሲኦል ሀደስ መነሳት ነበረባቸው፣ ወደ ሰማይም ሊገቡ የሚችሉት በማይሞተው የትንሳኤ አካል ብቻ ነው። ሙታን በትንሣኤ ሕያዋንም በመለወጥ ወደሰማይ ሄደዋል። ከ70 አ.ም በኋላ ባለው የመንግስት ዘመን አምነን የዳንን እኛ ደግሞ ወደሰማይ ለመሄድ የሞታችንን ቀን እንጠብቃለን እንጂ አሁን "ሙሉ በሙሉ በሰማይ ነን" ማለት አይደለም። እርግጥ ነው ከስፍራ አንጻር አቀማመጣችን (positionaly) በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ነን፤ ዳሩ ግን በዚህ በምድር በምዋቲውና ፈራሹ አካል ገና እየኖርን በሙላት በሰማይ ልንሆንም ሆነ ሁሉንም የሰማይ በረከቶች አሁን በሙላት ልንለማመድ አንችልም። የለበሥነው ሥጋ ያንን ለመለማመድ የሚያስችለው ተፈጥሮ የለውም፤ ስለዚህ ያ እንዲሆን ይህንን ልብስ አውልቀን ከዚህ ማደሪያችን እስክንወጣ ድረስ እንጠብቃለን።

በ70 አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ የሕያዋን አካላዊ ልዋጤ ሆኗል ወይ? ይህ ልዋጤ የህያዋን አካላዊ መለወጥ እንጂ የህያዋን ትንሣኤ እንዳልሆነ ልብ አድርጉ። ያኔ ሕያዋን ገና አልሞቱም፣ ስለዚህም ገና በምድር ላይ እንጂ በሲኦል ሀደስ አልነበሩም፣ በመሆኑም ሕያዋን ሆነው በምድር ላይ መለወጥን ሊለማመዱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንጂ ከሲኦል ሀደስ መውጣትና መምጣት በሚቻላቸው ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51-52 ሐዋርያው ጳውሎስ የሞቱ ቅዱሳን ከሲኦል ሀደስ ወጥተው በሚነሱበት ጊዜ ለሕያዋን ቅዱሳን ምን እንደሚሆንላቸው አንስቶ ሲናገር፦ "...የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም [ህያዋን ሆነን የቀረን ቅዱሳን] እንለወጣለን።" ይላል። በዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ "የኋለኛው መለከት ሲነፋ" በሙታን ላይ እና በሕያዋን ላይ የሚሆነውን ነገር ልዩነቱን ልብ በሉ። ሙታን የሆኑቱ ከሲኦል ሀደስ እንዲነሱና እንዲወጡ ተደርገው የማይሞተውን አካል እንዲለብሱ ይሰጣቸዋል፤  ህያዋን የሆኑት ቅዱሳንም ደግሞ በዚያንው ጊዜ አስቀድመው በሥጋ መሞት ሳያስፈልጋቸው አካላቸው የማይሞት ሆኖ ይለወጣል። ይህ በእውነት ከቃላት በላይ የሆነ ሊነገር የማይችል ክስተት ነው፣ ጳውሎስ ግን ልንገራችሁ የሚለንና እንድንሰማው የሚፈልገው "ምስጢር" ነው።

