"በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል"
ጌታ ኢየሱስ እንደተስፋ ቃሉ በ70 አ.ም ላይ በደመና ተመልሶ የመጣው እንዴት ነው? ይህንንስ ለማመን የሚያስችለን ምን የቃሉ ድጋፍ አለን? በዚህና መሰል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለበርካታ ጊዜ በተለያየ አቀራረብ የጻፍሁና ያስተማርሁ ቢሆንም ነገሩን ደጋግሞ ማንሳት ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል።
"ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።" ማቴ 24: 29-31
ትንቢት ላይ "ሁሉ ተፈጽሟል፣ ሳይፈጸም የቀረ ምንም የለም" ብዬ ለያዝሁት አቋም እና ለምከተለው የነገረ ፍጻሜ እይታ ተገቢና ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ ያለኝ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማረጋግጥ በግሌ መልሱን ለማግኘት እየፈለግሁ ከማነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎቼ መካከል አንዱና ዋናው ይህ በመግቢያዬ ላይ ያቀረብሁት ጥያቄ ነው፡፡ በውኑ ጌታ ኢየሱስ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታይቷልን? የተፈጸመውን ትንቢት በወጉ ለመተርጎም አንዱ ቁልፍ የሆነ ነጥብ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደመና የሚያስተምረውን መረዳት ነው። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ጌታ በፍርድ የመምጣቱን እውነት ለመግለጥ አዘውትሮ ይህንን ደመና የተሰኘ ኮስሞሎጂካል የሆነ አምሳል ይጠቀማል።
"በደመና ይመለሳል፣ በሚያስደንቅ ክብር ይገለጣል፣ ልጆቹን ፍለጋ ይመጣል፤…" እያለ ዘምሮ ለኖረ እንደኔ ላለው ሰው፣ "የለም ቀደም ሲል መጥቷል" የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ምን ያህል አዙሮ ሊደፋው እንደሚችል መቼም መገመት አያስቸግርም። በእርግጥም በርካታ ሰዎች ከዚህ ደብረ በጥብጥ ከሆነ ምልከታ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ሲፋጠጡ ከፍ ባለ የደም ግፊት ይህንኑ ጥያቄ አንስተው ይጠይቃሉ። እንደዚህ ማመኔን የሚያውቅ አንድ መጋቢ ወዳጄ እየቀለደም ቢሆን 'እንዴት መጥቷል ለማለት ደፈርክ? ሲመጣስ አይተሃል ወይ?" ሲልም ጠይቆኛል።
ሰዎች ሲመስላቸውና ሲገምቱ ይህ ትንቢት በ70 አ.ም ላይ አልተፈጸመም ሲሉም ይከራከራሉ። ቁሳዊውን የዝናብ ደመና ወይም የነፋስ ደመና እየተጠባበቁ አይናቸውን አንጋጠው ሰማይ ሰማዩን የሚመለከቱ ወዳጆቼን የምመክረው ከሰማዩ ፊት ይልቅ የመጽሐፉን ገጾች እንዲያገላብጡ ነው፤ የሰማዩን ፊት ማየት የሚጠቅመው ለሜትሪዮሎጂ ብቻ ነው፣ ለእምነት ቤተሰብ ግን ቅዱሳት መጻህፍትን ብቻ እንዲመለከቱ ያስፈልጋል። የሆነው ሆኖ ቃሉን እንደተጻፈው አምነው ምንም ሳይጨምሩበትና ሌላ ውጫዊ ድጋፍና ክራንቻ ሳያቀርቡለት ሌጣውን እያነበቡ የተቀሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በጥንቃቄ ለሚመረምሩ የቃሉ ተማሪዎች ሰብአዊው ክብር ካልተናነቃቸው በቀር፣ በእርግጥም ጌታ በ70 አ.ም ላይ በደመና እንደመጣ በግልጽ ለማየት አይሳናቸውም። "መጻህፍትን … አታውቁምና ትስታላችሁ" የተባለው ዘለፋ ትንሳኤ ሙታን የለም ብለው የክህደት አቋም ለሚያራምዱ ሰዱቃውያን የተሰጠ ነገረ ፍጻሜአዊ ተግሳጽ መሆኑን አስተውሉ። ዛሬም ህልቆ መሳፍርት እርማት የሚገባው ነገረ ፍጻሜአዊ የእምነትና የክህደት አቋም ይዘን እንደሰዱቃውያን የቂል ጥያቄ የምናነሳ ቃሉን ያወቅን የመሰለን ሁላ ለምን እና በምን እንደሳትን እናውቅ ዘንድ ከዚህ የጌታችን ዘለፋ ተግሳጽን ተምረን ወደመጽሐፉ ገጾች እንመለስ።
