Monday, March 16, 2020

ቅዱስ ጥምቀትን የሕጻናት ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊነት

ወንድም ስሜ ታደሰ "ሕፃናት መጠመቅ የለባቸውም!!!" በሚል ርእስ አቋም ይዞ፣ በተለይ የእኛን የሉተራውያንን የጥምቀት ትምህርትና ልምምድ ለማብጠልጠል፣ የመጥምቃውያንንም ትምህርት ትክክል ለማድረግ  በፌስ ብክ ገጹ ላይ ያቀረበውን ጽሁፍ ከተመለከትሁ ብኋላ እምነታችንን መረር ብዬ ለመከላከል አንድ ነገር ለማለት ሳስብ ቆይቻለሁ። በዚህም መሰረት የዚህች ትንሽ ጽሁፍ አብይ ሃሳብ አንባብያን በሁለቱ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የአስተምህሮ ልዩነት እንዲያውቁትና በጥምቀት አንጻር ማንኛችን በቃሉ መሰረት ላይ እንደቆምን፣ የማንኛችን አስተምህሮ ደግሞ ከቃሉ የተፋለሰ እንደሆነ እንዲረዱ ነው እንጂ፣ ፓስተሩ በጽሁፉ ስለ ኦርቶዶክስም ሆነ ስለ ሉተራውያን ያነሳውን ጉዳይ ሁሉ መተቸትና ማረም አይደለም። በአጭሩ ግን የጥምቀትን መሰረተ እምነት አንስቼ በተለይ የሕጻን ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊነት እና አስፈላጊነት ላይ በማተኮር ከዳግመኛ አጥማቂው መጋቢ ስሜ ታደሰ የተሰነዘረውን ተቃውሞ እንደ ሉተራዊ ቄስ እመክታለሁ። የመጋቢ ስሜ ታደሰን ልጥፍ ላላያችሁ እነሆ ሊንኩ   https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=3263258677035110&id=100000530293951

የጥምቀት መሰረተ እምነት
ጥምቀት በእግዚአብሔር ፈቃድ የታዘዘና የተመሰረተ (ማቴዎስ 28) በውኃ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ቃል ወይም ጳውሎስ እንዳለው "በቃሉ መታጠብ" (ኤፌሶን 5፥ 26) ነው እንጂ፤ በሰው የተፈቀደና የተመሰረተ፣ በውኃ ውስጥ ያለ ምትሃት፣ ወይም በውሃ መታጠብ ወይም ሌላ ማንኛውም ነገር አይደለም። ቅዱስ አውግስጢኖስም ከዚህ በመነሳት "ቃሉ በምልክቱ ላይ ይጨመር፣ ውጤቱም ቅዱስ ምሥጢር ይሆናል" ብሎአል። ከዚህ በተለየ ግን የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሆነውን ቃሉን በመዘንጋት እግዚአብሔር ኃጢአትን ሊያጥብ የሚችል አንዳች መንፈሳዊ (ምትሃታዊ) ኃይል በውኃ ውስጥ አስቀምጦአል፣ በውኃውም አማካኝነት ኃጢአትን ያጥባል፣ ጥምቀትም ኃጢአትን የሚያጥበው በመለኮታዊ ፈቃድ እርዳታ አማካይነት ነው፣ ይህም ማለት እጥበቱ የሚከናወነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ እንጂ በቃሉም ሆነ በውኃው አይደለም ብለው የሚያምኑና የሚያስተምሩ ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም። ምክንያቱም ጥምቀት የተጸለየበት ውኃ፣ የውሃ ጥምቀት፣ ወይም የተደገመበት የአስማት ውኃ ወይም ሌላ ምናቸውም ነገር ሳይሆን ጥምቀት የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል የተዋሃደው ውኃ ነው እንጂ ውኃ ብቻ አይደለም። እርሱም የአዲስ ልደት መታጠብ ነውና ጥምቀትንም ጥምቀት የሚያሰኘው ይኸው ነው። 

እደግመዋለሁ፣ ጥምቀት ተራ ውሃ ወይም የውሃ ጥምቀት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ዐውድ የተቀመጠና በእነርሱም የተቀደሰ ውሃ ማለት ነው። ውሃው በራሱ ከሌሎች ውሃዎች የበለጠ የከበረ ሆኖ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ስለተጨመሩበት መለኮታዊ ውሃ፣ ደግሞም ቅዱስ ጥምቀት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። ውሃው ምልክት ነው፣ ከጥምቀቱ ውሃ ጋር ተዋህዶ ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል ቅዱስነት ባለማስተዋል ጥምቀት ቅዱስ በሚል ተቀጥላ መጠራት አይገባውም የሚሉ  አናባፕቲስቶች ግን ስተዋል። ቤተ ክርስቲያን ስታጠምቅ ውሃን ትጠቀማለች፣ በቤተ ክርስቲያን እጅ የሚያጠምቀው እግዚአብሔር ግን በስሙና በቃሉ በተቀደሰው ውሃ በኩል ኃጢአተኛውን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃል። ስለዚህ ጥምቀት ከሰውና በሰው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ነው፣ ከእግዚአብሔር የሆነ ማናቸውም ነገር ደግሞ ቅዱስ ነው፣ ስለዚህም ውሃው ቅዱስ ጥምቀት ነው።