በዳግመኛ ምጽአቱ ወቅት ህያዋን ሆነው በምድር ላይ የነበሩ ቅዱሳን ግን ወደ ሰማይ መሄድ እንዲቻላቸው የአካላቸው ልዋጤ አስፈልጓቸው ነበር። ይህ ምናልባት በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ በጣም ስውር የሆነ አደናጋሪ ልዩነት ሊሆን ይችላል፤ መቼም በቃሉ ውስጥ የሌለ ነገር፣ እርሱም የወደፊት የሥጋ ትንሳኤ አለ ብሎ በከንቱ ከማመንና ተስፋ ከማድረግ፣ ቃሉ በግልጽ የሚያስተምረውን የሙታንን ትንሳኤና የመጀመርያው ክፍለዘመን ቅዱሳንን ልዋጤ ማመን ለቅዱስ ቃሉ ትምህርት በብዙ ይቀርባል። ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥ 1-4 ባለው ክፍል የሚያነሳውና አጥርተን እንድንሰማው የሚፈልገው ምስጢር ይህ ነው። በ70 አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ሙታን ተነስተው ሕያዋንም ተለውጠው ከክርስቶስ ጋር ወደ ሰማይ ሄደዋል ብለን ይህንን ምስጢር ለማመን ቃሉ ይደግፈናል። "በድንገት በቅጽበት አይን"፣ ይህም ማለት ወዲያውኑ የህያዋን ተዳሳሹ መዋቲ አካላቸው ከመዋቲነት ወደማይሞት ተለውጧል። ምንም እንኳ ይህ ክስተት አካላዊ ትንሳኤ ወይም የነፍሳት ትንሣኤ ባይሆንም፣ ይህ ግን ትንሣኤን የተቀበሉት ሙታን አዲሱን የማይሞት አካላቸውን በተቀበሉበት በዚያው ጊዜ ህያዋን የነበሩ ቅዱሳንንም በዳግመኛ ምጽአቱ ኩነትና ትሩፋት ውስጥ ተሳታፊ የሚያደርጋቸው እና አዲሱን አካላቸውን እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አንድ ዋና ነገር ነበር። ስለዚህም ሙታን ትንሣኤያቸውን፣ ህያዋንም አካላዊ መለወጥን አግኝተዋል፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 20 እና 21ም ያኔ በዳግመኛ ምጽአቱ ተፈጽሟል። እነዚያም ሙታን የነበሩና የተነሱቱ እንዲሁም ሕያዋን የነበሩና የተለወጡቱ ሁለቱም ወገኖች በአንድ ላይ ጌታን በአየር ለመገናኘትና ከእርሱ ጋር ሊታይ በማይችለው ሰማያዊ ግዛቱ ለዘላለም ለመሆን ተወስደዋል። ቅዱሳኑም በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ናፍቀው ሲጠባበቁት የነበረው ተስፋቸው ይኸው ነበር።

6. ክርስቶስ በሥጋው መነሳቱ

ክርስቶስን በተመለከተ፣ እርሱ በሥጋ ተነስቶ አልነበረምን? በእርግጥም ያለጥርጥር አዎ! "እነሆ ሥጋውን ያኖሩበት ስፍራ"፣ መቃብሩ ባዶ ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሥጋ ላይ ያደረገው ጥበቃና ክልከላ አያስገርምምን? "ከእርሱ አጥንት አይሰበርም" የተባለለት የኢየሱስ ሥጋ "መበስበስን እንዳያይ" ተደርጓል። ነገርግን የክርስቶስ ትንሣኤ አካላዊ ተዳሳሽ እስከሆነ ድረስ የእኛስ እንደዚያው አይሆንምን? ብሎ ለሚጠይቅ፣ መልሳችን ፈጽሞ አይሆንም! የሚል ነው። የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ እርሱ የሰጣቸውን ተስፋ እንደፈጸመው ያውቁና የትንሣኤው ምስክሮች ይሆኑ ዘንድ ለሐዋርያቱ ምልክት እንዲሆናቸው እንጂ ሞቶ የበሰበሰው አፈር፣ በእሳት የተቃጠለው አመድ፣ በጎርፍ የተወሰደው ብስባሽ፣ አውሬ የበላው ግዳይ፣ በአደጋ ምክንያት ተቆራርጦ እዚህና እዚያ የተበታተነው ቁርጥራጭ፣ ቀባሪ ያጣው ጥንብና የአሞራ ሲሳይ ሁሉ ተሰብስቦ እንደገና እንደሚመጣ የምናስብበት አይደለም። የኢየሱስ የሥጋው ትንሣኤ ለደቀመዛሙርቱ የነፍሱን ትንሣኤ ያረጋግጥላቸዋል። ዳዊት የተናገረውን ትንቢት ስሙ ፦

መዝ 16፥ 10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። 

ጴጥሮስም ዳዊት ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ሲናገር አስቀድሞ ማየቱን ሲሰብክ፦