ከሁሉ በፊት አክዬ ላነሳው የምወደው ጌታ ኢየሱስ በጊዜው ይኖር የነበረው ሊቀ ካህናቱ እንኳ ይህንን ኹነት ሲፈጸም በአይኑ ለማየት እንደሚበቃ የተናገረውን ነው፦
"ኢየሱስ ግን ዝም አለ፦ ሊቀ ካህናቱም፦ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።" ማቴ 26፥63-64
አንዳንዶች ይህ የሚያመለክተው በሲኦል እና በምድር ላይ ያሉ ኃጢአተኞች ሁላቸውም ገና ወደፊት እርሱ ሲመጣ ያዩታል እንደሚል አይነት አድርገው ነው። ይህ ግን ምንም ስሜት የማይሰጥ የፈጠራ ትርጉም ነው። እስቲ ይህንን በማሰብ እንኳ ጀምሩ፣ የሰው ልጅ በደመና ሲመጣ በሲኦል ያሉ ነፍሳት እንዴት ያዩታል? ኢየሱስ ለዚህ ሰው ሲናገረው፣ ኢየሱስ በኃይል ቀኝ ወይም በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ሲቀመጥ የሚያየው መሆኑንም ጭምር ነው። አሁን ጥያቄው፣ ኢየሱስ በሰማይ ከነበረና በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ከሆነ፣ ሊቀ ካህኑ በግሉ ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ለማየት የሚበቃው እንዴት ባለ ሁኔታ ነው? የሚል ነው። እንደሚታወቀው ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ እና በአባቱ ዙፋን ቀኝ ሲቀመጥ ሊቀ ካህኑ በዚያ ሰማያዊ ትዕይንት ፊት አልነበረም። ዙፋኑ የሚገኝበት ብቸኛ ስፍራ እዚያ በሰማይ ነውና። ይህ የሚናገረው ሁሉም ከሞቱ በኋላ ፍርዳቸውን ሊቀበሉ በፊቱ በሚቆሙበት ቀን ማለትም በፍርድ ቀን ስለሚሆነው የሚናገርም ፈጽሞ አይደለም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ተመሳሳይ ነገር ለደቀ መዛሙርቶቹም ነግሯቸው ነበርና፣ እነርሱም ይህንን ኹነት የሚያዩት ከሞቱ በኋላ በሰማይ ወይንም በሲኦል ሆነው እንዳልሆነ፣ ይልቁንም አንዳንዶቹ ገና በህይወት እያሉ የሚሆንና የሚያዩት እንደሆነ በግልጥ ነግሯቸዋል።
"የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።" ማቴዎስ 16፥ 27-28
እዚህ እንደተጻፈው እነዚህ ሰዎች ይህ ሁኔታ ከመፈጸሙ በፊት ሞትን አያዩም። በሌላ አባባል፣ ይህ እስኪሆን ድረስ ከጠላቶቹም ሆነ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል የሚሆነውን በአይናቸው ለማየት ገና በህይወት የሚኖሩ አሉ ማለት ነው። ይህም እንግዲህ ከስጋቸው ተለይተው፣ ገና ወደፊት በትንሳኤ ቀን የሚሰጣቸውንና በአዲሱ መንፈሳዊ አካል ውስጥ የሚኖረውን አዲሱን መንፈሳዊ ህይወት ተቀብለው እንደሚያዩት አድርጎ የሚያመለክትም ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ብዙዎች እንደሚመስላቸው የትንሳኤ ቀን ገና ወደፊት ከሆነና፣ እነዚህም ሰዎች ሞትን ካዮ ዘመናት የተቆጠረ በመሆኑ፣ ይህም እስካሁን ድረስ ሳይሆን ቀርቶ፣ ወይም ከዚህ በኋላ ገና ላልታወቀ ረዥም ወይም አጭር ዘመን ተላልፎ ከሆነ፣ ወይም ይህ ሊሆን የማይቻል አስቸጋሪ ነገር በመሆኑ ጌታ ቃሉን አጥፎ ከሆነ፣ እነርሱም በህይወት እያሉ ይህ መሆኑን ሳያዩ ሞተው ሁለት ሺህ አመታት ያለፈው ከሆነ፣ በአጭሩ ይህ ንግግር በሃሰተኛ ተስፋ የተሞላ ተራ ማታለልና ማደናገር ከመሆን በቀር ሌላ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ንግግሩንም በዚህ መንገድ ተረድቶ የሚተረጉም የመጻኢነት አቋም ጌታ ኢየሱስን እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው እውነተኛ ነብይ እና እንደ እግዚአብሔር ልጅ አያከብረውም፤ ኢየሱስን የማያከብር ትምህርት እና የእምነት አቋም ከኔ ይራቅ። ኢየሱስ ግን ይህንን ሲናገር በ70 አ.ም ላይ በፍርድ የሚመጣ መሆኑን እያመለከተ ነበር።
ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በ70 አ.ም ላይስ በደመና መጥቷል ሊባል እንዴት ይቻላል?