የህጻን ጥምቀት
ይህ "የህጻን ጥምቀት" የሚለው ሐረግም ሆነ "የአዋቂ ጥምቀት" የሚለው ሐረግ በቃሉ ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም፤ በታሪካዊው ትምህርተ ጥምቀት አስተንትኖም እንዲህ ያለ የአዋቂ ጥምቀት የሕጻን ጥምቀት የሚባል ቅዱስ ጥምቀትን በእድሜ የመመደብና የመገደብ አስተሳሰብ ፈጽሞ የማይታወቅ ሆኖ ኖሮአል። ዳሩ ግን ሰዎች፣ ግለሰቦች፣ ቤተስቦች ሲጠመቁ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ እናነባለን። መቼም የቆርነሌዎስ ቤተሰብ (ሐዋርያት 11፥ 13-14)፣ የልድያ ቤተሰብ (ሐዋርያት 16፥ 15)፣ የፍልጵስዩስ ወህኒ ቤት ጠባቂ ቤተሰብ (ሐዋርያት 16፥ 33)፣ የቀርስጶስም ቤተሰብ (ሐዋርያት 18፥ 8)፣ የእስጢፋኖስ ቤተሰብ (1ቆሮንቶስ 1፥ 16) ሲጠመቁ እዚያ ሕጻናት ልጆች አልነበሩም፣ ቢኖሩም እድሜአችሁ ለአቅመ ጥምቀት አልደረሰም ተብለው ከጥምቀት ተከልክለዋል የሚል ዘገባ ምንም የለም። አናባፕቲስቶች የሕጻናት ጥምቀትን ሲቃወሙ ምንም እንኳ መጽሑፍ ቅዱስ  ቤተሰብ እያለ ቢናገርም ይህ ልጆችን አያካትትም የሚል ውሃ የማያነሳ መከራከርያ ያቀርባሉ። ምናልባት እነዚያ ቤተሰቦች ሕጻናት ልጆች ላይኖሩባቸው ይችላል ቢባል እንኳ፣ ልጆች አልነበሩአቸውም ብሎ በድርቅና መገመትም መገገምም አይቻልም። እነዚህ አምስት የተለያዩ ቤተሰቦች በተለያየ ጊዜና አውድ ሲጠመቁ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠመቁ የሚለው ዘገባ ሳይታሰብበት እንዲያው ባጋጣሚ የተጻፈ አይደለም። እንዲያውም ሌሎችም በርካታ ቤተሰቦች እንደተጠመቁ መገመትና ማስተዋል እንችላለን። በእርግጥም እነዚያ ቤተሰቦች ውስጥ ሕጻናት ልጆች እንደነበሩና የጥምቀትም ተካፋዮች እንደነበሩ መገመትና ማሰብ አያስቸግርም። እንዲያውም ቤተሰብ የተሰኘውን ቃል በእስራኤል አውድና ትርጓሜ ያየነው እንደሆነ በአንድ ቤት ውስጥ አብረው የሚኖሩትን እያንዳንዳቸውን የሚያካትት ነው፤ ልጆችም እዚያ የቤተሰብ ቁጥር ውስጥ ይካተታሉ። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቤተሰብ የተሰኘው ስብስብ ምን ግዜም ቢሆን ሕጻናት ልጆችንም የሚያካትት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ስላደረጋቸው ቃል ኪዳናትም በመጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ ምንግዜም ቢሆን ቃል ኪዳኑ ልጆችን ያላካተተ ሆኖ አያውቅም፤ መላው የእስራኤል ማህበረሰብ ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ እና ልጆችን ያካተተ ሲሆን እያንዳንዱም የቃልኪዳኑ ተካፋይ ነው። ወደመርከቡ ገብተው ከጥፋት ውሃ የዳኑት ኖህና ቤተሰቡ ናቸው (ዘፍጥረት 7፥ 1)፤ አብርሃምና መላው ቤተሰቡ ግዝረትን ተቀብለዋል፣ ይስሃቅ ደግሞ በተለይ ገና የስምንት ቀን ሕጻን እያለ የዚህ ኪዳን ተካፋይ ሆኖአል (ዘፍጥረት 17፥ 23፤ 21፥ 4)። በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ አያስቸግረንም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ቤተሰብ በሚልበት ጊዜ ሕጻናት እዚያ ውስጥ አይደመሩም የሚለው መከራከርያ ረጅም ርቀት አያስኬድም።