ሐዋ 2፥ 31  ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።

እነዚህ ጥቅሶች መንፈሳዊውን ሞት ስለሚያመለክተው በሃደስ ስላለች ነፍስ እና አካላዊውን ሞት ስለሚያመለክተው የሥጋ መበስበስ የሚናገሩ ናቸው። ኢየሱስ ከሁለቱም አይነት ሞት ተነስቶአል። የኢየሱስ ሥጋ ከሞት የተነሳ ካልሆነ የእርሱ ነፍስ በሲኦል እንደነበረችና ከዚያ እንደተነሳች ደቀመዛሙርቱ ዋስትናና ማረጋገጫ አይኖራቸውም። 

የክርስቶስ አካላዊው ትንሣኤ ክርስቶስንና ድል መንሳቱን በተመለከተ ከእርሱ ጋር አብሮ የተቆራኘውን መንፈሳዊውን ትንሣኤ ለደቀመዛሙርቱ ለማረጋገጥ የግድ  አስፈላጊ ነበር። ኢየሱስ መቃብርንና ሲኦልን ድል መንሳቱ እኛን ከዘላለም ሞት ለመቤዠት የሰጠውን ተስፋ የሚታመንና እርግጠኛ ያደርገዋል። ከእርሱ ሞትና ትንሣኤ ውጭ በማይታየው መንፈሳዊ አለም በእርሱ ህልዎት ፊት በማይሞት አካል ለዘላለም ሕይወት ለመኖር ምንም አይነት እንጥፍጣፊ ተስፋ አይኖረንም። በሥጋ ከሞትን በኋላ በዚህ ፕላኔት ላይ የምድርን አየር እየተነፈስን እና የምድርን ምግብ እየተመገብን የምንኖር እስካልሆነ ድረስ የእኛ ሥጋ አካላዊ ትንሣኤ ምንም ትርጉም የለውም። በእግዚአብሔር ቃል ተስፋ ያልተሰጠ "የሥጋ" ትንሣኤ መጠባበቅ ዝናብ የሌለበትን ደመና እንደመከተል ነው። 

7. የአማኙ ሥጋ

አማኙ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ እንዲሆን በተቀደሰው ሥጋው ላይ ኃላፊነት እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል።

1ቆሮ 6፥ 12 -20 "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።"

የተዋረደው የክርስቲያን ሥጋ (ከ70 አ.ም ጀምሮ) በውስጡ ካለው የማይሞት መንፈስ የተነሳ እና የክርስቶስ (እና የክርስቶስ ብቻ) ከሆነውና ከተለወጠው ደግሞም ከከበረው ሥጋው የተነሳ ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መገለጫን ለብሶአል። ይህ መለወጥ መቼና እንዴት እንደሚሆን በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51-52 የተገለጠውን ማየት ይገባል፤ ጳውሎስ የሚናገረውን ስሙ፦ "ሁላችን አናንቀላፋም" ወይም አንሞትም፣ "ነገር ግን ሁላችን (የብሉይ ኪዳን ቅዱሳንን ጨምሮ) እንለወጣለን" ምን እየተናገረ እንደሆነ ታያላችሁ? ይህ ማለት አንዳንዶች ገና በሕይወት እያሉ ይለወጣሉ ማለት ነው። ጳውሎስ እየጻፈለት ያለው ይህ አይነቱ መለወጥ ተዳሳሽ ከሆነው ባዮሎጂካል አካላቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ሳይኖረው እንዴት ሊሆን ይችላል?  ይህ እንግዲህ ጊዜን አመልካች ከሆኑትና በማቴዎስ 16፥ 28፤ 24፥ 34 ወዘተ ከመሳሰሉት ምንባባት ጋር ተስማሚ ነው። የሚለውን ስሙ፣ ይህ ለውጥ፣ ይህ መንፈሳዊ ክስተት ተፈጻሚ የሚሆነው "የኋለኛው መለከት" ሲነፋ ነው። ስለዚህ የዚህ "የኋለኛው መለከት" ጊዜ የተወሰነና የተመደበ ነው፤ እርሱም የዳግመኛ ምጽአቱ ፖሮውዥያ መለከት ነው፤ ስለሰባተኛው መለከት በራዕይ 11፥ ቁጥር 15 ጀምሮ ምን እንደተባለ ተመልከቱ።