ብሉይ ኪዳን ለበርካታ ጊዜ እግዚአብሔር በህዝቦች ላይ ለመፍረድ እንደሚመጣ ሲያመለክት በደመና የመሆንን ሃሳብ ይጠቀማል። ይህም ደግሞ ከጥንቆላ ጋር ወይም ከግኖስቲሲዝም ጋር የሚመሳሰል የቅዱሳት መጻሕፍት አንዳንድ ምስጢራዊ ትርጓሜዎች አይደለም። እንዲህ ያሉ ማጣቀሻዎችን ለማግኘት ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ፣ ወደ ሌላ ቦታ ተመልክተን ቢሆን ኖሮ ምናልባት ያኔ "ሚስጥራዊ" ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በብዙ ማጣቀሻ ስለዚሁ ጉዳይ በግልጥ የሚናገሩ በመሆኑ በደመና የመምጣት ጽንሰ ሃሳብ ለመጽሐፍ ቅዱስ ባእድና እንግዳ ነገር አይሆንም። ጌታ ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱም ሆነ ለተቀሩት ሁሉ ዳግመኛ ምጽአቱን አስመልክቶ ሲናገር ሁላቸውም ሊግባቡ በሚችሉበት በግልጽ ቋንቋ በሰማይ ደመና፣ አባቱ እንደሚመጣ የሚመጣ መሆኑን ነገራቸው እንጂ፣ ነገሩን እያመሳጠረ የማይገባቸውንና የማያውቁትን ባእድ ነገር አልተናገረም። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መምጣት በደመና እንደነበረ ሁሉ፣ እንደዚያም ባለ ሁኔታ ሲመጣ በህዝቡና በአህዛብ ላይ ፍርድን በሚያደርግበት አኳኋን ነገስታትንና ሰራዊቶቻቸውን ለጦርነት እንደሚያስከትት ሁሉ፤ ልክ እንደዚሁ በአዲስ ኪዳንም እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነው የጌታ በደመና መምጣት በእስራኤል ላይ ፍርድን በኢየሩሳሌም ላይም ውድመትን በሚያደርግበት አኳኋን በአህዛብ ሰራዊቶች አማካኝነት የተፈጸመ ነው። አዲስ ኪዳን እንግዳ የሆነና ብሉይ ኪዳን የማያውቀው ሌላ አይነት ተፈጥሮ ያለው የጌታ በደመና መምጣትን አያስተዋውቀንም። እንግዲህ ወደሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት መመልከት የሚገባንም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን እንዲተረጉምና የገዛ ራሱን ትምህርት በገዛ ራሱ እንዲደግፍ መፍቀድ ስላለብን ነው።
ዳዊት ጠላቶቹ ባሳደዱት ጊዜ ተጨንቆ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኽ የነበረውን ሁኔታ ሲያብራራ የሚለውን እዩ፦
"በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።" 2ሳሙኤል 22፥ 7
የእግዚአብሔርም ምላሽ ምን እንደነበር ደግሞ ተመልከቱ፦
"ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፤ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩብም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፤ መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ። በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ። እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፤" 2ሳሙኤል 22፥ 8-14
ይህ ማለት እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ በፍርድ መጥቶ ነበር ማለት ነው። ዳዊት ሲናገር እግዚአብሔር ጨለማን ከእግሩ በታች ረግጦ የሰማዩንም ከባድ ደመና መሰወርያው ወይም ድንኳኑ አድርጎ፣ በኪሩብ ላይ ተቀምጦ መጣ ይላል።