የህጻናትን ጥምቀት ትክክለኛነትና ተገቢነት መከራከርያ በኖረው የክርስቲያን አስተምህሮና ልምምድ ላይ ብንመሰርተው እንኳ ይህንን ያህል ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለጥያቄ ብሎም በማንም ሳይጠረጠር መኖሩ አስገራሚ ይሆንብናል። የሕጻናት ጥምቀት ከቤተክርስቲያን ጅማሬ አንስቶ ሲለመድ የኖረ፣ ከሐዋርያቱ ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ፣ እኛም እስካለንበት ዘመን ድረስ ቦታና ጊዜ ሳይወስነው የዘለቀ፣ ክርስትናም በተስፋፋባቸው ሃገሮች በየዘመናቱ ሁሉ በመላው አለም በክርስቲያኖች ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሉል አቀፋዊ እምነት፣ ልምምድና ወግ ነው።  ስለሆነም ይህ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ ወግና ልማድ የሆነው ምስክርነት ከራሱ በላይ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት አድልቶ ያመላክታል። ስለ ሕጻናት ጥምቀት ያለን አቋምና ውሳኔም በቅዱሳት መጻህፍት ምስክርነት ላይ የተመሰረተ ደግሞ ነው እንጂ በወግና ልማድ ላይ የተንጠለጠለ ብቻ አይደለም። በድነትና በጥምቀት ጉዳይ እድሜን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያየው የአናባፕቲስቶች ትምህርት ግን ትንታኔውን አድጌአለሁ አገናዝባለሁም ለሚል የሰው አእምሮ እንዲመች አድርጎ ከማቅረብ በቀር፣ መሰረቱን በእግዚአብሔር ቃልም ሆነ በታሪካዊው የስነ መለኮት አውድ ውስጥ ማግኘት የሚቸግረው እንደሆነ ግልጽ ነው።

ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ በድነት ጉዳይ፣ አይደለም የእድሜ ልዩነት ይቅርና በምንም የማይታረቀውን የአይሁድ አህዛብ ልዩነት እንኳ የሻረ ክርስትናን ሰጥቶን እያለ በሰውና በሰው መካከል አድልዎ ለማድረግ፣ ህጻናት ሰዎችንም ከእግዚአብሔር ጸጋ እንዲዘገዩ ለማድረግ በነፍሳት ላይ እኛን ማን ሾሞናል? እንደ ሉተራውያን የወንጌል አማኝ በኦግስቡርግ የእምነት መግለጫ በግልጽ እንደተብራራው በጥምቀት  በኩል ለኃጢአተኛ ሰው የድነት ጸጋ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ሕጻናትም ኃጢአተኛ ሰዎች በመሆናቸው እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ ተጠምቀው የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዲቀበሉ መፍቀድ እንዳለብን፣ በዚህም ጥምቀት አማካኝነት በክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር አደራ የሚሰጡና እርሱን ደስ ለማሰኘት የሚችሉ የተወደዱ ልጆቹ ሊሆኑ ከእርሱ እንደሚወለዱ እናምናለን እናስተምራለንም።

ይህንን ስናምንና ስናስተምርም የዳግመኛ ጥምቀት አስተምህሮና አስተማሪዎች "ህጻናትን ማጥመቅ ልክ አይደለም፣ ህጻናት ያለጥምቀት ሊድኑ ይችላሉ" ብለው ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን ስህተት በአማኞች መካከል አሾልከው እያስገቡ የብዙ ያልተማሩ ምዕመናንን ህይወት ስለሚያቃውሱ በእኛ ዘንድ ፈጽሞ የተወገዙ ናቸው። በዚህም መሰረት ያልተጠመቁ ሕጻናት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች አይደሉም፣ ይልቁን ግን (በተፈጥሮ) ጻድቃንና የዋሆች ናቸው፣ በየዋህነታቸውም አመክንዮአቸውን ሙሉ በሙሉ ወደሚጠቀሙበት ደረጃ ስላልደረሱ ያለጥምቀት ይድናሉ፣ ስለዚህም ጥምቀት ለሕጻናት አስፈላጊ አይደለም፣ ወይም ሕጻናት በአመክንዮ ወደመጠመቅና በራሳቸው ወስነው እምነታቸውን ወደ መግለጥ የእድሜ ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ መጠመቅ አይገባቸውም የሚለው አስተሳሰብ፣ የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚያሳንስ፣ በእግዚአብሔር ጸጋም ብቻ ሳይሆን ድህነትን በሰው የማገናዘብ ችሎታና በማወቅ አቅሙ ላይ የሚመሰርት በመሆኑ፣ እንዲህ ያለውን የትብብር ድነት ፈጽሞ የማንታገሰውና በቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የሌለው ነው። 

አናባፕቲስቶችና ልምምዳቸውን የሚከተሉ ሌሎች መጥምቃውያን ሁሉ በትንሹ ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚቆይ "የጥምቀት ትምህርት" ካላስተማሩ በቀር አያጠምቁም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጥምቀትን በአጣዳፊነቱ እያመለከተ ያመኑት ወዲያውኑ እንደተጠመቁ ያስተምረናል እንጂ ማንንም በጥምቀት ትምህርት ስም ከጥምቀት ሲያዘገይ አናይም። ሕጻናትንም በእድሜ ብስለት ለአቅመ ማገናዘብ እስኪደርሱ በማለት ከጥምቀት አናዘገይም። ክርስትናን ሲቀበል "ወዲያውም …...፤ ተነሥቶ ተጠመቀ፥" የተባለለት ሳውል እንዴት ባለ አጣዳፊ ትእዛዝ እንዲጠመቅ እንደተነገረው ስሙ "አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።"