አሁን በዚህ ፍጥረታዊ አካላችን ላይ ለሥጋችን ያለብንን ኃላፊነት ባጭሩ እንመልከት፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በሚል ማመካኛ አርነታችንን በመጠቀም ሁሉን እንዳናግበሰብስ፣ ከአንድም ነገር በታች ለመገዛት ራሳችንን እንዳንሸጥ፣ ይልቁንም የክርስቶስ ብልቶች የሆነው ሥጋችን ንብረትነቱ የጌታ ነውና ሞቶ እስኪቀበር ድረስ ከጋለሞታ ጋር እንዳይተባበር፣ ከዝሙት እንዲሸሽ፣ በንጽህና እንዲጠበቅ፣ እንዳናረክሰው፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያም ነውና እግዚአብሔርን እንድናከብርበት ኃላፊነት አለብን። "እኛንም (ጳውሎስና የቆሮንቶስ ምዕመናን) በኃይሉ ያስነሳናል" ማለቱ ግን ስለሙታን ትንሳኤ ነው እንጂ ስለሥጋ ትንሳኤ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ይህም በ70 አ.ም በምጽአቱ መለከት በፓሮውዥያው ተፈጽሞአል።

ከ70 አ.ም በኋላ ያለን አማኞች በምንሞትበትበት ቅጽበት፣ ያኔውኑ የማይሞተውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ መንፈሳዊውን፣ ሰማያዊውን አካል ተቀብለን ከክርስቶስ ጋር በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ዘላለምን ማሳለፍ እንቀጥላለን። አሁን በዳግመኛ ልደት ያገኘነው አዲሱ ሕይወት፣ እርሱም ከጌታ ጋር የተባበረው አንዱ መንፈስ ከዚህ ምዋቲ ሥጋ ስንላቀቅ በማይሞተው በአዲሱ አካል የሚቀጥል ሕይወት ነው፤ አለመሞትም ይኸው ነው። ሥጋና ደም የሆነው የቀደመው አካላችን ይረግፋል፣ ወደአፈርና ብስባሽ ይመለሳል፣ ከዚያም ፈጽሞ አይኖርም አይታይምም። ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ያመኑ የእግዚአብሔር ምርጦች ብቻ፣ የጻድቃን መንፈሶች ናቸውና፣ ድል ነስተው ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ይገባሉ (ራዕይ 21፥ 27)። እነርሱ ብቻ አለመሞትን አግኝተዋል።  ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ ሥጋ በለበሰው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግን በብቸኝነት መበስበስን እንዳያይ ተስፋ የተገባለት የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ከመሆኑ የተነሳ፣ የእርሱ የከበረ ሥጋ ብቻ ሳይለወጥ ከብልሽት ነጻ የሆነ ሆኖ ይኖራል። "የእኔስ ሥጋ?" ብላችሁ በቅናትም ይሁን በፉክክር አትጠይቁ፤ ለፊተኛው ሰው አፈር ሆኖ ከአፈር የተሰራው ወደ አፈር መመለሱ የተመደበለት ዕድሉ ነው። ይህ ደግሞ አንዲት ጋት ያህል እንኳ አይለወጥም። መበስበስን እንዳያይ ሆኖ በከበረው አካል በሰማይ እንዲኖር የተገባው የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ነው። 