በውኑ ዳዊት ይህንን ተዳሳሽ በሆነ መንገድ አይቷልን? በእርግጥ እንደዚያ አላየም። ዳዊት ግን በመንፈስ ተነድቶ በአሳዳጅ ጠላቶቹ ላይ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ፍርድ በደመና እንደመምጣት አድርጎ እየገለጠው ነበር። በብሉይ ኪዳን በነበሩ ቅዱሳን አስተሳሰብ ውስጥ ይህ እጅግ የታወቀ የእግዚአብሔር ስዕል ነበር። ክርስቶስ በደመና እንደሚመጣ ለሊቀ ካህኑ በነገረው ጊዜ ይህ በደመና ስመጣ ታያለህ እያለው ያለው ሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ እያለው እንደሆነ በትክክል ያውቃል። ክርስቶስ እንዳልተሳሳተ ደግሞም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ እርሱም በሊቀ ካህንነቱ ዘመን ገና በሕይወት እያለ ኢየሩሳሌምን ለማውደም በፍርድ የሚመጣ መሆኑን ኢየሱስ እየነገረው መሆኑን ያውቃል።
ኢየሱስ ሊቀ ካህኑ በውል የማያውቀውን ነገር እየተናገረ አልነበረም። ከ2000 አመታት በኋላ የሚፈጸምና በተለይ ለቤተክርስቲያን ብቻ ግልጽ የሆነ ነገር እየነገረውም አልነበረም። ይልቁን ሊቀ ካህኑ ሊገባው የሚችለውንና ለእርሱ በጣም ታዋቂ የሆኑ ቃላትን ነበር የሚነግረው፤ ሊቀ ካህኑም ኢየሱስ እየተናገረ ያለውን ነገር በትክክል አውቆታል። የሊቀ ካህኑንም ምላሽ ብትመለከቱ ከዚያ የተነሳ ልብሱን ቀድዶ "ተሳድቧል" ብሎ እንደጮኸ ታያላችሁ።
"ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፦ ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ።" ማቴዎስ 26፥ 64-65
ሊቀካህኑ በደመና መምጣት እግዚአብሔር በፍርድ የሚመጣበት አመጣጡ መሆኑን ለመደገፍ እዚህ ላይ ያነስሁዋቸውን እና ከዚህም በኋላ የምጠቅሳቸውን እነዚህን የቅዱሳት መጻህፍት ንግግሮች ያስታውሳቸዋል። ኢየሱስ እያለ ያለው እርሱ በፍርድ የሚመጣው የብሉይ ኪዳኑ አምላክ መሆኑን ነው። ኢየሱስ እያለ ያለው ይህ የሰው ልጅ አምላክ ነው የሚል ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ደግሞ ልክ በብሉይ ኪዳን ዘመን የአህዛብ ሰራዊትን ተጠቅሞ ይፈርድባት እንደነበር ሁሉ ኢየሩሳሌም ላይ የሚፈርደውም እርሱ መሆኑን ጭምር ነው።
እግዚአብሔር በደመና ውስጥ መሆኑ እና መገኘቱ ጽድቅንና ፍርድን፣ ሕዝቡን ለማዳን ወይም በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ ሲመጣ የሚገለጠውን መለኮታዊ ሕልዎቱን የሚያመለክት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። ከብዙ በጥቂቱ እነዚህን ምሳሌ የሚሆኑ ምንባባት ተመልከቱ፦
"ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው።" መዝሙር 68፥ 34
"ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።" መዝሙር 97፥ 2
"እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥" መዝሙር 104፥ 3
"በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ቢመለከቱ፥ እነሆ፥ ጨለማና መከራ አለ፤ ብርሃንም በደመናዎችዋ ውስጥ ጨልሞአል።" ኢሳይያስ 5፥ 30
"እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው?" ኤርምያስ 4፥ 13-14
"የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።" ሕዝቅኤል 30፥ 3
"የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፥ እርሱም ቀርቦአልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፤ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤" ኢዩኤል 2፥ 1-2
"እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።" ናሆም 1፥ 3
"ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል። ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው። በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፥ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይፈስሳል።" ስፎንያስ 1፥ 14-17
ይህ እንግዲህ አሁንም አሁንም እየተደጋገመ የተነገረ ነው። ሊቀ ካህኑን ጨምሮ ኢየሱስ እንደዚያ ሲል የሰሙ እያንዳንዳቸው እነዚያን ቃላት የሚርዷቸው፣ የእግዚአብሔርን በፍርድ መምጣት በሚያመለክቱበት ደረጃ ቀርበው ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎች መሰል ጥቅሶችን በሚያስታውሱበት መንገድ ነው።
"እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።" ራእይ 1፥ 7
ዮሐንስ በራእዩ ክርስቶስ በደመና እንደሚመጣና በኢየሩሳሌም ያሉ የወጉት ሁሉ እንደሚያዩት ይናገራል። ይህንንም የወጉት ወይም የሰቀሉት ሰዎች በነበሩበት ሥፍራና ትውልድ የሚፈጸም መሆኑን ግልጽ ያደርጋል። የወጉት እነርሱ የሰው ልጅ መምጣት ምልክትን ያያሉ። መላው የአይሁድ ሕዝብና ነገድ ሁሉ በሚመጣው የእርሱ ፍርድ ምክንያት የሚወድመውን ከተማቸውን፣ የሚሆንባቸውን መቅሰፍተ እልቂት እና የሚቃጠለውን ቤተ መቅደስ እያዩ ዋይ ዋይ ብለው ያለቅሳሉ። የሮማውያን ጦር በ70 አ.ም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ ሲያወድማት ይህ ተፈጽሞባቸዋል። በደመና መምጣት የፍርድ መምጣት እንደሆነ፣ ፍርዱም በወጉት ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሩን ልብ በሉ። በደመና የሚመጣ ያህዌ ራሱ መሆኑን ከብሉይ ኪዳን ትምህርት ጠንቅቆ የሚያውቀው ሊቀ ካህኑ በደመና እመጣለሁ የሚለውን ይህንን የኢየሱስን ንግግር ሲሰማ "ተሳድቧል" ሲል ጮኸ። ሊቀ ካህኑ በመገረም ራሱን እያከከ ይህ ምን አይነት ነገር ነው የሚናገረው ሲል ከ2000 አመታትና እና ከዚያ በኋላ ስለሚሆን ነገር እየተናገረ ነው እንዴ አላለም። ሊቀ ካህኑ ጉዳዩ ገብቶታል። ኢየሱስም ይህ ሲሆን ታያለህ ብሎ ለሊቀካህኑ በግልጽ ነግሮታል።
ኢየሱስ በተዳሳሹ ደመና በአካል ሲመለስ በገሃድ ያየው አለን? አንድ ስንኳ የለም።
ከ66-70 አ.ም ድረስ በተካሄደው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ስትደመሰስ ግን ያኔ ፍርዱን አይተዋል። ኢየሱስም እርሱ በደመና ሲመጣ ሰዎች እንደሚያዩት የተናገረው ይህንንው ነው። የእርሱን ፍርድ፣ ማውደሙን እንደሚያዩ ነው የነገራቸው እንጂ በገሃድ በደመና ላይ ተሳፍሮ በአካል ከሰማይ ሲወርድ ያዩታል ማለት አይደለም። በደመና መምጣት በቀላሉ የውድመት እና የእግዚአብሔር ቁጣ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህም ውድመቱን ያያሉ።
አንዳንዶች ግን አሁንም "በሐዋርያት ሥራ 1፥ 9 ላይ ኢየሱስ በአካል ሲያርግ በሚታይ ደመና ሄዶ አይደለም ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
አዎ ልክ ነው። ክፍሉም እንዲህ ይላል፦
"ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።" ሐዋርያት 1፥ 9-11
በርካታ መጻኢያን የሆኑ ተርጓሚ ወዳጆቼ ይህንን ጥቅስ ይወዱታል፡፡ ምናልባትም የጌታን ምጽኣት ጨምሮ “ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል” ብለን የምናምነውን እኛን ኃላፋውያንን ለመቃወም ምቹ የሆነ ጥቅስ እንዳገኙ ያህልም ይሰማቸዋል፡፡ ለበርካቶች መጻኢያን ለሆኑ ተርጓሚዎች የህንን ክፍል ያኔ በ70 ዓ.ም ከሆነው ሁናቴ ጋር አጣጥመው በዚያው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተርጉሞ መረዳት ስለሚቸግራቸው፣ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተሰጠውን ቀጥተኛና ግልጹን ትምህርት ስተው፣ ይህንን ጥቅስ ብቻውን ለመተርጎም በሚያደርጉት ሙከራ፣ በትርጉማቸው ውስጥ የቀዋሚነት (Consistency) ስህተት እንደሚፈጽሙ አይታያቸውም።