ህጻናት በተፈጥሮ ጻድቃንና የዋሆች ናቸው የሚለው ይህ አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምረውን መላውን የውርስ ኃጢአት ትምህርትና ከእርሱም ጋር የተያያዘውን ማንኛውንም ነገር ገደል የሚከት አስተሳሰብ ነው። የእምነትንም ተፈጥሮ የሚያሳስት የአስተምህሮ ስህተት ነው። ማንም ቢሆን ላለማመን እንጂ ለእምነት የሚመች ወይም የቀረበ ተፈጥሮ የለውም። ማመን የሚችል የሚሆንለት ሕጻን የሌለውን ያህል ማመን የሚችል የሚሆንለት አዋቂ የለምና። እምነት ለሁሉ አይሆንም፣ "ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፣ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ ማንም የለም" የተባለው ያለ እድሜ ልዩነት ለሁሉ ነው። ኃጢአተኝነት እና መዘዙ ሁሉ የሰው ዘር እጣ ክፍል ነው። ኃጢአተኝነት አስቀድሞ የተደረገ ሳይሆን የተወረሰ ነው። ወላጆች ሞት የሚገባቸው ኃጢአተኛ እፉኝቶች ከሆኑ ልጆችም ርህራሄ የማይደረግላቸው  ኃጢአተኞች፣ እፉኝት የእፉኝት ልጆች ናቸው። እግዚአብሔር ብቻ ሊያድናቸው ሊለውጣቸውም ይችላል እንጂ ከጥምቀት በቀር የሚድኑበት፣ ዳግመኛም ተወልደው የሚለወጡበት ሌላ መንገድ የለም። የሚድኑትም ከውርስ ኃጢአትና ያንን ኃጢአት ተሸርጦ ሊገድላቸው ከሚያደባ የዲያብሎስ ወጥመድ ነው። ጥምቀት ሕፃኑን በሰይጣን ከተያዘበት፣ የኃጢአትና የቁጣ ልጅ ከሆነበት ጽኑ እስራት ይፈታውና፣ ፈጽሞ የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎ ያትመዋል፤ እንጂ ኃይማኖታዊ የውሃ ስርአት (የውሃ ጥምቀት) የሚፈጸምለት አይደለም።  
የውርስ ኃጢአትና መዘዙን የሚያቃልሉ ሰዎች ግን የጥምቀትን ዋጋ ያቃልላሉ። የሕጻን ጥምቀት በእጅጉ የውርስ ኃጢአትን እና መዘዙን ከማስወገድ ጋር የተቆራኘ ነው። የሕጻናትን ጥምቀት የማይቀበሉ ቡድኖች ግን የውርስ ኃጢአትን እውነታ በመካድ ከጸኑ ጴላግዮሳውያንና ማኒቄያውያን ስህተት ጋር ይደመራሉ። አርሜንያኒዝምም የውርስ ኃጢአትን እውነታ በመካድ የዚህ ስህተት አባቱ ነው። አናባፕቲስቶችም የውርስ ኃጢአትን እውነታ "አይኔን ግንባር ያርገው" በሚል ክህደት ዘመኑ ያፈራቸው አርሜንያን ወይም ከፊል ጴላግዮሳውያን ሆነውብናል።

የአምላክን ስም ጠርተን ሕጻኑን በቅዱስ ውሃ ስናጠምቅ ክፉውንና የእድሜ ልክ ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን በመቃወም፣ እንቦቀቅላውን ሕፃን በአምላክ ስም ከእጁ እንናጠቀዋለን። የውርስ ኃጢአት፣ እርሱም የአዳም ኃጢአት ሞትን ለሰው ሁሉ ያደረሰ መዘዘኛ ውድቀት ሲሆን፣ ምንም የማያውቁ ሕፃናትም ቢሆኑ እንኳ ሰለባው ናቸው። ታዲያ ይህንን የሞት ፍርድ በአንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ያለበትን ሕጻን እንዲድን ምን ያህል ዘመን እንታገሳለን? ሕፃናት ምንም ክፋት የሌለባቸው፣ በተፈጥሮም ንጹህና ጻድቃን ናቸው፣ ያለጥምቀትም ይድናሉ አትበሉ። "እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።" የሚለው የዳዊት ምስክርነት ለማንኛውም ለተጸነሰና ለተወለደ ሁሉ ይሰራል። ማናችንም ብንሆን ከአባታችን አዳም ኃጢአት የተነሳ ወደ እግዚአብሔር ያለን አቋቋማችን የጠላትነት አቋቋም ነው። በኃጢአት መወለድ ማለት በአመጸኛው የሰው ዘር ትውልድ ውስጥ መወለድ ማለት ነው። ይህም አዳም እግዚአብሔርን በመቃወም ያቋቋመውና የመሰረተው የጨለማ መንግስት ክፍል ወይም አካል የመሆን ጉዳይ ነው። የአዳም ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የሰው ዘር ሁሉ፣ ህፃናትም ቢሆኑ ያለልዩነት የዚያ ኃጢአት ተካፋይና አድራጊ በመሆን እግዚአብሔርን እምቢ ብሎ ለመግፋት በልደታቸው የመረጡ ናቸው። በዚህ አለም የሚወለደው ሕፃን ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚገባው የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖ የተወለደ ነው። እግዚአብሔር ግን በጥምቀት በኩል ለእርቅ እጁን ዘርግቶለታል።