8. ከክርስቶስ ጋር መጋጠም

ሥጋችን ከእርሱ ክቡር ሥጋ ጋር ህብረት በማድረጉ ከብሮአል እንጂ የከበረ ሥጋ ወደ መሆን አልመጣም። አስቀድሜ እንዳነሳሁት፣ ቃል በቃል ለመግለጥ የክርስቶስ ሥጋ በራሱ  የከበረ ነው፤ መበስበስን እንዳያይ ቃል የተገባለት ብቸኛ ሥጋ፣ ይህ የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ነው። የማንም ሰው ሥጋ ቢሆን የመጨረሻ መዳረሻው ወደ ምድር አፈር ይመለስ ዘንድ ነው። የክርስቶስ ሥጋ ግን በሦስተኛው ቀን ከመቃብር ወጥቶ በዕርገቱ ከብሮአል። "እነሆ ሥጋውን ያኖሩበት የእርሱ መቃብር ባዶ ነው"። በሥጋው የሞተውን እርሱን በትንሳኤው መንፈስ ሕያው አድርጎ ክቡር ሥጋውን ከመቃብር በማውጣት የአማኞችን መጻኢ ትንሳኤ እንደ በኩር መርቷል። በእምነት እና በቅዱስ ጥምቀት የትንሳኤውን መንፈስ የተቀበልን የእኛ ሥጋ ደግሞ በጊዜአዊነት የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ለመሆን ከእርሱ ጋር በመተባበር ከእርሱ ጋር አብሮ የከበረ ሆኖአል። እኛ የከበርነው በአቋቋም (positional sense) ደረጃ ነው።

ለምሳሌ፦

ሮሜ 6፥ 4  እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።

ተቀበርን የሚለው ቃል በግሪኩ sunthapto ነው። ቃል በቃል እኛ በአካል ተቀብረናልን? ከቶ አልተቀበርንም። ክርስቶስስ ተቀብሮ ነበርን? በእርግጥ ክርስቶስ ተቀብሮ ነበር። እኛ የተቀበርነው ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ብቻ ነው - ቀብሩ የእርሱ ቀብር ነበር፣ የእኛ ቀብር ግን በቅዱስ ጥምቀት ከእርሱ ጋር በትብብር (አብሮ) መቀበር ነው።

ይኸው ትብብር ራሱ ለፊልጵስዩስ 3፥ 21 ተጠቅሶ ሊያገለግል ይችላል፤ እርሱም (ክርስቶስ) ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ (የተዋረደው ሥጋችን) ክቡር ሥጋውን እንዲመስል (summorphon የእኛን ሳይሆን የእርሱን አይነት ለመሆን መተባበር፣ አብሮ መሰራት) የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል (metaschematizo - ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መግለጫ) ።

ይህ summorphon የተሰኘ ቃል በሌላም ክፍል እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ደግሞ እንይ፦

ሮሜ 8፥ 29 ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ (summorphon) አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤

ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በመጋጠማቸው ምክንያት እርሱን መስለዋል (summorphon ሆነዋል) - ማለትም፣ በእርሱ ምሳሌ አብረው ተሰርተዋል። ከ70 አ.ም ወዲህ በህይወት ለሚኖር አማኝ ለተቀበለው 'አምሳላዊ ልውጠት' (metaschematizo) ወይም ለአዲሱ ሁኔታ ሃላፊነት ያለበት  ከክርስቶስ ባህርይ ጋር ያለው ይህ አንድነትና ትብብር፣ ከክርስቶስ መልክ ጋር ያለው ይህ መመሳሰል (summorphon) ነው።

summorphon ከክርስቶስ ባህርይ ጋር መተባበርን እንጂ ከክርስቶስ ባህርይ ጋር  ትክክለኛ መመሳሰልን አያሳይም። ይህንን የስፍራ ትብብር (positional) በሮሜ 6 ላይ፦ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መቀበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መሰቀል፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፤ በኤፌሶን 2 ደግሞ፦ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ማግኘት፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው ስፍራ አብሮ መቀመጥ፤ በቆላስይስ 2 ላይም፦ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መቀበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፣ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ማግኘት፣ በሚል ተብራርቶ እናየዋለን። ሁሉም የትብብር አገላለጽ ነው፣ የአማኙን ከክርስቶስ እውነታ ጋር ያለ የስፍራና የደረጃ (positional) አቋም የግድ ይላል። ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ ተነስቶ፣ በህይወት በመኖር፣ በሰማያት ተቀምጦአል። አማኙ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ተሰቅሎ፣ አብሮ ሞቶ፣ አብሮ ተቀብሮ፣ አብሮ ተነስቶ፣ አብሮ በህይወት በመኖር፣ በሰማያት አብሮ ተቀምጦአል። በክርስቶስ ያለው እውነታው ነው፣ በአማኙ ያለው ደግሞ ከዚያ እውነታ ጋር መተባበር ነው።