ጉዳዩን በስሱ ለመመልከት ያህል፣ በመላው ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር በደመና መምጣት መለኮታዊ ሕልዎቱን እንዲሁም ሕዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ “እንዲሁ ይመጣል” የተሰኘው መግለጫ ደመናውን የሚያመለክት ነው ቢባል እንኳ፣ እንግዲያውስ አሳማኝ ለሆነና ቀዋሚነት ላለው ትርጉም፣ በቅዱሳት መጻህፍት በደመና መምጣት ማለት ምን እንደሆነና ምን ተፈጥሮ እንዳለው ከፍ ሲል ባየነው መሰረት ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡ እንዳትሳሳቱ፣ ኢየሱስን በእርገቱ ጊዜ “ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው”፣ ሲል ስለ መምጣቱ ግን “ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” ነው የተባለው እንጂ በዚህ ጥቅስ አካሄዱ ላይ ካልሆነ በቀር አመጣጡ ላይ ደመና አለመጠቀሱን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ያም ቢሆን እንደ ብዙዎች እምነት፣ እንበልና፣ በሄደበት አይነት ደመና የሚመለስም ቢሆን እንኳ የሚመለሰው ሲሄድ ላዩት ሰዎች፣ በዘመናቸውና በትውልዳቸው ነው እንጂ፣ ከእነርሱ ዘመን እና ትውልድ ውጭ ለምንኖር ሲሄድ ላላየነው ነው ብለን ድርቅ ማለት አይገባንም። "ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም።" (ምሳሌ 29፥ 1) እንደተባለ፣ ቃሉ አለመማሩን እየነቀፈና እየዘለፈ ያላለዘበው ግትርነት ጉዳቱ የከፋ ነው።
በሌሎች በርካታ የምጽዓቱ ምስክሮች በሆኑ የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተሰጠውን ተስፋ ታሪካዊ ፍጻሜ ብንመለከት፣ በ70 ዓ.ም በእስራኤል ላይ የሆነው ፍርድና የክርስቶስ መምጣት በተጨባጩ ተዳሳሽ ደመናም ሆነ ወይም በተዳሳሽ አካል የሆነ እንዳልሆነ እናስተውላለን፡፡ ይህም የ70ው ዓ.ም ምጽዓት ጭምር በብሉይ ኪዳን እንደተገለጹት ተደጋጋሚ የእግዚአብሔር መምጣቶች መንፈሳዊ መምጣት ሆኖ፣ ነገር ግን እውነተኛና ተጨባጭ ነበር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ብሉይ ኪዳን የማያውቀውን አይነት የመለኮት አመጣጥ ሊመጣ በሚታይ ደመና አልሄደም። የልጁ አመጣጥ ልክ እንደ አባቱ ነው። “የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል” (ማቴ 24÷ 30)፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ መስተዋል የሚገባው አንድ እውነት ይታያል የተባለው “የሰው ልጅ ምልክት” ሥፍራው ˝በሰማይ˝ ማለትም በመንፈሳዊው ዓለም እንጂ በምድር ወይ በጠፈር አለመሆኑን ነው፣ የሚመጣበት ደመናም ቢሆን የሰማይ ደመና ነው እንጂ የሄደበት አይነት የሚታይ ደመና አይደለም።
በዚህ የሐዋርያት ሥራ 1፥ 9-11 ባለው የንባብ ክፍል ላይ ያቀረብሁትን ትምህርት ለማየት ፍላጎቱ ያላቸውን የቃሉን ወዳጆችና ተማሪዎች በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ገብተው በብሎገሬ ላይ የተለጠፈውን ዘለግ ያለ ጽሁፍ እንዲመለከቱ ግብዣዬ ነው።
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/02/1-9-11.html