ይህ አለም አቀፋዊ ኃጢአተኝነትና ለክፋት የተሰጠ ዝንባሌ ሥነ ሰብን ባጠኑ አለማዊ ጠበብት እንኳ የሚታመንና ተቀባይነት ያለው ነው። እነዚህም ጠበብት በጥናቶቻቸው ሰነድ ላይ እንዳሰፈሩት፣ ክፋት ገና ጡት ባልጣሉ ሕፃናት ዘንድ እንኳ ሊገኝ እንደሚችል ያመለክታሉ። ጥናቶቹንም ካደረጉ ማዕከላት መካከል አንዱ እንዳረጋገጠው፣ ወንጀል የሚስፋፋው ከሰው ተፈጥሮአዊ ባህርይና ዝንባሌ እየተወለደ ገና ከሕፃንነት ወራት ጀምሮ አብሮ በሚያድግና በሚኖር ተፈጥሮ እንደሆነ ያሳያል።

ሁሉም ሕጻን ሕይወትን የሚጀምረው በትንሽ አረመኔነት ወይም ጭካኔ ነው። ፈጽሞ ራስ ወዳድና ራስ ተኮር የሆነም ፍጥረት ነው። የሚፈልገውን ማናቸውንም ነገር፣ ጡጦውን ይሁን፣ የእናቱን ቀልብና ልብታ ይሁን፣ አጫዋች አሻንጉሊቱን ይሁን፣ የእንግዳና የሰው ዕቃ ሰአቱን ወይም የሞባይል ስልኩን ይሁን፣ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር የሚፈልገው በሚፈልግበት ሰአት ነው። እነዚህን ፍላጎቶቹን በተከለከለ ጊዜ በዚያ ደካማና ምስኪን አቅመ ቢስነቱ ውስጥ ሆኖም እንኳ ገዳይ ሊሆን በሚችልበት ዝንባሌ በእጅጉ ተናዶና ተቆጥቶ ይመለከታል። ሕጻን መንጻት የሚያስፈልገው የቆሸሸ ሰው ነው፤ ምንም ስነ ምግባር የለውም፣ እውቀት የለውም፣ ጥበብ የለውም። ይህ ማለት እንደዚህ የሆኑት አንዳንድ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ልጆች የሚወለዱት ዱርዬና ወሮበላ ሆነው ነው። አጥኝ ጠበብቶቹ እንደደረሱበት ድምዳሜ አንድ ሕፃን ራስ ተኮር በሆነው የልጅነት ዓለሙ ውስጥ እንዲቀጥል ቢፈቀድለትና ቢተው፣ ፍላጎቶቹንም በራሱ መንገድ እንዲያሟላ ለዚያ ችኩል ስሜቱ ፈቃድ ቢሰጠው፣ ማንኛውም ሕጻን ወንጀለኛ፣ ሌባ፣  ነፍሰ ገዳይ፣ አስገድዶ ደፋሪ ሆኖ ያድጋል። 

ስለውርስ ኃጢአት ወይም ስለመጀመርያው ኃጢአት በእግዚአብሔር ቃል የሰፈረው ትምህርትም ከዚህ ጋር ይስማማል። ኃጢአት ወደ ሰው ሁሉ የደረሰው አዳም በግሉ በሰራው ኃጢአት አማካኝነት ነው። የሰው ልጆችም በእግዚአብሔር ፊት ሞት የሚገባቸው ኃጢአተኞች የሆኑት በውክልና በተሰራ ኃጢአት ነው። አዳም የሁላችን ፌደራል ሄድ ነውና። በዚህ ምክንያት የሰዎች ልጆች ገና ሲጸነሱና ሲወለዱ  ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተለዩ ጠላቶቹ ሆነው ተወልደዋል። ሁላችንም ሞት የሚገባን ርህራሄም የማይገባን ኃጢአተኞች ሆነን የተወለድን ነን። ለዚህ ነው ሕጻን መጠመቅ ያለበት። ሕጻን መጠመቅ የለበትም የሚለው እቋም በ"ወንጌላውያን" መጥምቃውያን ዘንድ በወጉ ያልታሰበበት አደገኛ ውሳኔ ነው። ሕጻን መጠመቅ የለበትም ማለት ሊገድለው በአንገቱ ላይ የተጠመጠመበት የኃጢአት ሞት ይግደለው ብሎ እንደመፍረድ ነው፤ ልክ የተጸነሰና በማህጸን ያለ ልጅ በውርጃ እንዲጨነግፍ የመፍቀድን ያህል የህጻንን ጥምቀት መከልከል ንስሃን የሚጠይቅ አደገኛ ውሳኔ ነው።