እንግዲህ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለው አስፈላጊ ነገር መሰረታዊ ከሆነው ከክርስቶስ ባህርይ ጋር መተባበር ነው። የአማኙ 'አምሳላዊ ልውጠት' (metaschematizo)፣ አዲስን ሁናቴ መልበስ፣ አዲስ ፍጥረት ሆኖ እንደገና መሰራት፣ እንደገና መዋቀር  ሊኖር የሚችለው በዚያ መንገድና በእርሱ በኩል ብቻ ነው። 

ማጠቃለያ

ስለዚህ ጳውሎስ እያለ ያለው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ አማኞች ገና በተዳሳሹ አካል በስጋቸው ውስጥ እያሉ ይለወጣሉ፣ መንፈሳቸውም የማይሞት ይሆናል፣ ነው። ይህ ለውጥ ደግሞ የሚሆነው አማኞች ከክርስቶስ የከበረ አካል ጋር በመተባበራቸው ምክንያት ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51 ላይ የተነገረለትም መለወጥ ይኸው ነው፦

1ቆሮ 15፥ 51-52 እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።

ለእርሱ የተመረጡትን ለመሰብሰብ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ድምጽ ጋር ልኳቸዋል (ማቴዎስ 24፥ 31)፣ ይህም የጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 16)፤ እነሆ የኋለኛው መለከት እርሱም ሰባተኛው መለከት ተነፍቷል(ራእይ 11፥ 15)፤ መንግስትም የጌታችን ሆኗል። ዘመኑም ተለውጧል። በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፍቷል። ትንሳኤም ልዋጤም ካሁን በፊት ሆኗል።

ይህ "ልዋጤ" እንዴት እንደሚሆን አሁን ጳውሎስ የሚናገረውን ተመልክተን እናብቃ፦

ፊል 3፥ 21 እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

"ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር"፥ ሲል ይናገራል። ይህ ልዋጤ በአማኞች ውስጥ የሚከናወነው ክርስቶስ ሁሉን ለራሱ በሚያስገዛበት አሠራርና ጊዜ ነው። ይህ አሠራር የእግዚአብሔር አሠራር ነው። ያ የሚሆነው መቼ ነው? 

1ቆሮ 15፥ 24-26 በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ 

አሠራሩና ሥራው የሚፈጸምበት ጊዜ አይተላለፉም፤ ነገር ሁሉ በጊዜው ውብ ሆኖ ተሰርቷል። በሞቱና በትንሳኤው ተሰርቶ የተመረቀው፣ ግርማን በሞላው የክርስቶስ ክቡር ኃይል በይፋ ተገልጦ በሙላት የተሰጠን አለመሞት የክርስቶስ የሁሉን ቻይነቱ አሰራር ነው። ይህም መንፈሳዊውን ሞት ደምስሶ አለመሞትን ያመጣበት አሰራር ይፋ የሆነው በዳግመኛ ምጽአቱ ነው። ከዚህ የተነሳ ምእመናን አሁን የማንሞት ሆነናል፣ በሚሞት ሥጋችን ውስጥ የማንሞት ሆነን እንኖራለን። በሥጋ ስንሞት ደግሞ፣ አስቀድሞ በዳግመኛ ልደት እንዳይሞት የተደረገው መንፈሳችን የማይሞተውን ሰማያዊ አካል ይለብስና ለዘላለም ከጌታ ጋር በሰማይ ይሆናል። ምክንያቱም ህይወትንና ህያውነትን ባመጣበት በክርስቶስ አምነን በቅዱስ ጥምቀት አለመሞትን ተቀብለናል።

♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦

ለዚህ ጥናት እንደ ግብዓት የተጠቀምኳቸው የጽሁፍ ስራዎች

Bromiley, Geoffrey W.; Theological Dictionary of the New Testament

Denton, T Everett; Pertinent Parousia Passages

Karl Rahner; Encycopedia of Theology  

Meek, Charles S; Christian Hope through Fulfilled Prophecy

Martin, Brian L; Behind the Veil of Moses

Nicholas, Michael Alan, preterism and the Afterlife

Raphael, Simcha Paull; Jewish Views of the Afterlife

Terry, Milton S;  Biblical Apocalyptic