የክርስቲያኖች ልጆችም ቢሆኑ ከክርስቲያን አማኞች ወላጆች የተወለዱ በመሆናቸው ያለ ጥምቀትና፣ ወይም ከጥምቀት በፊትም ቢሆን ቅዱሳንና የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው በሚል አስተሳሰብ የዳግመኛ ጥምቀት አስተምህሮን ለመደገፍና የሕጻን ጥምቀትን ውድቅ ለማድረግ የሚቀርበው መከራከርያ በራሱ ዋጋ የሌለውና፣ ክርስትናን ሊሰጠን የተከፈለውን የክርስቶስን ሞት የሚያቃልል የስድብ ትምህርት ነው። ጋራዥ የተወለደ ሁሉ መካኒክ አይሆንም፣ መካኒክ ሊደረግ ግን ይችላል፤ እንዲሁ በክርስቲያን ቤት የተወለደ ሁሉ ክርስቲያን አይሆንም፣ ክርስቲያን ግን ሊደረግ ይችላል። ክርስትናን ባዮሎጂካል ለማድረግ አታስቡ፣ ክርስትና መንፈሳዊ ነው። አንድ ሕጻን ክርስቲያን ሊደረግ የሚችልበት መንፈሳዊ ልደትን ሊሰጠው ከሚችል ጥምቀት በቀር ሌላ ምንም መንገድም እድልም የለም።  ማንም ሰው ማንንም ክርስቲያን ሊያደርገው አይችልም፣ እግዚአብሔር ግን ብቻውን ይችላል፤ እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው ኃጢአትን በጥምቀት እያጠበ ነው። ጥምቀትም ያድናል ስንል ስርአቱ ያድናል እያልን ሳይሆን ክርስቶስ ለአዲስ ልደት ባዘዘው ጥምቀት በኩል ኃጢአታችንን እያጠበ ያድናል ማለታችን ነው እንጂ ሌላ አይደለም። ስለዚህ ጥምቀት ኃይማኖተኛ ሰዎች የሚፈጽሙት ኃይማኖታዊ ተግባር ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ሊመረመር በማይችል አደራረጉ ኃጢአትን እያጠበ አዲስ ልደትን የሚሰጥበት የጸጋ መንገድ ነው። የክርስቲያን ጥምቀት በተገለጠበት በየትኛውም የአዲስ ኪዳን ምንባብ አብሮት ያለውን ልዕለ ተፈጥሮአዊ ተግባር ባለማስተዋል ነገሩን የስርዓት አፈጻጸም ጉዳይ ብቻ አድርጎ መውሰድ ካለመማርና የጥምቀትን ትርጉም ካለመረዳት የሚመጣ ስህተት ነው።

በመሆኑም በክርስቶስ የተገኘው ለሰዎች ሁሉ (ቲቶ 2፥ 11) የሆነው የቤዛነት ሥጦታ እነርሱንም የሚመለከት ነው እንጂ ነጥሎ ያገለላቸው ስላልሆነ ሕጻናትን ማጥመቅ ይገባናል፤ ይህንን የእግዚአብሔርን ስጦታ ወደ ሕጻናቱ እንዳይደርስ የምትከላከል ቤተክርስቲያን ደግሞ የታላቁ ተልዕኮ (ማቴ 28፥ 19) እንቅፋት በመሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቃወማለች። ምክንያቱም ጥምቀት በእምነት በኩል ከክርስቶስ ጋር በመተባበር በአምላክ ስም አጠራር፣ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ወደ ክርስቲያኑ ምኅበረሰብ የምንቀላቀልበት የመጀመርያ እርምጃ ነው። እግዚአብሔር በሉአላዊ ፍቃዱ ሰውን ሲገናኘው እከሌ ትልቅ እከሌ ደግሞ ትንሽ ብሎ አያደላም፤ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አይደለም የተወለዱ ሕጻናት ይቅርና ገና በእናታቸው ማህጸን እያሉ መለኮት በሉአላዊነቱ የጎበኛቸውን መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ማንም ያልተጠመቀ መጠመቅ ይገባዋል አለበለዚያ ድነት በሌላ በማናቸውም መንገድ አይታሰብም። ስለዚህ ጥምቀት በአምላክ ስም የሚከናወን የአምላክ ትዕዛዝ እንጂ በዋዛ የሚታለፍ የጨዋታ ነገር አይደለም። በእግዚአብሔር ስም መጠመቅ ደግሞ በሰዎች መጠመቅ ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሔር መጠመቅ ነው። መጠመቅም በሰዎችም እጅ የሚከናወን የእግዚአብሔር ሥራ ነው። 

በታሪክ፣ እንግዳው የአና ባፕቲዝም አስተሳሰብ በክርስቲያኖች መካከል ሳያቆጠቁጥ በፊት፣ ቤተክርስቲያን በዘመኗ ሁሉ ያለ ጥያቄና፣ ደግሞም ለአፍታ እንኳ ሳትጠራጠር ሕጻናቶችዋን እያጠመቀች ወደ ቅዱሳን ማህበር ስትቀበል ኖራለች።  ከጊዜ በኋላ የመጣው መጤ የእምነት ቡድን ግን ጥምቀትን በሚያቃልል ድምጸት፣ መጠመቅ ውጫዊ ነገር እንደሆነና፣ ውጫዊ ነገሮች ደግሞ ምንም እንደማይጠቅሙ በጩኸት እየተናገረ ለቤተክርስቲያን መከፋፈል ምክንያት ሆኖአል። ነገር ግን ጥምቀት ምንም ያህል ውጫዊ ምልክት ተደርጎ ቢታይም ልዩነት አያመጣም፣ ምክንያቱም ጥምቀትን ያቋቋመልንን፣ የመሰረተልንን እና ያረጋገጠልንን የእግዚአብሔርን ስም የተሸከመው የእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ጸንቶ ይኖራልና። እግዚአብሔር የመሰረተውና ያዘዘው ነገር ጥቅም የሌለው ከንቱ ነገር ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር በክርስቶስ የሻራቸው በርካታ የብሉይ ኪዳን የመንጻት ስርአቶች የመኖራቸውን ያህል ጥምቀት ደግሞ የአዲስ ልደት መታጠብ ሆኖ እግዚአብሔር  በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ለዘላለም ያጸናው አገልግሎትና የጸጋ ስራ ነው። ልንፈጽማቸው የሚያስቸግሩንን ከባባድ የሆኑትን የብሉይ ኪዳን ስርአቶች አስቀርቶልን ልንፈጽመው የምንችለውን ቀላል "የጥምቀት ስርአት" እንደሰጠን የሚመስላቸው ቃሉን በወጉ ያልተማሩ አላዋቂ ሳሚ ሆነው ያስቸግራሉ። ጥምቀት የአፈጻጸም ስነ ሥርአት ሊኖረው ይችላል፣ ኃይማኖታዊ ስርአት ግን አይደለም፤ ጥምቀትን በስርአት ደረጃ አዋርዶ መረዳት በእውነት አላዋቂነት ነው።
 
የክርስቲያን ጥምቀት የህግ ስራ ሳይሆን የእምነትና የጸጋ ስራ፣ የሰው ስራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ስራ የሆነ መለኮታዊ አገልግሎት ነው። ጥምቀት እንደዚያ መሆኑን የማያውቁ ወይም የማይቀበሉ ቡድኖች ሰው ያለጥምቀትም ቢሆን ክርስቲያን ሊሆን እንደሚችል ይመስላቸዋል፤ ይህ ግን ስህተት ነው። ያለጥምቀት ክርስቲያን መሆን አይቻልም ማለት  ያለእምነት መዳን አይቻልም ማለት ነው። በእምነትና በመጠመቅ መካከል ያለው አንድነት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያለ አንድነት ሆኖ እንጂ፣ እንደ ደረጃና ቅደም ተከተል መታየት የለበትም። በአብዛኛው ቃሉን ለማሳከር የሚፈልጉ ሰዎች በማርቆስ የተዘገበውን የታላቁን ተልዕኮ ትዕዛዝ እየጠቀሱ እምነትን ቀዳሚ ጥምቀትን ተከታይ ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፤ ታላቁ ተልዕኮ ግን በማቴዎስም ተዘግቦልናል፣ ማቴዎስ ጥምቀትን አስቀድሞ እምነትን ወይም መማርን አስከትሎ መጻፉን አያስተውሉም። ያም ሆኖ ግን የሁለቱ ወንጌላውያን ትኩረት ልንከተለው የሚገባንን ቅደም ተከተል ማስቀመጥ ሳይሆን፣ ይልቁንም እምነትና ጥምቀት ወይም ጥምቀትና እምነት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ማጽናት ነው። እምነት ስንልም የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ማመን ማለታችን እንጂ የማመን ብቃትና ችሎታ ማለታችን አይደለም። 

ወደር የማይገኝለትን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ባለጠግነት እያሳየ አድናቆትን ከሚሞላኝ መለኮታዊ አገልግሎት መካከል አንዱና ዋናው የሕጻናት ጥምቀት ነው። ሁልጊዜም "ምስጋና ስለ ጥምቀትህ" እያለ ያዘምረኛል። በጸጋው ብቻ እንዲሁ አድኖኛል እንጂ የእኔን የማመን ችሎታና ብቃት አይከታተልም። እኔ ማመን ባልችል እንኳ ቃሉ የታመነ ሆኖ ይኖራል። ስለዚህ ዐብዩን ትኩረትም በተጠመቂው ግለሰብ፣  ህጻን ይሁን አዋቂ፣ በማመን አለማመኑ ላይ ማድረግ አያስፈልግም። ይልቁንም ትኩረታችን ጥምቀቱ ዋጋ ያለው እንዲሆን በሚያደርገው በእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ላይ ጥገኛና ተደጋፊ ሆኖ በመፈጸሙ ላይ ነው እንጂ። ጥምቀትን የሚፈጥረው የኔ ማመን አይደለም፣ እምነት ጥምቀትን ይቀበላል እንጂ ፈጣሪው አይደለምና። ጥምቀትም የተያያዘው ከእምነታችን ጋር ወይም ከአቅመ ማገናዘባችን ጋር ሳይሆን ጸጋን ከተሞላው ከቃሉ ጋር ብቻ ነውና። የእግዚአብሔርን የጸጋ አሰራር ለአእምሮአችን በሚመቸንና እኛን በሚመጥነን የሰብዓዊ ማገናዘብ ልክ ማለትም በውድቀታችን ደረጃ ልንወስነው አንድፈር። እግዚአብሔር በሰጭነቱ የጸጋው ክብር የሚመሰገንበትን፣ ጽድቅንም በመፈጸም ረገድ የሰው ድርሻና ክፍል የሌለበትን ቅዱስ ጥምቀት ሰጥቶናል፤ የማይሰራውን ኃጢአተኛም ሊያድነው የሚችለው ሰራተኛ የሆነው የጸጋው ታላቅነት ብቻ ነው። ቅዱስ ጥምቀትን የምንረዳው በዚያ መንገድ ነው።

እደግመዋለሁ! ሕጻናት ባያምኑ እንኳ፣ (አያምኑም ለማለት ግን አልደፍርም፣ ምክንያቱም ማቴዎስ 18፥6፤ ማርቆስ 9፥42፤ መዝሙር 22፥9 ወዘተ፣ እነዚህን የመሳሰሉ ምንባባት የሕጻናትን እምነት ይመሰክራሉ) በእግዚአብሔር ስም የተቀበሉት ጥምቀት ትክክለኛ ስለሆነ፤ ካደጉም በኋላ ቢሆን ማንም ዳግመኛ እንዲያጠምቃቸው አያስፈልጋቸውም፤ የምን "ጣመኝ ድገመኝ" ነው? የጥምቀት ኪዳን እንደሆነ ለዘላለም ይኖራል። እኛ ግን ከጸጋው ወድቀን ኃጢአትን ብንሰራ መልሰን በድል የምንነሳበትና የምንታደስበት ወደ ጥምቀት ኪዳናችንም የምንመለስበት የንስሃ እድል ተሰጥቶናል እንጂ እንደገና ውሃ ውስጥ መግባት አያስፈልገንም። መቶ ጊዜ በውሃ ውስጥ ብንዘፈዘፍም ከአንዲት ጥምቀት የበለጠ ሊሆንልን አይችልም። ይህንን ባለመረዳት ከእናት ቤተክርስቲያናቸው እየተሰረቁ ኃጢአትን እንደሚፈጽሙ ያህል በግላጭ ሳይሆን ተሸሽገው በመሄድ በዳግመኛ አጥማቂዎች የእምነት ተቋማት ጥምቀታቸውን የሚደግሙ በርካቶች የመኖራቸውን ያህል፣ በዚያው ልክ ከዳግመኛ አጥማቂዎቹ ዘንድ ወደ እናት ቤተክርስቲያናችን እየቀረቡ ለህጻናቶቻቸው የጥምቀት ጥያቄ የሚያቀርቡ ወላጆችም ቁጥር ቀላል አይደለም።

በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከዚህ በበረታ መልኩ ምካቴ ሊጽፉ የሚቻላቸው ከደርዘን በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሉተራን አማኞች መምህራን እንዳሉ አውቃለሁ። እነርሱ ዝም ስላሉና የአዋቂ ጥምቀት አቀንቃኞች "የጣመኝ ድገመኝ" ትምህርታቸውን ስላስጮሁት የጮኸ ሁሉ እውነት ነው ማለት አይቻልም። በህጻናት ጥምቀት ለምታምኑ ሉተራውያን የወንጌል አማኞች ይህች ትንሽ ጽሁፍ እምነታችንን ከአናባፕቲስቶች ጥቃት ለመከላከል መንደርደርያ ልትሆናችሁ ስለምትችል ትጠቀሙባት ዘንድ እየመከርሁ፣ ለሁሉ እንዲደርስ ሼር፣ ላይክ እያደረጋችሁ ወዳጆቻችሁን ሁሉ ታግ አድርጉ።

ይህችን አጭር ምካቴ ሳዘጋጅ ግብአት ሆነው ያገዙኝን፦ The Book of Concord, The Confessions of the Evangelical Lutheran Church; The Theology of Martin Luther; Salvation In Christ, A Lutheran- Orthodox Dialogue; እንዲሁም The Bondage of the Will; የተሰኙትን መጻህፍት ተጠቅሜአለሁ። መምህር ነብዩ ኢሳይያስም በሃሳብ አግዞኛል።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/